ዴንማርክ ለመጀመሪያ ጊዜ ሴቶችን ለወታደራዊ ግዳጅ መመዝገብ ጀመረች

የፎቶው ባለመብት, Getty Images
ዴንማርክ ለመጀመሪያ ጊዜ ሴቶችን ለብሔራዊ ውትድርና መመልመል መጀመሯን ገለጸች።
አውሮፓዊቷ ሀገር ከዚህ አልፎ ቀድሞ የነበረውን ብሔራዊ ውትድርና አገልግሎት ጊዜን ማራዘሟን አስታውቃለች።
ዴንማርክ በሚቀጥሉት አምስት ዓመታት የመከላከያ በጀቷን 6 ቢሊዮን ዶላር በማድረስ የኔቶን ግብ ለመምታት ማቀዷንም ይፋ አድርጋለች።
“ይህን የምናደርገው ጦርነት ፈልገን አይደለም። ይህን የምናደርገው ጦርነትን ማስወገድ ስለምንፈልግ ነው” ብለዋል ጠቅላይ ሚኒስትር ሜቴር ፍሬድሪክሰን።
ሩሲያ ከሁለት ዓመት በፊት ዩክሬንን መውረሯን ተከትሎ በአውሮፓ ያለው ውጥረት ከሯል።
የዴንማርክን ዕቅድ ረቡዕ ይፋ ያደረጉት ጠቅላይ ሚኒስትሩ፤ መንግሥታቸው “በፆታዎች መካከል እኩልነት” እንዲሰፍን እንደሚሠራ ገልጸዋል።
በሌላ በኩል የመከላከያ ሚኒስትሩ ትሮልስ ለንድ ፖልሰን “የፆታ እኩልነት የሚታይበት ሁሉን አካታች የሆነ ምልመላ በመከላከያ በኩል ያለንን ክፍተት ይሞላል፤ ብሔራዊ ንቅናቄውን ያጠናክራል፤ መከላከያ ሠራዊታችንም ይደረጃል” ብለዋል።
በስካንዴኔቪያዋ ሀገር ሴቶች ከዚህ ቀደም በፈቃደኝነት ለወታደራዊ አገልግሎት መመዝገብ ይችሉ ነበር።
ነገር ግን አሁን በአውሮፓውያኑ ከ2026 ጀምሮ ሴቶች ለብሔራዊ አገልግሎት መመዝገብ ግዴታቸው ይሆናል። ዴንማርክ ከኖርዌይ እና ስዊድን ቀጥሎ ሴቶች ወታደራዊ ግዴታቸውን እንዲወጡ በማድረግ ሶስተኛዋ አውሮፓዊት ሀገር ትሆናለች።
ሌላው የዴንማርክ ዕቅድ የወታደራዊ ግዴታውን ጊዜ ከአራት ወራት ወደ 11 ማሳደግ ነው። ሴቶችም ሆኑ ወንዶች ለወታደራዊ ግዳጅ ከተመዘገቡ ለ11 ወራት የማገልገል ግዴታ ይኖርባቸዋል ማለት ነው።
ባለፈው ዓመት 4700 ሰዎች ለብሔራዊ አገልግሎት የተመዘገቡ ሲሆን 25 በመቶው ሴቶች ናቸው። ይህ ቁጥር በዓመት ወደ 5 ሺህ ያድጋል ተብሎ ይጠበቃል።
የዴንማርክ የመከላከያ ሠራዊት ቁጥር አሁን 20 ሺህ ገደማ ሲሆን 9 ሺህ አካባቢው ሙሉ ሥልጠና ያላቸው ወታደሮች ናቸው።
የሕዝብ ቁጥሯ 6 ሚሊዮን የሚገመተው ዴንማርክ ከጠቅላላ ሀገራዊ ምርቷ 1.4 በመቶውን ለወታደራዊ አቅሟ ታውላለች።
ዴንማርክ ይህን ቁጥር ወደ 2 በመቶ በማሳደግ የሰሜን አትላንቲንክ ጦር ቃል ኪዳን [ኔቶ] ግብን ለማሳካት አቅዳለች።
ባለፈው ዓመት የሀገሪቱ ሕግ አውጭዎች አንድ የሕዝብ በዓል የሚከበርበት ቀን በማስወገድ ለበዓሉ የሚወጣውን ወጭ ወደ መከላከያ ሠራዊቱ አዛውረዋል።
ዴንማርክ ያለመታከት ለዩክሬን የጦር መሣሪያ እና የገንዘብ ድጋፍ ከሚያደርጉ ሀገራት መካከል ናት።
አልፎም አሜሪካ ሠራሽ ኤፍ-16 የጦር ጄት አብራሪዎችን በማሰልጠን ለዩክሬን ድጋፏን ገልጻለች።
ፊንላንድ እና ስዊድን በቅርቡ ኔቶን ተቀላቅለዋል። ሩሲያ ዩክሬንን መውረሯን ተከትሎ የጦር ቃል ኪዳኑ አባላቱን እያሰፋ ይገኛል።












