መድፈኞቹ በሊቨርፑል ላይ ጠንካራ ክንዳቸውን ሲያሳርፉ ሮናልዶ አዲስ ታሪክ ጻፈ

የፎቶው ባለመብት, Getty Images
ሊቨርፑልን በኢሚሬትስ ስታዲያም ያስተናገዱት መድፈኞቹ ውጥረት በበዛበት ጨዋታ 3 ለ 2 አሸንፈዋል።
አርሰናል በሊቨርፑል ላይ ያስመዘገቡት ድል የመጣው በሰሜን ለንደን ባላንጣቸውን ቶተነሃምን ካሸነፉ ከአንድ ሳምንት በኋላ ነው።
ይህ በእንዲህ እንዳለ የማንቸስተር ዩናይትድ የፊት መስመር ተጫዋች ክርስቲያኖ ሮናልዶ አዲስ ታሪክ አስመዝግቧል።
ፖርቹጋላዊው ሲአር7 ቡድኑ ማንቸስተር ዩናይትድ ከኤቨርተን ጋር በነበረው ጨዋታ ያስቆጠራት ጎል በክለብ ደረጃ ኳስን ከመረብ ሲያገናኝ 700ኛው ሆና ተመዝግባለቸው። ይህም አዲስ ክብረ ወሰን ሆኖ ተመዝግቦለታል።

የፎቶው ባለመብት, Getty Images
የመድፈኞቹ ጠንካራ ክንድ
የቢቢሲው እግር ኳስ ተንታኝ ፊል ማነልቲ መድፈኞቹ ትናንት ምሽት በሊቨርፑል ላይ ጠንካራ ክንዳቸውን አሳርፈዋል ይላል።
የውድድር ዘመኑን በጥሩ አቋም ቢጀምሩም እስካሁን ባካሄዷቸው ጨዋታዎች በጠንካራ ቡድን አልተፈተሹም ሲባሉ ለነበሩት መድፈኞቹ፤ በአንድ ሳምንት ልዩነት በቶተነሃም እና በሊቨርፑል ላይ የበላይነትን ይዘው ማሸነፋቸው ሚኬል አርቴታ በክለቡ ለውጥ አምጥቷል አስብሏል።
ባለፈው ሳምንት በነበረው የሰሜን ለንደን ደርቢ አርሰናል በጨዋታ እና በጎል ብልጫ ይዞ ‘ሰሜን ለንደን ቀይ’ መሆኑን አስመስክሮ ነበር።
ትናንት በነበረው ግጥሚያም የጨዋታው ኮከብ ሆኖ ያመሸው ገብርኤል ማርቲኔሊ ገና በመጀመሪያ ደቂቃው በጉዳት ተቀይሮ የውጣውን ትሬንት አልክሳንደር-አርቦልድን በማለፍ ለመድፈኞቹ የመጀመሪያ ጎል አስቆጥሯል።
አርሰናል እና ሊቨርፑል ባደረጓቿው ባለፉት ጨዋታዎች የበላይነትን ይዘው ያጠናቅቁ የነበሩት ሊቨርፑሎች ትናንት ምሽት ሁለት ግዜ በአርሰናል ቢመሩም በዳርዊን ኑኔዝ እና ፈርሚኒዮ ባስቆጠሯቿው ጎሎች አቻ መሆን ችለው ነበር።
ይሁን እንጂ መድፈኞቹ ብዙ አጨቃጫቂ የሆኑ ፍጹም ቅጣት ምት ካገኙ በኋላ ወጣቱ ቡካዮ ሳካ ፍጹም በተረጋጋ ስሜት የሊቨርፑሉን ግብ ጠባቂ አሊሰንን በመርታት ጎልን ከመረብ አገናኝቷል።
የቢቢሲው የእግር ኳስ ተንታኝ ፊል ውጥረት በበዛበት ምሽት አርሰናል እራሳቸውን አደራጅተው የውድድር ዘመኑ ትልቁ ድላቸውን አስመዝግበዋል ይላል።

የፎቶው ባለመብት, Getty Images
በክለብ ደረጃ 700 ጎሎች
ከወራት በኋላ 38ኛ ዓመቱን የሚደፍነው ፑርቹጋላዊ አሁንም በትልቅ ሊጎች ጎልን ከመረብ ማገናኘት ከባድ የሆነበት አይመስልም።
ሮናልዶ ትናንት ዩናይትድ በጉደሲን ፓርክ ከኤቨርተን ሲገናኝ ከተቀያሪ ወንበር ተነስቶ ማሸነፊያ ጎል አስቆጥሯል።
ይህም ሲአር7 በክለብ ደረጃ ያሰቆጠራቸውን ጎሎች ብዛት 700 አድርሶለታል።
ሮናልዶ በሪያል ማድሪድ መለያ 450፣ ለማንችስተር ዩናይትድ 144፣ ለጁቬንቱስ 101 እና ለቀደመ ክለቡ ስፖርቲንግ ሊዝበን 5 ጎሎችን አስቆጥሯል።












