ፑቲን፣ በክራይሚያ ድልድይ ላይ የደረሰው ‘የሽብር ጥቃት’ ነው አሉ

የፎቶው ባለመብት, EPA
የሩሲያው ፕሬዝዳንት ቭላድሚር ፑቲን ዩክሬን በክራይሚያ ድልድይ ላይ የሽብር ጥቃት አድርሳለች ሲሉ ከሰሱ።
ፑቲን የዩክሬን የደኅንነት ኃይል በሩሲያ መሠረተ ልማቶች ላይ የሽብር ጥቃት ዓላማ ይዞ እንደተነሳም አስገንዝበዋል።
ፑቲን ጥቃቱ የሽብር ጥቃት ነው ያሉት አደጋውን የሚመረምር ኮሚቴ ተጠሪ የሆኑትን አሌክሳንደር ባስትሪክን ባነጋገሩበት ወቅት ነው።
ባለሥልጣናት ድልድዩ ላይ በደረሰው ጥቃት ሦስት ሰዎች መሞታቸውን አስታውቀዋል።
ሟቾቹ ድልድዩ ሲጋይ በቅርብ ርቀት በተሽከርካሪ እያለፉ ነበር ተብሏል።
“በዚህ ጥርጥር አይግባችሁ፤ ይህ የሩሲያን ሁነኛ መሠረተ ልማቶች ለማውደም የተቃጣ የሽብር እርምጃ ነው" ብለዋል ፑቲን።
አክለውም፣ የዚህ ጥቃት ጠንሳሾቹ፣ ፈጻሚዎቹና አትራፊዎቹ ሁሉም የዩክሬን የደኅንነት መሥሪያ ቤት አገልግሎት ሰዎች ናቸው ብለዋል።
የመርማሪ ኮሚቴው ተጠሪ አሌክሳንደር ባስትሪኪን በበኩላቸው የውጭ ኃይሎች ይህ ጥቃት እንዲፈጸም ድጋፍ ሰጥተዋል።
እንደ እርሳቸው ማብራሪያ ከሆነ ጥቃቱን ያደረሰው ከባድ ተሽከርካሪ ከቡልጋሪያ ተነስቶ በጆርጂያ፣ አርሜኒያ፣ ኖርዝ ኦሴሺያ እና ክራስኖዳር ግዛቶች አልፎ ነው የመጣው።
የዩክሬን ኃይሎች ይህን ጥቃት ስለመፈጸማቸው ያሉት ነገር የለም።
የፕሬዝዳንት ቮሎድሚር ዘለንስኪ አማካሪ ሚካይሎ ፖዶሊያክ የፑቲንን ክስ አጣጥለውታል።
“ፑቲን ዩክሬንን በሽብር ከሰሱ? ይህ ለሩሲያ ራሱ የማይመስል ነገር ነው።" ብለዋል የዘለንስኪ ረዳት።
ረዳታቸው ይህን ይበሉ እንጂ ቅዳሜ ዕለት ፕሬዝዳንት ዘለነስኪ በዕለታዊው ጋዜጣዊ መግለጫቸው እንዲህ ብለው ነበር፦
“ዛሬ መጥፎ ቀን አልነበረም። እንዲያውም ቀኑ በኛ ግዛቶች ፀሐያማ ነበር። በክራይሚያ ግን ደመናማ ይመስላል።"
ሩሲያ በኃይል ከያዘችው የክራይሚያ ግዛት የሚያገናኛት ረዥሙ ድልድይ አሁን ለትራፊክ ክፍት ተደርጓል።
ይሁንና የሚያልፉት ተሽከርካሪዎች አነስተኛ ጭነት ያላቸው ብቻ ናቸው።
የድልድዩ አካል የሆነው የባቡር ሐዲድ መስመርም ለትራፊክ ክፍት ተደርጓል።
ይህ ሩሲያን ከክራይሚያ የሚያገናኘው ድልድይ 19 ኪሎ ሜትሮች ይረዝማል። በርዝመቱም በአውሮፓ ተስተካካይ የለውም።
በተለይ ለሩሲያ ወታደሮች ስንቅና ትጥቅ የሚተላለፍበት ድልድይ በመሆኑ ጠቀሜታው እጅግ የጎላ ነው።
የክራይሚያ ድልድይ በፈረንጆቹ 2018 በፑቲን ፊታውራሪነት ተገንብቶ የተመረቀ ነው።
ይህም የሆነው ሩሲያ ክራይሚያን በኃይል ከያዘች ከአራት ዓመት በኋላ ነበር።












