ይህ ዝቅተኛ ዳታን በመጠቀም ጽሑፍ ብቻ የሚቀርብበት የቢቢሲ አማርኛ ድረ ገጽ ነው
"የአማራ ክልል 95 በመቶ አካባቢ ሰላም ነው" ጋሻው መርሻ የአብን የሕዝብ ግንኙነት ኃላፊ
የአማራ ብሔራዊ ንቅናቄ (አብን) ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ ወደ ሥልጣን ከመምጣታቸው በፊት ይካሄዱ የነበሩ ሕዝባዊ እንቅስቃሴዎችንተከትሎ በተሰባሰቡ ወጣቶች ነበር ወደ ፓርቲነት ያደገው።
ከለውጡ በኋላም በአማራ ክልል በርካታ ደጋፊዎችን ማፍራት የቻለ አገራዊ የፖለቲካ ፓርቲ ለመሆን በቅቷል። በ2013 ምርጫ የተወዳደሩ የተወሰኑ አመራሮቹ የምክር ቤት መቀመጫ ሲያገኙ ሌሎች ደግሞ መንግሥታዊ ሹመት ይዘው በተለያዩ ተቋማት ውስጥ እያገለገሉ ይገኛሉ።
የሕዝብ ተወካዮቹ በምክር ቤቱ ጠንካራ ሃሳቦችን እና ትችቶችን ከማንሳት ባለፈ ፓርቲው በሚወክለው ሕዝብ ላይ እየደረሱ ነው ያላቸውን በደሎችን እና የመብት ጥሰቶች በጠንካራ መግለጫ ሲያስታውቅ ቆይቷል።
ከቅርብ ጊዜ ወዲህ ግን የፓርቲው እንቅስቃሴ እና ድምጽ እምብዛም አይሰማም። በአባላቱ መካከልም ክፍፍል ተፈጥሯል። ክፍፍሉ ለምን ተፈጠረ? በክልሉ ስለሚካሄደው የትጥቅ እንቅስቃሴ ምን ይላል? እና ሌሎችንም ጥያቄዎች እንዲመልሱልን የፓርቲውን የሕዝብ ግንኙነት ኃላፊ አቶ ጋሻው መርሻን ጋብዘናል።
ቢቢሲ፡ የአማራ ብሔራዊ ንቅናቄ (አብን) ከዚህ ቀደም እንደነበረው ጠንካራ ድምጹ አይሰማም። አብን አሁን ምን ላይ ነው ያለው?
አቶ ጋሻው፡ አብን አለ። በጥሩ ቁመና ላይ ነው ያለው። በቅርቡ ጉባዔ አካሂደናል። አዳዲስ አመራሮችን መርጠናል፤ የነበሩትም ቀጥለዋል። ስለዚህ በጥሩ የድርጅታዊ ቁመና ላይ ነው ያለው።
በአሁኑ ወቅት በኢትዮጵያ ፖለቲካ ውስጥ ከፍተኛ መሳከር ስላለ እና ግጭት የሚካሄድበት ስለሆነ፤ እኛ የምንንቀሳቀስበት አካባቢ ደግሞ ለሦስት ዓመት ገደማ በግጭት ውስጥ ነው ያለው። ከዚህ የተነሳ ሕዝባዊ ስብሰባዎችን ስናካሂድ ላንታይ እንችላለን፤ ነገር ግን ድርጅታዊ ሥራ እየሠራን በጥሩ ቁመና ላይ እንገኛለን።
ቢቢሲ፡ በምትወክሉት ክልል ውስጥ በሚካሄደው ግጭት የሰብዓዊ መብት ጥሰቶች እየተፈጸሙ እና ቀውሶች እያጋጠሙ እንደሆነ ሪፖርቶች ይወጣሉ። ሆኖም አብን በዚህ ላይ መግለጫ ሲያወጣ አይታይም። ለምንድን ነው?
