ኢላን መስክና ማርክ ዛከርበርግ በፍርግርግ አጥር ተከበው ቡጢ ለመግጠም ተስማሙ
![ኢላን መስክ [ግራ] እና ማርክ ዛከርበርግ](https://ichef.bbci.co.uk/ace/ws/640/cpsprodpb/1fba/live/c2be3a40-10d1-11ee-816c-eb33efffe2a0.jpg.webp)
የፎቶው ባለመብት, Reuters and Getty Images
ሁለቱ ጉምቱ የዓለማችን የቴክኖሎጂ አውራዎች መስክና ዛከርበርግ ቡጢ ለመግጠም ተስማሙ።
ከገጠምን አይቀር ከልካይ በሌለበት በፍርግርግ በታጠረ መድረክ ይሁን ያሉት ቢሊየነሮቹ በቡጢ ሊዋጣላቸው ነው።
መስክ ነው ከአንድ የትዊተር መልዕክት በታች “ቡጢ እንግጠም ይሆን” ሲል ለዛከበርግ ጥያቄ ያቀረበው።
የፌስቡክና ኢንስታግራም ባለቤት የሆነው ሜታ አለቃ ማርክር ዛከርበርግ “አድራሻውን ላክልኝ” ሲል ምላሽ ሰጥቷል።
የሜታ ቃል አቀባይ ለቢቢሲ እንዲህ ብለዋል “ያው ምንም የተደበቀ ነገር የለም።”
ዛከርበርግ አድራሻህን ላክልኝና መጥቼ ልግጠምህ የሚል መልዕክት ከሰደደ በኋላ ኢላን መስክ “ቬጋስ ኦክታገን” እንገናኛለን ብሏል።
ቬጋስ የሚገኘው ኦክታገን ተቧቃሾች ከአንድ ዳኛ በቀር ያለማንም ከልካይ የሚናረቱበት በሽቦ የታጠረ መድረክ ነው።
በተለይ ደግሞ ዓይናቸውን እስኪያብጥ፣ ድዳቸው እስኪገጥ የሚፋለሙት ዩኤፍሲ የተሰኘው ስፖርት እዚያ ይዘወተራል።
ለዚያም ይመስላል ዩኤፍሲ ዋና መሥሪያ ቤቱን ላስ ቬጋስ ኔቫዳ የገነባው።
በያዝነው ወር መገባደጃ 52 የሚሞላው ኢላን መስክ የቡጢ ምስጢሩን ለመላው የትዊተር ሕዝብ አጋርቷል።
“አንድ መላ አለኝ። ‘ዘ ዋልረስ’ ስል እጠራዋለሁ። መላ ሰውነቴን ተቀናቃኜ ላይ ወርውሬ መቀመጥ ነው።”
መስክ ቀጥሎ እንዲህ አለ። “እርግጥ ነው የአካል ብቃት እንቅስቃሴ አላደርግም። ልጆቼን አፍሼ እንደ ቅርጫት ኳስ ወደሰማይ ሰዶ ከመቅለብ በቀር።”
የ39 ዓመቱ ማርክ ዛከርበርግ ደግሞ ሚክስድ ማርሻል አርትስ የሚሉት ትምህርት ወስዷል።
ኧረ እንደውም በቅርቡ በአንድ የጁ-ጂትሱ ውድድር ተሳትፎ ተቀናቃኙን በጫማ ጥፊ በመዘረር ሜዳሊያ ተጎናፅፏል።
ትዊተር ከቢቢሲ ጥያቄ ቢቀርብለትም እስካሁን ምላሽ ሊሰጥ አልሻተም።
ሁለቱ ቱጃሮች ለቡጢ ቀጠሮ ከያዙ በኋላ የማሕበራዊ ሚድያ ተጠቃሚዎች ማን ይረታል ወደሚል የሞቀ ክርክር ገብተዋል።
ሜታ በቅርቡ ትዊተርን የመሰል ማሕበራዊ ሚድያ ለማስተዋወቅ ማቀዱን ውስጥ አዋቂዎች ለቢቢሲ ገልጠዋል።
ተጠቃሚዎች ኢንስታግራም ላይ የሚከተሏቸውን ሰዎች በቀላሉ በአዲሱ ድር ላይም መተከል ይችላሉ።
ይህን ዜና አንድ ተጠቃሚ ትዊተር ላይ ሲለጥፈው ነው ኢላን መስክ ተቧቅሰን ይውጣልን የሚል አስተያየት የሰጠው።












