“የልብ ድካም ባጋጠመኝ ጊዜ ድመቴ ሕይወቴን አተረፈው”

አንዲት ብሪታኒያዊት ሴት የልብ ድካም ባጋጠማት ወቅት ድመቷ ከነበረችበት የእንቅልፍ ሰመመን በማንቃት ሕይወቷን እንዳተረፈው ትናገራለች።
ሳም ፌልስቲድ የልብ ድካም ታማ በነበረችበት ወቅት ቢሊ የተሰኘው ድመቷ እሷ ላይ እየዘለለ ድምፅ ባያወጣ ኖሮ በእንቅልፍ ላይ እያለች በዚያው ልታሸልብ ትችል እንደነበር ታምናለች።
ሳም ከእንቅልፏ ስትነቃም በቀኝ ጎኗ መንቀሳቀስ አልቻለችም ነበር፣ እናም እናቷ ሆስፒታል በመውሰድ ሕክምና እንድታገኝም ረድታታለች።
ሁለት የድመት ባለሙያዎች ቢሊ በሳም ባህሪይ ወይም አካላዊ ሁኔታ ላይ ለውጦች በማየቱ ምላሽ ሊሰጥ እንደሚችል ለቢቢሲ ተናግረዋል።
“ድመቴ፣ ቢሊ ታውቆታል”
በብሪታንያ ኖቲንግሃምሻየር፣ ስቴፕልፎርድ ከተማ ነዋሪ የሆነችው ሳም “ዶክተሮቹ በወቅቱ ሐኪም ቤት በመድረሴ ጥሩ አደረግሽ ብለውኛል” በማለት ታስረዳለች።
“ቢሊ አብዛኛውን ጊዜ ከእኔ ጋር አይቀመጥም፣ ነገር ግን የዚያን ቀን ብቻዬን ያልተወኝ የሆነ ችግር እንዳለ ተረድቶት ነው።”
“ቢሊ ሕይወቴን አትርፎታል፤ ከእሱም በተጨማሪ በዙሪያዬ ያሉ ሰዎች እንዲሁ” ብላለች።

ድመት እና ተመሳሳይ ዝርያ ያላቸውን እንስሳት ባህሪይ የሚያጠኑት ሉሲ ሆይል፣ ቢሊ በሳም ላይ የአካላዊ፣ ወይም የባህሪይ ለውጦችን በመመልከቱ አስጨንቆት ሊሆን እንደሚችል ያምናሉ።
“በእሷ ላይ መውጣቱ፣ ድምፅ ማሰማቱ እና መዝለሉ የጭንቀት ምልክት ሊሆን ይችላል” ይላሉ።
“ሕይወቷን አትርፎታል ብዬ አምናለሁ፣ ምክንያቱም የህክምና እርዳታ እንድታገኝ ያስቻላት ይህ ነው። ነገር ግን ሆን ብሎ አውቆ ነው ያደረገው በሚለው አልስማማም። ማለት የምችለው ነገር ድመቱ ላስጨነቀው ነገር ምላሽ ሰጥቷል፤ ይህም ሕይወቷ እንዲተርፍ ምክንያት ሆኗል” ይላሉ።
“ቢሊ በጣም ጎበዝ ነበር”
ባለሙያዋ እንደሚሉት ሳም በላብ ስትጠመቅ፣ ከመደበኛው በተለየ መልኩ ስትንቀሳቀስ፣ ድምፅ ስታወጣ፣ በእንቅልፍ ልቧ ስትጨነቅ፣ ጠረኗ ላይ ለውጥ መምጣቱን ቢሊ ማየትና መገንዘብ ችሏል።
“በላብ ተጠምቄ ነበር፤ ምናልባት እሱን ተረድቶት ይሆናል” በማለት ሳም ታስረዳለች።
“ይባርከውና በጣም ጎበዝ ነበር። በዚህ ወቅት ከጎኔ ነበር። አብዛኛውን ጊዜ ከእናቴ አጠገብ ነው የሚቀመጠው እናቴን ይወዳታል፤ ፍቅሩንም ይገልጽላታል” ትላለች።

የፎቶው ባለመብት, Sam Felstead
የድመቶች ክሊኒካዊ የእንስሳት ባህሪይ ባለሙያ የሆኑት ሊንዳ ራያን ቢሊ በሳም ላይ ያየው አዲስ ባህርይ አስደሳች ወይም አስጨናቂ ሆኖበት ነበር ይላሉ።
“ድመቱ በመደናገጥ ወይም በመጨነቅ ሊሆን ይችላል። ሳም ስታደርገው የነበረው እንቅስቃሴ ወይም የአካሏ መንቀጥቀጥ ትኩረቱን እየሳበ ነበር። ምክንያቱም ድመቶች ለእንቅስቃሴ ትኩረት ይሰጣሉ” ይላሉ።
“እኔ እንደማስበው ይህ የተፈጠረው በባህሪይ ካለው ለውጥ ጋር የተያያዘ ሊሆን ይችላል። ድመቶች በተፈጥሯቸው የበለጠ ብቸኝነት የሚያጠቃቸው ሲሆን፣ እንደ ውሾች ወይም ፈረሶች ወይም ጥንቸሎች ካሉ ማኅበራዊ እንስሳት ጋር አንድ አይነት ባህሪይ የላቸውም” ይላሉ።
“ድመቱ ሆን ብሎ ያደረገው ነው ብሎ ማመን ቀላል ቢሆንም፤ ምክንያቱ ግን እሱ አይደለም። ስለዚህ ሆን ተብሎ ሕይወቷን ለማዳን የተፈጸመ ነገር ነው ብሎ ማመን አይቻልም” በማለት አስረድተዋል።
“አልተጨነቀም”
ሳም ከዚያ ክስተት በኋላ ለጥቂት ቀናት በሆስፒታል ውስጥ ነበረች። የደም ቧንቧዋ በመጥበቡ ምክንያትም በሕክምና መስተካከል ነበረበት። በተጨማሪም መድኃኒቶች መውሰድ ይጠበቅባታል።
“ከሆስፒታል ከወጣሁ በኋላ ለየት ያለ ጠረን ይዤ በመምጣቴ ሊሆን ይችላል አላውቅም፣ ቢሊ ለጥቂት ሰዓታት አጠገቤ ድርሽ አላላም ነበር” ትላለች።
ቢሊ ሕይወቷን ስላተረፈው “ከፍተኛ ምስጋና” ብታቀርብም ግድየለሽ የሆነ ይመስላል።
“ምን እንደተፈጠረ ትንሽ ፍንጭ ያለው አይመስለኝም። እስካበላሁት ድረስ አይጨነቅም” ብላለች።