አቶ ጋሻው፡ ጠንካራ መግለጫ ሲያወጡ አይታይም የሚለው የአረዳድ ጉዳይ ነው። ፓርቲው አሁንም ጠንካራ ነው። ሁልጊዜ ለሕዝብ የወገነ ፓርቲ ነው። ሕዝብ ተበድሏል፤ ሥርዓት ተጓድሏል ብለን ባሰብን ጊዜ ሁሉ መግለጫዎችን እናወጣለን፤ ጋዜጣዊ መግለጫዎችን እንሰጣለን። አስፈላጊ የሆኑ ትግሎችንም እናካሂዳለን።
ምናልባት በጣም ስሜታዊ በሆነ መልክ፣ ስሜት ኮርኳሪ በሆኑ ቃላት አልተናገራችሁም ወይም ደግሞ ነገሩን የሚያባብስ ነገር አልተናገራችሁም የሚል ግምገማ ከዚህም ከዚያም እንሰማለን። ያ ግን ፖለቲካ አይደለም። ፖለቲካ በስሌት እንጂ በስሜት የሚሠራ አይደለም። እኛ በነበርንበት ቁመና ላይ ነው ያለነው። ከነበርንበት ቁመና ላይ አንድ ስንዝር እንኳን አልራቅንም።
ቢቢሲ፡ በተለይ ግጭቱ ከተቀሰቀሰ ወዲህ በክልሉ እየደረሱ ያሉ በርካታ ሰብዓዊ እና ማኅበራዊ ቀውሶች ነቅሳችሁ ያወጣችሁበትን መግለጫ አልታየም። በክልሉ ምን እየተካሄደ እንዳለ እየደረሰ ያለው ቀውስ ምን ያህል እንደሆነ ታውቃለችሁ?
አቶ ጋሻው፡ በየወረዳው እና በየዞኑ ከዚያም አልፎ በቀበሌዎች ተወካዮች አሉን፤ እንመዘግባለን። በክልሉ ብቻ ሳይሆን የአገሪቷን የፖለቲካ ሁኔታ እንገመግማለን፤ ምልከታ እንይዛለን። አንዳንዶቹ ግን ለሕዝብ መቅረብ የሌለባቸው ነገሮች አሉ። ችግሩን ከመፍታት ይልቅ ሊያባብሱ የሚችሉ ነገሮች አሉ።
ፖለቲካ ስለሆነ የምንሠራው እንደ ሒሳብ አንድ ሲደመር አንድ ሁለት ተብሎ የሚገለጽ አይደለም። ያለው ጥቅም እና ጉዳት ታይቶ የትኛው ይጠቅማል ብለን ነው መረጃዎችን የምናጋራው። ለዛሬ ብቻ ሳይሆን ለወደፊትም የትኛው ነው ሕዝብን ከሕዝብ ሊያኗኑር የሚችለው፣ የትኛው ነው ሕዝብን የሚጠቅም? ከሚል እና ከጊዜያዊ ስሜት በተሻገረ ሁኔታ 'ስትራቴጂካሊ' አስበን አንዳንድ መረጃዎችን እናጋራለን።
በአጠቃላይ ግን በክልሉ ከፍተኛ ውድመት እየተካሄደ ነው። ትምህርት ቤቶች ተዘግተዋል። ጤና ጣቢያዎች በአግባቡ እየሠሩ አይደለም። እናቶች ወደ ጤና ጣቢያ ሄደው እየወለዱ አይደለም። ተላላፊ እና ተላላፊ ያልሆኑ በሽታዎች በከፍተኛ ሁኔታ እየተስፋፉ ነው። የሰብዓዊ እና ቁሳዊ ውድመቱ በጣም ከፍተኛ ነው። ይህንን ሁሉ እየሰነድን ነው። ምክንያቱም የምንኖረው እዚሁ አገር ነው። አባሎቻችን አማራ ክልልን ጨምሮ በመላው ኢትዮጵያ ነው ያሉት።
ያለንን መረጃ ሁሉ የሕዝቡን ስሜት ሊኮረኩር በሚችል መልኩ ማቅረብ አይኖርብንም። ኃላፊነት የሚሰማን ሰዎች ነን። ችግሩን ግን በአግባቡ እና በልኩ እየገለጽን መጥተናል። የመንግሥት ባለሥልጣናትን፣ የፀጥታ ሰዎችን አልፎ አልፎም በግጭቱ ተሳታፊ የሆኑ ኃይሎችን እያገኘን ወደ ጠረጴዛ እንዲመጡ እና በውይይት ችግሩ እንዲፈታ የምንችለውን እየሞከርን ነው።
ቢቢሲ፡ አብን በፊት በነበረበት ቁመና ላይ እንደሚገኝ ገልፀውልኛል። ነገር ግን ያለፈውን ምርጫ ተከትሎ የተወሰኑ የፓርቲው አመራሮች የመንግሥት ሥልጣን መያዛቸውን ተከትሎ በፓርቲው አመራሮች መካከል ክፍፍል ተፈጥሯል። ምክንያቱ ምንድን ነው?
