ከባድ ፍንዳታ ያጋጠመው የክሬሚያ ድልድይ በከፊል ተከፍቷል - ሩሲያ

ከሩሲያ ወደ ክሬሚያ የሚወስደው ድልድይ

የፎቶው ባለመብት, Reuters

በከባድ ፍንዳታ የወደመው እና ከሩሲያ ወደ ክሬሚያ የሚወስደው ብቸኛ ድልድይ ከሰዓታት በኋላ አነስተኛ ቁጥር ያላቸው መኪኖችን ማስተናገድ ቀጥሏል።

በአውሮፓ ረዥሙ ድልድይ ላይ በደረሰው ፍንዳታ የሦስት ሰዎች ህይወት ማለፉን መርማሪዎች ተናግረዋል። ድልድዩ እአአ በ 2014 ሩሲያ ከዩክሬን ባሕረ ገብ መሬቱን የመውሰዷን ምልክት ተደርጎ ይታያል።

ተጎጂዎቹ በአቅራቢያው ባለ መኪና ውስጥ እያሉ ሌላ መኪና መፈንዳቱን የሩሲያ ባለስልጣናት የተናገሩት።

የነዳጅ ታንከሮች የተቃጠሉበት የድልድዩ የባቡር ሐዲድ ክፍልም እንደ ገና ተከፍቷል።

የሩስያ የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ቅዳሜ ምሽት ላይ ባሰራጨው ቪዲዮ መኪኖች ድልድዩን ሲጠቀሙ አሳይቷል።

በ2018 የተከፈተው ድልድይ እና የባቡር ሃዲድ ሩሲያ ለዩክሬን ጦርነት የምትጠቀምበትን ሎጂስቲክ የምታገኝበት ቁልፍ መስመር ነው። 

የዩክሬን ፕሬዝዳንት ቮሎዲሚር ዜለንስኪ አማካሪ ማይካሂሎ ፖዶሊያክ የዩክሬን ኃላፊነት በቀጥታ ባይቀበሉም “ክሪሚያ፣ ድልድይ፣ መጀመሪያው” የሚሉ ቃላትን አስፍረዋል።

"ህገ ወጥ ነገር ሁሉ መወገድ አለበት። የተሰረቀው ነገር ሁሉ ወደ ዩክሬን መመለስ አለበት። በሩሲያ የተያዘው ነገር ሁሉ መባረር አለበት" ብለዋል።

የዩክሬን መከላከያ ሚኒስቴር የድልድዩን ፍንዳታ በሚያዝያ ወር ከሰጠመችው የሩስያዋ ሞስኮቫ የሚሳኤል መርከብ ጋር አነጻጽረዋታል።

"በዩክሬን ክሬሚያ ውስጥ የነበሩ ሁለት ታዋቂ የሩሲያ የታላቅነት ምልክቶች ወድመዋል። በቀጣይስ ምን አለ?" ሲሉ በትዊተር ገጻቸው ላይ አስፍረዋል። 

የዩክሬን መንግስት በትዊተር ገጹ “ተቃጥሏል” ብሎ አስፍሯል።

በፕሬዚዳንት ፑቲን የተከፈተውን ድልድይ በእሳት ሲቃጠል ማየት ያለውን ጠቀሜታ እና ምሳሌያዊነት ማጋነን ከባድ ነው።

ክሬምሊን ድልድዩን ተጠቅማ ወታደራዊ መሣሪያዎችን፣ ጥይቶችን እና ወታደሮችን ከሩሲያ ወደ ደቡብ ዩክሬን የጦር አውድማዎች ታዘምታለች።

የዩክሬን ባለስልጣናት ባህረ ሰላጤውን መልሰው ለመውሰድ ቃል ስለገቡ ይህ ትክክለኛ ዒላማ ነው ብለዋል ።

ከፍተኛ የሩስያ ጦር ባለባት በክሬሚያ ላይ የሚደርስ ማንኛውም ጥቃት ለክሬምሊን ሌላ ትልቅ ውርደት ተደርጎ ይታያል።

Skip podcast promotion and continue reading
የቢቢሲ አማርኛ ዩቲዩብ ቻናል

ዜና፣ ትንታኔ እና ታሪኮችን በምሥል እና በድምጽ ለማግኘት

ይህንን በመጫን ሰብስክራይብ ያድርጉ

End of podcast promotion

በተለይም በዩክሬናውያን ድልድዩ ይጠላል። የሩሲያው ፕሬዝዳንት ቭላድሚር ፑቲን 70ኛ ዓመት የልደት በዓላቸውን ባከበሩበት ቀን ድልድዩ በእሳት መያያዙን በማየታቸው በዩክሬን ያሉ የማህበራዊ ድርአምባዎች ተጠቃሚዎች በደስታ ተሞልተው ነበር ። 

