ደቡብ አፍሪካ ፡ 'የአናብስቱ አባት' በሚንከባከቧቸው አንበሶች ተበሉ

ማቲው ከአንበሳ ጋር

የፎቶው ባለመብት, MATHEWSON FAMILY

ዌስት ማቲውሰን ይባላሉ። እውቅ የአካባቢ ተንከባካቢ ነበሩ። በተለይም ከደቦሎች ጋር ባላቸው ቅርበት 'የደቦል አንበሶች አባት' የሚል ቅጽል አስገኝቶላቸዋል።

እኚህ እውቅ የደቡብ አፍሪካ የዱር እንሰሳት ተንከባከባቢ የነበሩት ሰው ታዲያ በሚንከባከቧቸው አንበሶች መበላታቸው ተሰምቷል።

ክስተቱ ያልተመለደና ያልተጠበቀ ነበር።

ሚስተር ማቲውሰን በአናብስቱ ሲበሉ ባለቤታቸው አብረዋቸው በቅርብ ርቀት ነበሩ።

ሚስተር ማቲውሰን ነጫጭ አናብስቱን ለማለዳ የእግር ጉዞ ነበር ከጥበቃ ጎሬያቸው ይዘዋቸው የወጡት። ትንሽ እግራችንን አፍታተን እንመለስ ብለው።

ሆኖም ሳይመለሱ ቅርተዋል።

ባላቸውንና ለእግር ጉዞ ይዘዋቸው የወጡትን አናብስት በመኪና ከኋላ ኋላ ሲከተሏቸው የነበሩት የሟች ሚስት ነገሮች መልካቸውን እየለወጡ እንደሆነ ሲረዱ አንበሶችን ትኩረት ለማስቀየር ሙከራ ቢያደርጉም አልተሳካላቸውም።

የ68 ዓመት ባላቸውንም ከመበላት አላስጣሏቸውም።

ዌስት ማቲውሰን በደቡብ አፍሪካ ታዋቂውን የሳፋሪ ሎጁ ያስተዳድሩ ነበር። ስሙም ላየን ትሪ ቶፕ ሎጅ ተብሎ ነው የሚጠራው። የሚገኘውም በደቡብ አፍሪካ፣ ምዕራብ ጆሐንስበርግ፣ ሊምፖፖ ግዛት አካባቢ ነው።

አንበሶቹ ከዚህ ቀደም ወደ አንድ ሌላ ሎጅ ተወስደው የነበረ ሲሆን በቅርብ ጊዜ ወደ ዱር ተመልሰው ሊወሰዱ እንደነበር ተዘግቧል።

አንዷ ሴት አንበሳ ያልተጠበቀ ባህሪ ማሳየቷ ነው ነገሮችን የለወጣቸው።

በወቅቱ ሴቷ አንበሳ ባልተለመደ መልኩ በሌላኛዋ አንበሳ ላይ ጨከን የማለት ባህሪ ታይቶባት ነበር።

ከዚያ ወዲያው ደግሞ ፊቷን መልሳ ከእኚህ ከተጠባቂያቸው ጋር ልፍያ ጀመረች። ሳይታሰብ ጠባቂዋን መቦጫጨቅ እንደጀመረች ተነግሯል።

የሟች ዘመዶች እንደሚሉት የሰውየው ለሞት መዳረግ ምናልባት አንበሶቹ እርስበርስ መቦጫጨቅና ኃይል የተቀላቀለበት ልፍያ ማድረጋቸው ያመጣው መጥፎ አጋጣሚ ሊሆን ይችላል።

የሚገርመው ሰውየው አናብስቱን ከሚታደኑበት ስፍራ አውጥተው በሕይወት እንዲቆዩ ማድረጋቸው ነው።

መካነ አደን (canned hunting) እንሰሳት በአንድ ክልል ሆነው ሰዎች በሕጋዊ አደን እንዲገድሏቸው የሚደረግበት ክልል ነው።

እነዚሁ አናብስት በ2017 እንደ አውሮፓ አቆጣጠር ክልላቸውን ጥሰው በመውጣት አንድ በአካባቢው የሚጎራበታቸውን ሰው ገድለዋል።

እኚህን ጠባቂያቸውን ሲገድሉ ታዲያ ይህ ሁለተኛ ጊዜያቸው መሆኑ ነው።

ሚስተር ማቲውሰን አናብስቱን ያሳደጓቸው ገና ደቦል ሳሉ ነበር። ሰውየው ከአናብስቱ ጋር አብረዋቸው ሲላፉና ሲጫወቱ በርከት ያሉ ዘጋቢ ፊልሞች አሏቸው።