በጋና ደቦሎችን ለመስረቅ ያሰበው ግለሰብ በአንበሶች ተበልቶ ሞተ

የፎቶው ባለመብት, FORESTRY COMMISSION GHANA
በጋና ዋና ከተማ አክራ በሚገኘው የእንስሳት ማቆያ እና መጎብኛ ስፍራ ውስጥ ዘሎ የገባ አንድ ግለሰብ በአንበሶች በደረሰበት ጉዳት ህይወቱ አለፈ።
የአገሪቱ የዱር እንስሳት ጥበቃ ባለስልጣናት ባለፈው ህዳር የተወለዱት እና ትልቅ ትኩረት የሳቡትን ሁለት ብርቅዬ ነጭ የአንበሳ ደቦሎችን ለመስረቅ አስቦ ሊሆን እንደሚችል ጥርጣሬጣቸውን ገልጸዋል።
ፖሊስ በጥቃቱ ዙሪያ ያሉ ምክንያቶች እና ሁኔታዎች ለማጣራት ያቀደ ምርመራ ከፍቷል። የተጎጂው አስከሬን ከእንሳቱ መኖሪያ ወጥቶ በአቅራቢያው ወደሚገኝ መቃብር ተወስዷል።
በጋና ብዙዎችን ያስደነገጠውን ይህንን ክስተት ተከትሎ አክራ የእንስሳት መኖሪያ ለጊዜው ለህዝብ እይታ ዝግ ተደርጓል።
አደጋው በተከሰተበት ጊዜ ሁለት ሴት እና ወንድ አንበሶች ብሎም ሁለቱ ነጫጭ ደቦሎቻቸው በግቢው ውስጥ ነበሩ።
የጋና የመሬት እናተፈጥሮ ሀብት ምክትል ሚኒስትር የሆኑት ቤኒቶ ኦውሱ ባዮ "አንበሶቹ ደቦሎች አሏቸው። ስለዚህ በጣም ከተጠጋህ ልጆቻቸውን ለመውሰድ እንደምትሞክር ሊሰማቸው ይችላል" ሲሉ ለጋዜጠኞች ተናግረዋል።
"ህብረተሰቡ ከእንደዚህ አይነት ድርጊት እንዲቆጠብ እንጠይቃለን" ሲሉም አክለዋል።
ዘራፊ ነው ተብሎ የተጠረጠረው ሟች ወደ አንበሶቹ ቅጥር ግቢ ለመግባት ባለ 20 ጫማውን አጥር ከመዝለሉ በፊት ሌላ ባለ 10 ጫማ አጥር ዘሎ ወደ ውስጥ ዘልቋል።
ሁለቱ ደቦሎች ለቆዳቸው ቀለም መንጣት ምክንያት የሆነው ሉሲዝም የተሰኘ በዘር የሚተላለፍ ልዩ የቆዳ ባይሪይን ከወላጆቻቸው በመውረሳቸው ነው። ይህንን ተክትሎም በጋና ውስጥ ትልቅ መስህብ ሆነዋል።
አለም አቀፉ የነጭ አንበሳጥበቃ ተቋም መረጃ እንደሚያሳየው በመላው አለም የሚገኙ የነጭ አንበሶች ቁጥር እጅግ አነስተኛ ነው።
ጋና አንበሶች በጫካዎቿ ውስጥ እምብዛም አይገኙም። ነገር ግን ተመራማሪዎች በሰሜናዊ ሞሌ ብሔራዊ ፓርክ እና አካባቢው ውስጥ አነስተኛ ቁጥር ያላቸው አንበሶች ሊኖሩ ይችላሉ ሲሉ መላምታቸውን ያስቀምጣሉ።












