ይህ ዝቅተኛ ዳታን በመጠቀም ጽሑፍ ብቻ የሚቀርብበት የቢቢሲ አማርኛ ድረ ገጽ ነው
የአገሩ ወጣቶች ከሩሲያ ጎን ሆነው ዩክሬንን እንዲወጉ ሲያባብል ነበር የተባለ ኬንያዊ ክስ ተመሰረተበት
የኬንያ ፖሊስ ወጣቶችን በሥራ ዕድል ሽፋን ወደ ሩሲያ እንዲሄዱ በማግባባት በዩክሬን ጦርነት እንዲሳተፉ እያደረገ ነበር የተባለ ግለሰብ ላይ ክስ መሰረተ።
የግሎባል ፌስ ሂውማን ሪሶርስ የቅጥር ኃላፊ ሆነው ፌስተስ አራሳ ኦምዋምባ 22 ኬንያውያንን "በማጭበርበር ለብዝበዛ አውሏል" ሲል አቃቤ ሕግ ሐሙስ ዕለት አስታውቋል።
ተጎጂዎቹ ባለፈው መስከረም ወር በዋና ከተማዋ ናይሮቢ አቅራቢያ በምትገኘው አቲ ሪቨር ከሚገኝ አፓርትመንት ውስጥ እያሉ ወደ ሩሲያ ከመጓዛቸው በፊት ተይዘዋል።
ይሁን እንጂ ሌሎች ሦስት ግለሰቦች ከኬንያ ወጥተው ስለነበር በጦር ግንባር ላይ ጉዳት አስተናግደው ወደ አገራቸው መመለሳቸውን አቃቤ ሕግ አክሏል። የ33 ዓመቱ ኦምዋምባ የተመሰረተበትን ክስ ጥፋተኛ አይደለሁም ሲል አስተባብሏል።
ባለፈው ሳምንት የኬንያ ብሔራዊ የስለላ አገልግሎት (ኤንአይኤስ) ሪፖርት እንዳመለከተው በድምሩ አንድ ሺህ ኬንያውያን ከተጀመረ አራት ዓመታትን ባስቆጠረው የዩክሬን ጦርነት ከሩሲያ ጎን ሆነው ለመዋጋት ተመልምለዋል።
ሪፖርቱን ለፓርላማ አባላት ያቀረቡት የፓርላማ አብላጫ መሪ ኪማኒ ኢሽንጉዋህ እንዳሉት ኬንያውያንን ለመመልመል እና ለማጓጓዝ ሰው አዘዋዋሪዎች እና ባለሥልጠናት "በጣም በሚረብሸው" የወንጀል መረብ ውስጥ ተሳትፈዋል።
ኦምዋምባ በዚህ ወር መጀመሪያ ላይ ለፖሊስ እጁን የሰጠው በኢትዮጵያ ድንበር አቅራቢያ ባለች ከተማ ነው።
ባለፈው መስከረም ወር ከአቲ ሪቨርስ የተያዙት ተጎጂዎች ስሙ ካልተጠቀሰ የውጭ አገር የሥራ አገናኝ ኤጀንሲ ጋር ውል መፈራረማቸውን ፖሊስ አስታውቋል። ለቪዛ፣ ለጉዞ፣ ለማረፊያ እና ለሌሎች ሎጂስቲክስ እስከ 18 ሺህ ዶላር ለመክፈል ቃል ገብተዋል ሲል ሲል አክሏል።
የብሔራዊ የስለላ አገልግሎት እንደገለጸው ከሆነ በርካታ ኬንያውያን አነስተኛ ወታደራዊ ሥልጠና ካገኙ በኋላ ወደ ግንባር ይሰማራሉ።
በዚህ ወር መጀመሪያ ላይ የኬንያ መንግስት ሩሲያ በዩክሬን እንዲዋጉ ኬንያውያንን መመልመልን እንድታግድ እንደሚያሳስብ ተናግሯል።
በናይሮቢ የሚገኘው የሩሲያ ኤምባሲ በበኩሉ ኬንያውያን በዩክሬን እንዲዋጉ ማበረታታትን ወይም "በዩክሬን ልዩ ወታደራዊ ኦፕሬሽን ውስጥ ለመሳተፍ ወደ ሩሲያ ለመጓዝ ለሚፈልጉ የኬንያ ዜጎች ቪዛ ሰጥቷል" መባሉን ውድቅ አድርጓል።
ኤምባሲው የውጭ ዜጎችን ባይመዘግብም፣ የሩሲያ ሕግ በሩሲያ ውስጥ በሕጋዊ መንገድ የሚገኙ የውጭ ዜጎች በፈቃደኝነት በጦር ኃይሉ ውስጥ እንዲመዘገቡ እንደሚፈቅድ ገልጿል።
የዩክሬን የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ረቡዕ ዕለት እንዳስታወቀው ከሆነ ከ36 የአፍሪካ አገሮች የተውጣጡ ከአንድ ሺህ 700 በላይ ሰዎች ለሩሲያ ለመዋጋት ተመልምለዋል።
ደቡብ አፍሪካ ሐሙስ ዕለት ሁለት ዜጎቿ በዩክሬን እንደተገደሉ እና ሌሎች 15 ደግሞ ባለፈው ሳምንት ወደ አገራቸው እንደተመለሱ አስታውቃለች። ሁለቱ ደግሞ ሩሲያ ውስጥ "በጣም ከባድ" ጉዳት በማስተናገዳቸው ህክምና እያገኙ መሆኑን የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ሮናልድ ላሞላ ተናግረዋል።
የዩክሬን ባለሥልጣናት ለሩሲያ የሚዋጋ ማንኛውም ሰው እንደ ጠላት እንደሚቆጠር እና ብቸኛው መውጫ መንገድ እጅ መስጠት እና እንደ ጦርነት ምርኮኛ መታየት መሆኑን ደጋግመው አስጠንቅቀዋል።
ይሁን እንጂ ዩክሬንም አፍሪካውያንን ጨምሮ የውጭ ዜጎችን ከጎኗ ሆነው እንዲዋጉ ለመመልመል በመሞከሯ ቀደም ሲል ትችት ተሰንዝሮባታል።