የወልቃይት ጠገዴ ኮሚቴ በምርጫ ቦርድ እና በስምረት ፓርቲ የፍርድ ቤት ክርክር ውስጥ ለመግባት ጠየቀ

የንባብ ጊዜ: 3 ደቂቃ

የወልቃይት ጠገዴ አማራ የማንነት እና ወሰን አስመላሽ ኮሚቴ፤ የፌደራል ከፍተኛ ፍርድ ቤት በአከራካሪ የምርጫ ክልሎች ላይ ምርጫ እንዲያካሄድ ባሳለፈው ጊዜያዊ ዕግድ ውስጥ ገብቶ ለመከራከር አቤቱታ አቀረበ።

ኮሚቴው በፌደራል ከፍተኛ ፍርድ ቤት በአመልካች በዲሞክራሲያዊ ስምረት ትግራይ ፓርቲ እና በኢትዮጵያ ምርጫ ቦርድ መካከል በፍርድ ቤት እየታየ ያለው ጉዳይ መብት እና ጥቅሙን እንደሚነካ በመግለጽ ጣልቃ ገብቶ ለመከራከር በጠበቃ በኩል ጥያቄ ማቅረቡን አስታውቋል።

በዚህም መሠረት ፍርድ ቤቱ ጉዳዮን ተመልክቶ ውሳኔ ለመስጠት ለየካቲት 25/2018 ዓ. ም. ቀጠሮ መስጠቱን ለጉዳዩ ቅርበት ያላቸው ምንጭ ለቢቢሲ አረጋግጠዋል።

ምርጫ ቦርድ በሁለቱ ክልሎች መካከል አወዛጋቢ በሆኑ አምስት የምርጫ ክልሎች ከትግራይ እና ከአማራ ክልል ውጭ ሆነው በቀጥታ የተወካዮች ምክር ቤት ዕጩዎች ምርጫ እንዲካሄድባቸው ውሳኔ ያስተላለፈው ሰኞ የካቲት 16/2018 ዓ. ም. ነበር።

ይህንንም ተከትሎ በአቶ ጌታቸው ረዳ የሚመራው ዴሞክራሲያዊ ስምረት ትግራይ (ስምረት) ፓርቲ ባቀረበው አቤቱታ የፌደራል ከፍተኛ ፍርድ ቤት ሐሙስ የካቲት 19/2018 ዓ. ም. በውሳኔው ላይ ዕግድ ጥሏል።

ይህንንም ተከትሎ የወልቃይት ጠገዴ የአማራ ማንነት እና ወሰን አስመላሽ ኮሚቴ በውሳኔው "ለሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት የመምረጥ እና የመመረጥ መብት ከተሰጣቸው የምርጫ ክልሎች ውስጥ የሁመራ እና የአድ ረመፅ ምርጫ ክልሎች" ከትግራይ ክልል ወጥቶ በወልቃይት ጠገዴ ሰቲት ዞን ሥር ራሱን የሚያስተዳድር ነው ብሏል።

ኮሚቴው ስምረት ባቀረበው አቤቱታ መሠረት አመልካቾች ፍርድ ቤቱ በሰጠው "ዕግድ በክርክሩ ሂደት ውስጥ ተካፋይ ባልሆንበት ሁኔታ የሚሰጠው ውሳኔ በኢ.ፌ.ዴ.ሪ ሕገ መንግሥት አንቀፅ 38 ላይ የተመለከተውን የመምረጥና መመረጥ መብት እና ጥቅማችንን የሚነካ ነው" ብሏል።

በዚህም ምክንያት ፍርድ ቤት በስምረት ፓርቲ እና በብሔራዊ ምርጫ ቦርድ መካከል በሚደረገው ክርክር ውስጥ ጣልቃ ገብተው እንዲከራከሩ እንዲፈቀድላቸው ጠይቀዋል።

የፌዴሬሽን ምክር ቤት በአማራ እና በትግራይ ክልሎች መካከል አከራካሪ በሆኑ ቦታዎች "ከትግራይ ክልላዊ መንግሥት ውጪ ሆነው ለብቻቸው" በቀጥታ ለሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ምርጫ እንዲደረግ መወሰኑን የኢትዮጵያ ብሔራዊ ምርጫ ቦርድ ማሳወቁን ተከትሎ ነው ጉዳዩ ወደ ፍርድ ቤት ያመራው።

