በእነዶክተር ወንድወሰን መዝገብ 15 ተከሳሾች በማስረጃ እንዲከላከሉ ተበየነባቸው

የንባብ ጊዜ: 2 ደቂቃ

በእነዶክተር ወንድወሰን አሰፋ መዝገብ ጉዳያቸው እየታየ ያሉ 15 ተከሳሾች የቀረበባቸውን የሽብር ክስ በማስረጃ እንዲከላከሉ ተወሰነ።

ተከሳሾቹ ሐምሌ 15/2015 ዓ. ም. በአማራ ክልል በነበረው ሁከት ተጠርጥረው በቁጥጥር ሥር የዋሉ ናቸው።

በዶ/ር ወንድወሰን አሰፋ ስም በሚጠራው መዝገብ 51 ተከሳሾች የነበሩ ሲሆን፤ አራቱን ጋዜጠኞች መስከረም አበራ፣ ጎበዜ ሲሳይ፣ ዳዊት በጋሻው እና ገነት አስማማውን ጨምሮ 23ቱ ተከሳሾች ባሉበት መዝገባቸው እየታየ ይገኛል።

ጥር 28/2018 ዓ. ም. የዋለው የፌደራል ከፍተኛ ፍርድ ቤት ልደታ ምድብ ሦስተኛ የፀረ ሽብር እና ሕገ መንግሥታዊ ችሎት፤ ስድስቱን ተከሳሾች በነጻ ማሰናበቱን የተከሳሾች ጠበቃ አቶ ሰለሞን ገዛኸን ለቢቢሲ ተናግረዋል።

ሁለቱ ተከሳሾች ደግሞ "አንቀጽ እና የተከሰሱበትን ሕግ በመቀየር ጥፋተኛ ናቸው እና ይከላከሉ ሲል" ፍርድ ቤቱ ብይን መስጠቱን አክለዋል።

የተቀሩት 15ቱ ተከሳሾች ደግሞ በሽብር አዋጁ ቁጥር 1176/12 አንቀፅ 3 ንዑስ ቁጥር 2 ከዕድሜ ልክ እስከ ሞት የሚያስቀጣ ክስ የቀረበባቸው ሲሆን፤ ፍርድ ቤቱ ተከሳሾቹ የጥፋተኝነት ብይኑን በማስረጃ እንዲከላከሉ ለሚያዚያ 26/2018 ዓ. ም. ቀጠሮ መስጠቱን የተከሳሾች ጠበቃ አቶ ሰለሞን ለቢቢሲ ተናግረዋል።

ተከሳሾቹ ከአማራ ክልል ሁከት ጋር በተያያዘ ተጠርጥረው ከተያዙ ሦስት ዓመት ገደማ ይሆናቸዋል።

"ዐቃቤ ሕግ ያቀረበው የድምጽ እና የቴክኒክ ማስረጃ ላይ አስተያየት ከሰጠን ሦስት ወር ሊሆነው ነው። ፍርድ ቤቱ የእኛን አስተያየት ከተቀበለ እና የዐቃቤ ሕግን መልስ ከወሰደ በኋላ [ጥር 28/2018 ዓ. ም.] ብይን ሰጥቷል" ሲሉ ጠበቃው ተናግረዋል።

አራቱን ጋዜጠኞች ጨምሮ 15ቱ ተከሳሾች በሽብር ክስ ጥፋተኛ መባላቸውን አቶ ሰለሞን አስረድተዋል።

"ይህ ድንጋጌ በሽብር አዋጁ ከባዱ ነው። ምክንያቱም የመጨረሻውን የሞት እና የዕድሜ ልክ ቅጣት የሚያስቀጣ የሕግ ድንጋጌ ነው" ብለዋል።

ከተከሳሾቹ መካከል የቀድሞ የሐሮማያ ዩኒቨርስቲ መምህር ዶ/ር ሲሳይ አውግቸው ክስ፤ ከሽብር አዋጁ ቁጥር 1176/12 አንቀፅ 3 ንዑስ ቁጥር 2 ወደ አንቀፅ 9 (ድጋፍ የማድረግ) ክስ በመቀየሩ እና ይህም ዋስትና ስለማያስከለከል እንደ አዲስ ለዋስትና መብት እንደሚከራከሩ ጠበቃው ተናግረዋል።

በሌላ በኩል ከተከሳሾቹ መካከል አቶ ሞላልኝ፣ 4 ቦምብ ይዞ በመገኘት እንደተከሰሱ የተናገሩት አቶ ሰለሞን፤ "ሌሎች ማስረጃዎች አልቀረበቡበትም። ከአንደኛ ተከሳሽ ዶ/ር ወንድወሰን አሰፋ ጋር ስላለው ግንኙነትም ምንም የቀረበ ማስረጃ የለም" ብለዋል።

ተከሳሹ ይዘው የተገኙት ቦምብ "በትግራይ ጦርነት ወቅት ማርከው የታጠቁት" እንደሆነ በማመናቸው በሽብር አዋጅ ሳይሆን ብዛት ያለው ሕገ ወጥ መሣሪያ ይዞ በመገኘት እንዲከሰሱ ተወስኗል።

ክሳቸው ለተቀየረው ሁለቱ ተከሳሾች የዋስትና መብት እንደሚከራከሩ የተናገሩት ጠበቃው፤ 15ቱን በሽብር ክስ ጥፋተኛ የተባሉ ተከሳሾችን በተመለከተ ደግሞ የመከላከያ ዝርዝር ለመስማት ከሚያዝያ 26 እስከ 30/2018 ዓ. ም. ቀጠሮ እንደተሰጣቸው ገልጸዋል።

ከዚህ ቀደም ሐምሌ 25/2015 ዓ. ም. ላይ በእነዶ/ር ወንድወሰን አሰፋ መዝገብ የፍርድ ሒደታቸውን እየተከታተሉ ያሉት ተከሳሾች "የመሃል ዳኛው ጉዳያችንን በገለልተኛነት ሊዳኙ አይችሉም" በሚል በሌላ እንዲተኩላቸው መጠየቃቸው አይዘነጋም።

ከዚያ በፊት ደግሞ ሐምሌ 12/2015 ዓ. ም. ተከሳሾቹ አቅርበውት የነበረው የዋስትና ጥያቄ ውድቅ ተደርጎ፤ ተከሳሾቹን በተመለከተ በመገናኛ ብዙኃን የቀረቡ ዘገባዎች እንዲነሱ ፍርድ ቤት ትዕዛዝ ሰጥቶ እንደነበር ይታወሳል።