አቶ ጋሻው፡ ይህ ግምገማ ትክክለኛ ነው ብዬ አላስብም። አንዳንድ የፓርቲው አመራሮች የመንግሥት ሥልጣንን በራሳቸው ጊዜ አልያዙም። ገምግመን ከመንግሥት ጋር መሥራት አለብን ብለን አቅጣጫ አስቀምጠን ነው ይህ የሆነው። ይህ በሆነበት ሁኔታ አንዳንድ አካላት ከመንግሥት ጋር ስለሠሩ ቅሬታ እንደተፈጠረ እና በፓርቲው ውስጥ ሽኩቻ እንደተፈጠረ የሚነገረው ነገር ስህተት ነው።
ቢቢሲ፡ ክፍፍል አልተፈጠረም ነው የሚሉት?
አቶ ጋሻው፡ ክፍተቱ የተፈጠረው በመንግሥት ኃላፊነት ላይ ከመሥራታችን ጋር በተያያዘ አይደለም። ምናልባት ምክንያት ሆኖ ሊሆን ይችላል፤ ነገር ግን ከዚህ ያለፈ የፖለቲካ አስተሳሰብ ልዩነት ነበረን። ለምሳሌ በጉልበት በትጥቅም ቢሆን መንግሥትን መገልበጥ አለብን ብለው የሚያምኑ ኃይሎች ነበሩ። ሰላማዊ እና ሰላማዊ ትግል ብቻ ነው አዋጩ የምንል ኃይሎች ነበርን። ዋናው የግጭቱ ማዕከል እዚህ ጋር የተያያዘ የነበረ እንጂ ከመንግሥት ጋር መሥራት፣ አለመሥራት የሚለው አይደለም። ይህን ቅሬታም የሚያነሱ ሰዎች በጎን 'ሹሙኝ' ብለው ለመንግሥት ደብዳቤ ያስገቡ ናቸው።
እዚህ አገር ፖለቲካ ላይ የተለመደው ነገር አንዱ ዝም ብሎ ይከስሳል፤ ከዚያ በኋላ ሕዝብ ጋር ይሄድና ጥያቄም ሳይቀርብበት ሃሳብ ሆኖ ይቀጥላል። ነገር ግን ከመንግሥት ጋር አብረው እየሠሩ ትግላችንን ሸጠዋል የሚሉ ሰዎች በጎን 'እኛን ሹሙን፤ ከእነርሱ የተሻለ እኛ እናገለግላለን' ብለው ደብዳቤ ያስገቡ ሰዎች ናቸው። በስምም ጠቅሶ መናገር ይቻላል።
ቢቢሲ፡ ፓርቲውን ወክለው የምክር ቤት አባል የሆኑት ዶ/ር ደሳለኝ ጫኔ በቅርቡ በመጪው ምርጫ እንደማይወዳደሩ አስታውቀዋል። ሌላኛው የምክር ቤት አባል አበባው ደሳለውም ሌላ ፓርቲ እንደተቀላቀሉ ገልጸዋል። አቶ ክርስቲያን ታደለም እስር ቤት ናቸው። እነዚህ ሰዎች ለክልሉ ሕዝብ የፓርቲው አመራሮች የነበሩ ናቸው። እነርሱ በሌሉበት ፓርቲው በቀደመው ቁመና ላይ ነው ማለት ይቻላል?
