ይህ ዝቅተኛ ዳታን በመጠቀም ጽሑፍ ብቻ የሚቀርብበት የቢቢሲ አማርኛ ድረ ገጽ ነው
አሜሪካ እና ኢራን የፕሬዝዳንት ትራምፕን ጥቃት ሊያስቀር ይችላል የተባለ ወሳኝ ንግግር ዛሬ ያደርጋሉ
የአሜሪካ እና የኢራን ባለሥልጣናት ፕሬዝዳንት ትራምፕ የተዘጋጁበትን ጥቃት ሊያስቀር ይችላል የተባለውን ሦስተኛ ዙር ቀጥተኛ ያልሆነ ንግግር ዛሬ [ሐሙስ] ስዊትዘርላንድ ውስጥ ያደርጋሉ።
ፕሬዝዳንት ዶናልድ ትራምፕ የኒውክሌር ስምምነት ላይ ካልተደረሰ ኢራን ላይ ጥቃት ላይ እንደሚሰነዝሩ ዝተዋል።
ውይይቱ የሚካሄደው በመካከለኛው ምሥራቅ በአውሮፓውያኑ 2003 አሜሪካ ኢራቅን ከወረረች ወዲህ ትልቁ ነው የተባለ የአሜሪካ ወታደራዊ ኃይል በተሰማራበት ወቅት ሲሆን ኢራን ጥቃት ቢፈጽምባት ምላሽ እንደምትሰጥ አስጠንቅቃለች።
ውይይቶቹ ግጭትን ለመከላከል የመጨረሻ ጥረት ተደርገው ቢወሰዱም፣ ስምምነት ላይ የመድረስ ዕድል ላይ ግን ግልጽ የሆነ ነገር የለም።
ትራምፕ ቀውሱን በዲፕሎማሲ መንገድ መፍታት እንደሚመርጡ ቢናገሩም፣ መሪዎቿ ስምምነቱን እንዲቀበሉ ጫና ለመፍጠር በኢራን ላይ የተመጠነ ጥቃት ለመፈፀም እያሰቡ መሆኑንም ተናግረዋል።
ዶናልድ ትራምፕ ከዚህ ድርድር ምን እንደሚፈልጉ እና አሁን ወታደራዊ እርምጃ መውሰድ ለምን አስፈላጊ ሊሆን እንደሚችል ለማስረዳት ብዙም ጥረት አላደረጉም።
ባለፈው ዓመት ሰኔ ወር ላይ በኢራን እና በእስራኤል መካከል ለ12 ቀናት ጦርነት በተካሄደበት ወቅት አሜሪካ የኢራን የኒውክሌር ተቋማትን ደብድባለች።
ኢራን በግዛቷ ውስጥ ዩራኒየም ማበልጸግ እንድታቆም አሜሪካ ያቀረበችውን ጥያቄ ውድቅ አድርጋለች።
ነገር ግን በኒውክሌር ፕሮግራሟ ላይ አንዳንድ ለውጦችን ለማድረግ ዝግጁ መሆኗን የሚያሳዩ ምልክቶች አሉ።
በሁለቱ አገራት መካከል በኦማን አደራዳሪነት እየተካሄዱት ባሉት ንግግሮች የኢራንን ልዑክን የሚመሩት የውጭ ጉዳይ ሚኒስትሩ አባስ አራጋቺ ሲሆኑ፣ አሜሪካ በኩል ደግሞ የፕሬዝዳንቱ ልዩ መልዕክተኛው ስቲቭ ዊትኮፍ እና የትራምፕ አማች ጃሬድ ኩሽነር ናቸው።
ከቅርብ ጊዜ ወዲህ አሜሪካ በሺህዎች የሚቆጠሩ ወታደሮቿን እንዲሁም ሁለት የጦር ጄቶች ተሸካሚ መርከቦችን እንዲሁም የጦር አውሮፕላኖችን እና ነዳጅ የሚመሞሉ አውሮፕላኖችን ወደ ቀጣናው አሰማርታለች።
ትራምፕ ኢራን ላይ የአየር ድብደባ ለመፈጸም የዛቱት ባለፈው ወር በአገሪቱ የተካሄደውን ሕዝባዊ አመጽ ለማፈን ከፍተኛ ወታደራዊ እርምጃ በወሰደችበት እና በሺህዎች የሚቆጠሩ ተቃዋሚዎች በተገደሉበት ወቅት ነበር።
ከዚያ ወዲህ ግን የትራምፕ ትኩረት ምዕራባውያን ከኢራን ጋር ላላቸው አለመግባባት ማዕከል የሆነው የኒውክሌር ፕሮግራም ሆኗል።
ለአስርት ዓመታት እስራኤል እና አሜሪካ አገሪቱ በምሥጢር የኒውክሌር ፕሮግራሟን ትገነባች እያሉ ሲወነጅሏት ነበር።
ኢራን ግን በተቃራኒው የኒውክሌር ፕሮግራሟ ለሰላማዊ አገልግሎት ብቻ የሚውል መሆኑን በመግለጽ ትከራከራለቸ።
ትራምፕ ማክሰኞ ዕለት ለኮንግረስ ባደረጉት ንግግር፣ ከኢራን ጋር ስላለው ውጥረት አጭር ነገር ቢያነሱም ጥቃት ለመፈጸም ስለማሰባቸው ግን ያሉት ነገር የለም።
በዚህ ንግግራቸው ላይ ዝርዝር መረጃ ሳይሰጡ ኢራን "በቅርቡ" ወደ አሜሪካ የሚደርሱ ሚሳዔሎችን ለመገንባት እየሠራች መሆኑን ተናግረዋል።
ባለፈው ዓመት የተፈጸሙትን ጥቃቶች ተከትሎ አገሪቱ የኒውክሌር ጦር መሳሪያ ፕሮግራሟን "እንደገና ለመጀመር" እየሞከረች ነወ ሲሉ ከስሰዋል።
"በዓለም ላይ ቁጥር አንድ የሽብር ደጋፊ...የኒውክሌር ጦር መሣሪያ እንዲኖረው" መፍቀድ እንደማይቻልም ተናግረዋል።
ይሁን እንጂ የኢራን የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ይህ የትራምፕ ንግግር ከተደረገ ከጥቂት ሰዓታት በኋላ በማኅበራዊ ሚዲያ ገፁ ላይ ኢራን "በምንም ዓይነት ሁኔታ የኒውክሌር ጦር መሣሪያ ግንባታ እያደረገች አይደለም" ሲል ጽፏል።
የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር አራግቺ "የጋራ ጉዳዮችን የሚፈታ እና የጋራ ጥቅምን የሚያስገኝ ታይቶ የማይታወቅ ስምምነት ለማድረግ ታሪካዊ አጋጣሚ" እንዳለ ተናግረዋል።
የኢራን የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ቃል አቀባይ ለትራምፕ ንግግር ምላሽ ሲሰጡ፣ አሜሪካ ስለ ኒውክሌር ፕሮግራሟ፣ ስለ ባላስቲክ ሚሳዔሎች እና የተገደሉትን ተቃዋሚዎች ቁጥር በተመለከተ "ትልልቅ ውሸቶችን" እየደጋገመች ነው ሲሉ ተችተዋል።