የማንቸስተር ዩናይትዱ አሠልጣኝ ሩበን አሞሪም ለምን ተባረረ?

ማንቸስተር ዩናይትድ አሠልጣኝ ሩበን አሞሪምን ማባረሩን አስታውቆ እስከ ውድድር ዘመኑ መጨረሻ ድረስ የሚቆይ ጊዜያዊ አሠልጣኝ እንደሚተካ ገልጿል።

ዩናይትድ ረቡዕ ከበርንሊ ጋር በሚኖረው ጨዋታ የቀድሞው የክለቡ አማካይ ዳሬን ፍሌቸር ቡድኑን እየመራ ወደ ሜዳ ይገባል።

ስኮትላንዳዊው አማካይ ጊዜያዊ አሠልጣኝ እስኪሾም ድረስ ነው ቡድኑን የሚመራው። ቀጥሎ የሚሾመው ጊዜያዊ አሠልጣኝ አሞሪምን የሚተካ ቋሚ መሪ እስኪመጣ ድረስ እንደሚቆይም ተሰምቷል።

ባለፈው አርብ አሞሪም በሰጠው ጋዜጣዊ መግለጫ ከክለቡ አመራሮች ጋር ግጭት ውስጥ እንደገባ የሚጠቁም ነበር።

በጥር ወር የተጫዋቾች ዝውውር መስኮት ክለቡ ሊደግፈው እንደማይችልም ተናግሯል።

ቡድኑ እሑድ ዕለት ከሊድስ ጋር የነበረው ጨዋታ 1-1 የተጠናቀቀ ሲሆን፣ ከግጥሚያው በኋላ ፖርቹጋላዊው አሠልጣኝ ከክለቡ አመራሮች ጋር እሰጥ አገባ ውስጥ እንዳለ የሚጠቆም አስተያየት ሰጥቷል።

አክሎም ኮንትራቱ ሲጠናቀቁ ክለቡን ለቆ ለመሄድ ዝግጁ መሆኑን ተናግሯል።

ይህን በተናገረ 24 ሰዓታት ሳይሞላው ነው ዩናይትድ ለ14 ወራት ካገለገለው አሠልጣኝ ጋር መለያየቱን ያስታወቀው።

"ክለቡ በፕሪሚዬር ሊጉ ስድስተኛ ደረጃ ላይ ነው የሚገኘው። አሁን ባለው ሁኔታ ለውጥ መኖር እንዳለበት የክለቡ አመራር ያምናል" ይላል የዩናይትድ መግለጫ።

"ክለቡ ሩበን አሞሪም ላደረጉት አስተዋፅዖ ምስጋናውን እያቀረበ በመጪው ዘመኑ መልካም ዕድል እንዲገጥመው ይመኛል።"

አሞሪም የአሠልጣኝ ቡድናቸውን ይዘው ነው ክለቡን የለቀቁት።

ባለፈው ጥቅምት የዩናይትድ ጥምር ባለቤት የሆኑት ሰር ጂም ራትክሊፍ "አሠልጣኙ ታላቅ መሆናቸውን ለማሳየት" ሦስት ዓመት እንደሚሰጧቸው ተናግረው ክለቡ "ትዕግስት" እንደሚኖረው ጠቁመው ነበር።

ነገር ግን የቢቢሲ ስፖርት ምንጮች እንደሚሉት በያዝነው የውድድር ዘመን የአሞሪም ዩናይትድ ይህ ነው የሚባል ለውጥ ባለማሳየቱ ነው አሠልጣኙ እንዲነሱ የተደረገው።

የ40 ዓመቱ አሠልጣኝ በአውሮፓውያኑ ኅዳር 2024 ነው በ11 ሚሊዮን ዩሮ ከፖርቹጋሉ ስፖርቲንግ ክለብ የመጡት።

አሞሪም የቀያይ ሰይጣኖቹ አሠልጣኝ ሆነው በቆዩበት ጊዜ 63 ጨዋታዎች አድርገው 25 አሸንፈዋል። ለ14 ወራት በኦልድ ትራፈርድ የቆዩት አሞሪም ከዴቪድ ሞየስ ቀጥሎ ሁለተኛው ለጥቂት ጊዜ የቆዩ የዩናይትድ አሠልጣኝ ሆነዋል።

የዩናይትድ ከ18 ዓመት በታች ቡድን አሠልጣኝ የሆነው ዳረን ፍሌቸር የፕሪሚዬር ሊግ ክለብ ለማሠልጠን ሲመጣ ይህ የመጀመሪያው ነው።

የ41 ዓመቱ ስኮትላንዳዊ ከአውሮፓወያኑ 2005 እስከ 2015 ለዩናይትድ የተጫወተ ሲሆን፣ አምስት ጊዜ የእንግሊዝ ፕሪሚየር ሊግ አንድ ጊዜ የአውሮፓ ቻምፒዮንስ ሊግ ዋንጫ ማንሳት ችሏል።