አቶ ጋሻው፡ በመጀመሪያ ደረጃ እነዚህን ሰዎች በሥነ ምግባር ግድፈት ከፓርቲው የተባረሩ ናቸው። ሲያራምዱ የነበረው የፓርቲውን አቋም ሳይሆን የራሳቸውን የግለሰብ አቋም ነው። ይህንን አሳውቀናል። ስለዚህ የፈለጉትን መምረጥ ይችላሉ። ያባረርናቸው በሥነ ምግባር ጉድለት ነው። የሚያደርጉት ትግልም ለአማራ ሕዝብ የሚደረግ ትግል ነው ብለን እንደ ፓርቲም አናምንም፤ እኔም እንደ ግለሰብ አላምንም።
የሻዕቢያን የውክልና እንቅስቃሴ ነው የሚያካሂዱት። የአማራ ሕዝብ ትግልን አይደለም የሚያካሂዱት። ይህን እኛ በግልጽ ተናግረናል። በዚህም ምክንያት ከፓርቲው አባረናቸዋል።
ይህ በፓርቲው ላይ ምንም የተለየ ተፅዕኖ አያመጣም። ግለሰቦች ይሄዳሉ፤ ግለሰቦች ይመጣሉ። የአማራ ሕዝብ እና ፓርቲ ግን ቀጣይ ናቸው። ምናልባት አንዳንድ በሚዲያ የሚጮሁ ሰዎች በጣም ከፍተኛ ተፅዕኖ ያላቸው መስለው ይታያሉ። በፓርቲ ሥራ ግን እዚህ ግባ የሚባል ሥራ ሠርተው አያውቁም፤ ነገር ግን በጣም በተኳኳለ ቃል እና ከፍተኛ የሆነ ጩኸት በማስተጋባት ዋነኛ የፓርቲው ሰዎች መስለው የሚታዩ ነበሩ። የእነርሱ መምጣትም ሆነ መሄድ በፓርቲው ላይም ሆነ በአማራ ሕዝብ ላይ የሚፈጥረው ነገር የለም፤ አይኖርምም።
ቢቢሲ፡ በመንግሥት ሹመት ላይ ያላችሁ የፓርቲው አመራሮች ደግሞ የመንግሥትን ሃሳብ አስፈፃሚ እንጂ ለሕዝብ የቆማችሁ አይደላችሁም ተብላችሁ ትከሰሳላችሁ። ለዚህ ያለዎት ምላሽ ምንድን ነው?
አቶ ጋሻው፡ እንግዲህ እኛ ነባር ፖለቲከኞች ነን። የዚህን አገር ፖለቲካ ከየት ወዴት የምናውቅ ሰዎች ነን። ገና ለገና ሃሳባችን ከመንግሥት ስለገጠመ ከመንግሥት ጋር አብረው ናቸው እንዳንባል ብለን ልንቃወም አንችልም።
ከመንግሥት ጋር በምንስማማበት ጉዳይ አብረን እየሠራን እንቀጥላለን። ከመንግሥት ጋር ልዩነት ባለን ጉዳይ ላይ ደግሞ መንግሥት ላይ ተፅዕኖ እየፈጠርን የምንችለውን እያደረግን እንቀጥላለን። ይህ የሠለጠነ የፖለቲካ አካሄድ ነው። መጯጯህ እና ስሜታዊ በሆኑ ቃላት ሕዝብን ማስቆጣት ፖለቲካ ሳይሆን ስሜት ነው።
ፖለቲካ የስሌት ጉዳይ ነው። እኛ ትክክለኛው አቋም ላይ ነው ያለነው። ፓርቲው ከማንኛውም ጊዜ በተሻለ የጠራ ሃሳብ እና የጠራ አቋም ያላቸው አመራሮች በሚመሩት ወቅት ላይ ነው ያለው። ተግባራዊ የሆነ እንቅስቃሴ ላይ ነው ያለነው። ፓርቲውም፣ የተጠቀሱት ሰዎችም ከመንግሥት ጋር የሚሠሩትም አገራቸውን እያገለገሉ ነው ያሉት።
በአብዛኛው በአማራ ሕዝብ ስም የሚደረግ ጩኸት ለሻዕቢያ እና ለወያኔ የሚደረግ ራስን የማሳየት ጩኸት እንጂ ለአማራ ሕዝብ የሚጮህ ጩኸት ነው ብለን አናምንም። አየን እኮ! ለአማራ ሕዝብ በጠመንጃ መንግሥት እንጥልልሃለን ያሉት ሰዎች የአማራን ሕዝብ ጥለው አሳዩን እኮ። በጩኸት በጫጫታ ሕዝብን በፕሮፖጋንዳ በማደንዘዝ ምን ያህል ዋጋ እንደተከፈለ አየን እኮ!