ቦርዱ እንዳለው ያወጣውን የምርጫ ክልሎችና ጣቢያዎች ዝርዝር ተከትሎ የፌዴሬሽን ምክር ቤት ጥር 25/2018 ዓ. ም. ለቦርዱ በጻፈው ደብዳቤ በሁለቱ ክልሎች መካከል አከራካሪ ሆነው የቆዩ አምስት የምርጫ ክልሎች ጉዳይ እስኪፈታ ለብቻቸው ምርጫ እንዲደረግ መወሰኑን አስታውቋል።

እነዚህ በትግራይ እና በአማራ ክልል የይገባኛል ጥያቄ የተነሳባቸው እና ከሁለቱም ክልሎች ውጭ ሆነው በራሳቸው ምርጫ እንዲደረግባቸው የተወሰኑት የሁመራ፣ የአዲ ረመፅ፣ የኮረም አፍላ፣ የጠለምት እና የራያ አላማጣ ምርጫ ክልሎች ናቸው።

በእነዚህ አምስት የምርጫ ክልሎች የሚገኙ መራጮች ድምጻቸውን የሚሰጡት ለሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ዕጩዎች ሲሆን፣ የክልል ምክር ቤት ምርጫው በአካባቢዎቹ ላይ የተነሳው የይገባኛል ውዝግብ በሕገ መንግሥት ውሳኔ ከተፈታ በኋላ እንደሚካሄድ የፌዴሬሽን ምክር ቤት ማሳወቁን ቦርዱ ገልጿል።

ይህንንም ተከትሎ በአቶ ጌታቸው ረዳ የሚመራው ዴሞክራሲያዊ ስምረት ትግራይ (ስምረት) ፓርቲ ባቀረበው አቤቱታ የፌደራል ከፍተኛ ፍርድ ቤት በውሳኔው ላይ ዕግድ ጥሏል።

በትግራይ የሚንቀሳቀሰው ስምረት ፓርቲ የፌዴሬሽን ምክር ቤት ውሳኔን ብሔራዊ ምርጫ ቦርድ ይፋ ሲያደርግ በይፋ ተቃውሞውን በመግለጫ ያሳወቀ ሲሆን፣ ጉዳዩንም በፕሬዝዳንቱ አቶ ጌታቸው በኩል ለፍርድ ቤት አቅርቧል።

የጠቅላይ ሚኒስትሩ የምሥራቅ አፍሪካ ጉዳዮች አማካሪ የሆኑት የቀድሞው የትግራይ ክልል ጊዜያዊ አስተዳደር ፕሬዝዳንት አቶ ጌታቸው በማኅበራዊ ገጻቸው ላይ ባጋሩት በዚህ ውሳኔ ምርጫ ቦርድ መልሱን የካቲት 25/2018 ዓ. ም. እንዲያቀርብ ፍርድ ቤት አዝዟል።

የኢትዮጵያ ብሔራዊ ምርጫ ቦርድ በአማራ እና ትግራይ ክልሎች መካካል አከራካሪ ሆነው የቆዩ የተባሉትን አምስት የምርጫ ክልሎች በተመለከተ ከፌዴሬሽን ምክር ቤት ደርሶኛል ያለውን ውሳኔ ይፋ ካደረገ በኋላ የሁለቱ ክልሎች ፖለቲከኞች ድጋፍ እና ተቃውሟቸውን ግልጸዋል።

የትግራይ ክልል ጊዜያዊ አስተዳደር፣ ህዝባዊ ወያነ ሓርነት ትግራይ (ህወሓት)፣ ዲሞክራሲያዊ ስምረት ትግራይ (ስምረት) እና ሌሎችም በትግራይ የሚንቀሳቀሱ ፓርቲዎች ውሳኔውን ሲቃወሙ፤ በአማራ ክልል በኩል ያሉ የፖለቲካ ፓርቲዎች የተላለፈውን ውሳኔ ደግፈውታል።

በዛሬው ዕለትም በትግራይ ጊዜያዊ አስተዳደር ጥሪ በተለያዩ የክልሉ አካባቢዎች ነዋሪዎች አደባባይ ወጥተው የተቃውሞ ሰልፍ ማድረጋቸውን የክልሉ መገናኛ ብዙኃን ዘግበዋል።