በክሬሚያ የሚገኙ ባለስልጣናት በከፊል የተከፈተውን ድልድይ መጠቀም ለማይችሉ ከባድ ተሽከርካሪዎች መሸጋገሪያ መርከቦችን አዘጋጅተዋል።

የሩሲያ ብሄራዊ የፀረ-ሽብርተኝነት ኮሚቴ “ዛሬ በታማን ባሕረ ገብ መሬት ላይ በሚገኘው የክሬሚያድልድይ አውራ ጎዳና ላይ በሚገኝ የጭነት መኪና ላይ ፍንዳታ ተፈጽሟል። ወደ ክሬሚያ ባሕረ ገብ መሬት ይሄድ የነበረውን ባቡር ሰባት የነዳጅ ጋኖች በእሳት ጋይተዋል” ብሏል። 

"የድልድዩ ሁለት አውራ ጎዳናዎችም በከፊል ወድመዋል።"

የክሬሚያ ፓርላማ አፈ-ጉባኤ ቭላድሚር ኮንስታንቲኖቭ ፍንዳታውን “የዩክሬን አጥፊዎች በመጨረሻም ደም የተቀባ እጃቸውን ወደ ክሬሚያ ድልድይ ለማድረስ ችለዋል” ሲሉ ወቅሰዋል።

የሩስያው ፕሬዝዳንት ቭላድሚር ፑቲን በድልድዩ ስለደረሰው "ድንገተኛ አደጋ" ገለጻ የተደረገላቸው ሲሆን ምርመራ እንዲደረግ ትዕዛዝ ሰጥተዋል ሲሉ የክሬምሊን ቃል አቀባይ ዲሚትሪ ፔስኮቭ ተናግረዋል። ምርመራም በመካሄድ ላይ ነው።

2.7 ቢሊየን ፓውንድ የፈጀው 19 ኪሎ ሜትር የሚረዝም ድልድይ የተከፈተው ሞስኮ ክሬሚያን በህገ-ወጥ መንገድ ወደ ራሷ ከቀላቀለች ከአራት ዓመታት በኋላ ነው።

በሩሲያ መገናኛ ብዙሃን "የክፍለ ዘመኑ ግንባታ" ተብሎ ተወድሷል። የሩሲያ ባለስልጣናት ቀደም ሲል ከአየር፣ ከመሬት ወይም ከውሃ ላይ ጥቃቶች ስጋት በደንብ የተጠበቀ ነው ብለው ነበር። 

ድልድዩ ከዩክሬን ከወሰደው ግዛት ከ100 ማይል በላይ ይርቃል። አንድ የፍንዳታ ባለሙያ ለቢቢሲ እንደተናገሩት እሳቱ የተነሳው በሚሳኤል ምክንያት አይደለም።

"በመንገድ ላይ ግልጽ የሆነ ፍንዳታ/የመበታተን ጉዳት አለመኖሩ ከአየር የተተኮሰ መሳሪያ ጥቅም ላይ እንዳልዋለ ያሳያል" ብለዋል።

“በጥሩ ሁኔታ የታቀደ ጥቃት መንስኤ ሊሆን ይችላል” ሲሉም ተናግረዋል።

"በመኪና ድልድዩ እና በባቡር መስመር ላይ ፈንጂዎች በሬድዮ ትዕዛዝ በአንድ ጊዜ ጥቅም ላይ ውለዋል ብዬ እጠራጠራለሁ" ሲሉ አክለዋል።

ኪዬቭ በዚህ ግጭት ጥሩ መነሳሳት ላይ ትገኛለች። ሰራዊቱ ሰፊ ቦታዎችን ያስመለሰ ሲሆን የሩሲያ ወታደሮች ለረዥም ጊዜ ከያዟቸው ቦታዎች ጭምር እየለቀቁ ነው። 

ሞስኮ የተመሰቃቀለ ወታደራዊ ቅስቀሳ ጀምራለች። ይህም ሩሲያ ውስጥ ያልተለመደ የፀረ-ጦርነት ተቃውሞዎችን ሲያስነሳ በወታደራዊ ዕድሜ ክልል ያሉ ወንዶች ሃገር ለቀው እንዲወጡ አድርጓል።

በሩሲያ የቴሌቪዥን አቅራቢዎች እና እንግዶች ስለ ሁኔታው ጥፋት እና ጨለማው እየጨመረ ስለመሆኑ እየተናገሩ ነው ።

ጥቃቱ በዩክሬን ከተፈፀመ ክሬሚያን ዒላማ ያደረገችበት የመጀመሪያ ጥቃቷ አይሆንም።

ባለፈው ወር በሩሲያ ሳኪ የጦር ሰፈር ላይ የደረሰውን ጥቃት ጨምሮ ዩክሬን በክሬሚያ በተከታታይ ለተፈጸሙ የአየር ጥቃት ኃላፊነቱን ወስዳለች።