ለሦስት ዓመት ትምህርት ቤት አልተከፈተም። በሚሊዮን የሚቆጠሩ ተማሪዎች ከትምህርት ገበታ ውጪ ናቸው። ኢንዱስትሪዎች ከሥራ ውጪ ናቸው። መሠረተ ልማቶች እየወደሙ ነው። የትምህርት ቤት ጣራ ተገፎ እየተሸጠ ነው። ይህንን የሚቀሰቅሱ ሰዎች ታጋይ ሆነው እኛ ከሃዲ የምንሆንበት ምንም ዓይነት የሞራልም፣ የመርኅም ሌላም ምክንያት የለም።
ምን አልባት ሕዝብ መስማት የሚፈልገውን መናገር እና እንዲሆንለት የሚፈልገውን ማድረግ የተለያዩ ናቸው። እኛ ሕዝብ እንዲሆንለት የሚፈልገውን፣ ቢሆንለት ይጠቅመዋል የሚለውን በመሥራት ላይ እንገኛለን።
ቢቢሲ፡ ወደ ምርጫ እንምጣ። በተለያዩ የአገሪቱ ክፍል በሚካሄዱ ግጭቶች ምክንያት አስቻይ ሁኔታ የለም ሲሉ ስጋታቸውን የሚገልጹ አሉ። እናንተ የምትወክሉት ሕዝብ ግጭት ውስጥ ነው ያለው። እናንተስ አስቻይ ሁኔታ አለ ብላችሁ ታምናላችሁ?
አቶ ጋሻው፡ ዲሞክራሲ የአንድ ቀን ሥራ አይደለም። ሁልጊዜ በአበባ ላይ መራመድም አይደለም። አንዳንዴ ተግዳሮቶችን ማለፍም ያስፈልጋል። ሁኔታው የተመቸ ስለሆነ አይደለም እኮ የምንታገለው። ሁኔታው የተመቸ ቢሆንማ ፓርቲ አቋቁመን አንታገልም ነበር እኮ። የተመቸ ሁኔታ ስለሌለ ነው ፓርቲ አቋቁመን እየታገልን ያለነው።
ቢቢሲ፡ስለድሎትና ምቾት አይደለም ያነሳሁት። ወደ ክልሉ ሄዶ ከሕዝብ ጋር መወያየት ያስፈልጋል። ክልሉ ግጭት ውስጥ ነው። ነዋሪዎችም አስቸጋሪ ሁኔታ ውስጥ እንዳሉ ነው የሚናገሩት።ይህንን እንዴት ነው የምትጋፈጡት?
አቶ ጋሻው፡ ፖለቲካ ማለት ይህንን መጋፈጥ ነው። ነገሩ ሁሉ አልጋ ባልጋ ከሆነማ እኛም ወደ ሌላ ሥራ እና ልጆቻችን ወደ ማሳደግ እንሄድ ነበር እኮ። ነገር ግን ይህንን ፈተና ተጋፍጦ እዚያ ተግዳሮት ጋር በሚደረግ ትግል የሚመጣ ውጤት ነው የፖለቲካ ውጤት የምንለው።
ሆኖም አገሩ ሰላም በሰላም ነው፤ ፍቅር በፍቅር ነው እያልኩ አይደለም። ትግራይ፣ አማራ፣ ኦሮሚያ፣ ጋምቤላ፣ ቤኒሻንጉል ጉሙዝ እንዲሁም በየቦታው ግጭት አለ፤ ግን አጠቃላይ የአገሪቱ መገለጫ አይደለም።
የተወሰነ የተወሰነ ኪስ ቦታዎች እና ወረዳዎች ላይ ግጭት አለ። ለምሳሌ አማራ ክልልን ብንወስድ ከ95 በመቶ በላይ ያለው አካባቢ ሰላም ነው።
ግጭቱ በከፍተኛ ሁኔታ ስለሚጮህ አገሩ በሙሉ ችግር ውስጥ ያለ መስሎ ስለሚታይ ነው እንጂ ኪስ ቦታዎች ላይ ነው ግጭቶች ያሉት። እነዚያ ቦታዎችም ላይ ቢሆን አስፈላጊ ነው የሚል እምነት የለንም። የሚገለውም የሚሞተውም የራሳችን ወንድሞቻችን ናቸው። ይህ የመገዳደል አዙሪት በቃን ማለት ይገባል የሚል ከፍተኛ የሆነ ፅኑ አቋም አለን።
