ከጎርፍ ሲሸሹ የነበሩ ናይጄሪያዊንን የያዘች ጀልባ ከሰመጠች በኋላ 76 ሰዎች ሞቱ

የፎቶው ባለመብት, Reuters
በናይጄሪያ ደቡብ ምሥራቅ በምትገኘው የአናምብራ ግዛት በደረሰ የጀልባ መስመጥ አደጋ ቢያንስ 76 ሰዎች መሞታቸው ተዘገበ።
ቢያንስ 80 ሰዎችን አሳፍራ ስትጓዝ የነበረችው ጀልባ አርብ ዕለት በአናምብራ ግዛት ኦግባሩ አካባቢ ስትደርስ ሰምጣለች።
አብዛኛዎቹ ሟቾቹ ሴቶች እና ህጻናት ሲሆኑ አካባቢያቸው በጎርፍ በመጥለቅለቁ ከአካባቢው ሲወጡ አደጋው እንደገጠማቸው ተነግሯል።
ፕሬዝዳንት ሙሐመዱ ቡሃሪ "በአሳዛኙ" አደጋ ለተጎጂዎች ቤተሰቦች መጽናናትን ተመኝተዋል።
በተጨማሪም የሃገሪቱ የውሃ ትራንስፖርት ስርዓት የደህንነት እርምጃዎች እንዲከለሱ አዘዋል። የአደጋ ጊዜ ሠራተኞች የጠፉትን ለማግኘት ሁሉንም ነገር ማድረግ አለባቸውም ብለዋል።
ቡሃሪ አክለውም የመንግሥት ተቋማት "በእነዚህ የመጓጓዣ ጀልባዎች ላይ የደኅንነት ፕሮቶኮሎችን እንዲፈትሹና ተመሳሳይ አደጋዎች እንዳይከሰቱ እንዲከላከሉ" ጠይቀዋል።
የአገሪቱ መገናኛ ብዙሃን እንደዘገቡት በጀልባው ላይ የተሳፈሩት ሰዎች በአከባቢው ወደሚገኘው ንኮዎ ገበያ በማምራት ላይ ነበሩ። ባለስልጣናት ጀልባዋ የሞተር ችግር ካጋጠማት በኋላ ድልድይ ገጭታ ሰምጣለች ብለዋል።
በብሔራዊ ድንገተኛ አደጋ አስተዳደር ኤጀንሲ የደቡብ ምስራቅ አስተባባሪ የሆኑት ቲክማን ታኒሙ ለኤኤፍፒ የዜና ወኪል እንደተናገሩት "የውሃው መጠን በጣም ከፍተኛ በመሆኑ ለፍለጋ እና ለማዳን ሥራው በጣም አደገኛ ነው" ብለዋል።
የአናምብራ ገዥ ቻርለስ ሶሉዶ በበኩላቸው አደጋው ነዋሪውንም ሆነ የግዛቱን መንግስትም ያስደነገጠ መሆኑን ጠቅሰው ለተጎጂ ቤተሰቦችም ሃዘናቸውን ገልጸዋል።
በናይጄሪያ የጀልባ አደጋዎች የተለመዱ ናቸው። ለአብዛኛዎቹም ከልክ በላይ መጫን ወይም ዝቅተኛ የደህንነት እርምጃዎች በምክንያትነት ይቀርባሉ።












