በአሜሪካ ኢንዲያናፖሊስ አንበሳዋ የሶስት ልጆቿን አባት ገደለችው

ዙሪ የተሰኘችው አናብስት

የፎቶው ባለመብት, Reuters

አንበሳዋ የሶስት ልጆቿን አባት በመካነ አራዊት ውስጥ እንደገደለችው የሀገሪቱ ባለስልጣናት አስታውቀዋል።

ዙሪ የምትሰኘውና በነፍስ ግድያ የተጠረጠረችው 10 ዓመቷ ሲሆን የልጆቿ አባት ኒያክ ደግሞ የ10 ዓመት ጎረምሳ ነው። ከመሞቱ በፊት የመካነ አራዊቱ ባለስልጣናት ሊለያይዋቸው ባለመቻላቸው ታፍኖ መሞቱ ተዘግቧል።

እነዚህ ሁለት አንበሶች በአንድ ጣሪያ ስር ለስምንት ዓመታት አብረው በፍቅር የኖሩ ሲሆን እንደ ፈረንጆቹ አቆጣጠር በ2015 ዓ.ም 3 ደቦሎችን አፍርተዋል።

የመካነ አራዊቱ ባልደረቦች በድርጅቱ ፌስቡክ ገፅ ላይ እንዳስቀመጡት በትክክል ምን እንደተፈጠረ "ጥልቅ ምርመራ" እናካሂዳለን ብለዋል።

ኒያክ የተሰኘው አንበሳ ይህንን ይመስል ነበር

የፎቶው ባለመብት, Reuters

"ኒያክ ግርማ ሞገሱ የሚያስደምም አንበሳ ነበር፤ በእጅጉ ሞቱ ልብ ሰባሪ ነው" ሲሉም አክለዋል።

የመካነ አራዊቱ ሰራተኞች ባልተለመደ መልኩ ከአናብስቱ መኖሪያ ማጓራት መስማታቸውንና በፍጥነት ወደስፍራው ማምራታቸውን ያስታውሳሉ።

ሲደርሱም ዙሪ የኒያክን አንገት ጨምድዳ ይዛ የነበረ ሲሆን ሊያስለቅቋት በሞከሩ ቁጥር መንቀሳቀስ እስኪያቆም ድረስ ሳትለቀው መቆየቷን ተናግረዋል።

ከዚህ በፊት በሁለቱ መካከል እንዲህ ኃይል የተቀላቀለበት ተግባር አስተውለው እንደማያውቁ የተናገሩት ሰራተኞቹ " ከአንበሳው ጋር የተለየ ቅርበት ነበረን፤ በሞቱ እጅጉን አዝነናል" ብለዋል።

የኢንዲያና ፖሊስ መካነ አራዊት ሃላፊ በበኩሉ "ለበርካቶቻችን እንደቤተሰብ ነበር" በማለት በመካነ አራዊቱ የሚገኙ አንበሶች አኗኗር ላይ ምንም አይነት ነገር ለመቀየር እቅድ እንደሌለ ጨምረው ገልፀዋል።