ይህም እስከ ግንቦት ድረስ የመሻሻል ዕድል ይኖራል የሚል ተስፋ አለኝ። ባይሆንም እንኳን ባለው ፈተና ውስጥ አልፎ መውጣት ነው እንጂ ፖለቲካ ትግል የሚባለው አበባ እየተነሰነሰ በእርሱ ላይ መራመድ አይደለም። ፈተና ሲኖር የምንወጣበት፤ ፈተና ሳይኖር ደግሞ ከፊት ለፊት የምንቀድምበት አይደለም። ይህ ነው ፖለቲካ፣ ሕዝባዊነት፣ ከሕዝብ ጋር መወገን ማለት። ስለዚህ ምንም እንኳ ችግር ቢኖርም ያን ችግር ለመጋፈጥ ዝግጁ ነን።
በቢሲ፡ ቀደም ብለው የቀድሞ የፓርቲው አመራሮች 'በጉልበት በትጥቅም ቢሆን መንግሥትን መገልበጥ አለብን ብለው የሚያምኑ ኃይሎች ነበሩ' ሲሉ ከሰዋል።በአማራ ክልል በሚካሄደው የትጥቅ ግጭት ውስጥ እነዚህ የቀድሞ የፓርቲው አመራሮች እጃቸው አለበት ወይም ምክንያት ናቸው ብላችሁ ታምናላችሁ?
አቶ ጋሻው፡ እሱን መንግሥት ያጣራ። እሱን አላልኩም። እሱን መንግሥት ነው ማጣራት ያለበት። እኔ ፖለቲከኛ ነኝ የፖለቲካ አስተያየት ነው የምሰጠው እንጂ ከእዚህ ታጣቂ ጀርባ እገሌ ነው የሚያደራጀው የሚል ሃሳብ የለኝም። ነገር ግን በአማራ ክልል የሚደረገው ትግል የትጥቅ ትግል ነው ብዬ አላምንም። የሻዕቢያ እና የወያኔ የውክልና ጦርነት ነው የሚል በጣም ፅኑ አቋም ነው ያለኝ።
ቢቢሲ፡ . . . እዚህ ድምዳሜ ላይ የደረሳችሁት በምን ምክንያት ነው? መንግሥት ስለሚል ነው ወይስ ተጨባጭ መረጃ አላችሁ?
አቶ ጋሻው፡ በነገርሽ ላይ ባያዝድ [ወገንተኛ] ናችሁ።
ቢቢሲ፡ ወገንተኛ አይደለንም። ጥያቄ ነው የጠየቅክዎት። ተጨባጭ መረጃ አላችሁ ወይ?
አቶ ጋሻው፡ እኔ እዚህ አገር ነው የምኖረው። የዚህችን አገር እያንዳንዷን እንቅስቃሴ የማውቅ ሰው ነኝ። ላለፉት 20 ዓመታት የፖለቲካ እንቅስቃሴ ውስጥ እያንዳንዱን መውጣት መውረድ ተከታትያለሁ፤ ተሳትፌያለሁ። 'መንግሥት ስለሚል ነው ወይ?' ብለሽ መጠየቅሽ ለእኔ ስድብ ነው። መንግሥት ሰዎች ናቸው እንደኔ።
አማራ ክልል ውስጥ በሚደረግ ውጊያ ላይ የሻዕቢያ እና የወያኔ ሰዎች ይማረካሉ። የአማራ፣ የኦሮሚያ ፣ የጋምቤላ፣ የቤኒሻንጉል ጉሙዝ እንዲሁም ሌሎችም ታጣቂዎች ኤርትራ ሄደው፤ ትግራይ ሄደው ሠልጥነው ይመጣሉ። መሳሪያ ይላካል፤ ይያዛል። እዚህ እኮ ነው ያለነው። ይህ ተጨባጭ ማስረጃ አይደለም እንዴ? ወስጄ ላሳይሽ እንዴ? የምን ተጨባጭ መረጃ ነው የምትይኝ። ቢቢሲ አማርኛ ለወያኔ የሚያደላ ሚዲያ ነው። እንዲያውም የህወሓት ሚዲያ ሴንተር ነው። እውነት እንነጋገር ከተባለ . . . [አቶ ጋሻው በቁጣ ስልካቸውን ዘግተው ቃለ መጠይቁን አቋረጡ]. . .