በአውሮፓ ሃገራት ጥቁሮች ላይ ያነጣጠረ ዘረኝነት “በአሳፋሪ” ሁኔታ እየጨመረ ነው

የፎቶው ባለመብት, ANADOLU AGENCY/GETTY
የአውሮፓ ሕብረት መሠረታዊ መብቶች ኤጀንሲ ባወጣው ዘገባ አፍሪካዊያን ላይ የሚደርሰው የዘረኝነት ጥቃት እየጨመረ መምጣቱን አሳይቷል።
በ13 የአውሮፓ ሃገራት የሚኖሩ ጥቁር ሕዝቦች የተካተቱበት ይህ ጥናት እንደጠቆሞው ጥቁሮች መገለልና ጥቃት እየደረሰባቸው ነው “የዕለተ ዕለት ኑሯቸውን የሚገፉት።”
መሰል ጥናት ከተሰራበት 2018 ጀምሮ ባለው ጊዜ በተለይ በጀርመን መገለል የሚደርስባቸው ሰዎች ቁጥር ጨምሯል።
የጥናቱ ውጤት “ማንቂያ ደወል ሊሆን ይገባል” ብሏል የአውሮፓ ሕብረት።
ሥራ ለማግኘት እና ቤት ለማፈላለግ ከመንገላታት ጀምሮ በሚደርስባቸው ዘረኝነት ምክንያት “ጥልቅ መረበሽ” እየፈጠረባቸው ነው ይላል።
ኤጀንሲው አክሎ በርካታ ጥቁር ሰዎች በአውሮፓ ህብረት “በቆዳቸው ቀለም ብቻ” መድልዎና መገለል እየደረሰባቸው እንደሆነ ይገልጣል።
ጥናቱ ከ6700 በላይ በኦስትሪያ፣ ዴንማርክ፣ ቤልጂየም፣ ፈረንሳይ፣ ፊንላንድ፣ ጀርመን፣ አየርላንድ፣ ጣሊያን፣ ሉግዘምበርግ፣ ፖርቹጋል፣ ፖላን እና ስዊድን የሚኖሩ የመጀመሪያና ሁለተኛ ትውልድ ጥቁር ዜጎችን አካቷል።
የዚህን ዓመት ጥናት ውጤት ከአምስት ዓመት በፊት ከተደረገው ጋር ያነፃፀረው ጥናቱ ዘረኝነት በተመለከተ “አሳሳቢ መንቀራፈፍ” ይታያል ብሏል።
በአውሮፓውያኑ 2016 አፍሪካዊ የዘር ግንድ ያላቸው ሰዎች የሚደርስባቸው መድልዎ 39 በመቶ ነበር፤ በ2022 ደግሞ 45 በመቶ ደርሷል።
በኦስትሪያና በጀርመን ከሚኖሩ በጥናቱ ከተካተቱ መካከል 64 በመቶው ባለፉት 12 ዓመታት መገለል እንደደረሰባቸው ይናገራሉ።
ይህ ቁጥር ባለፉት አምስት ዓመታት በጀርመን 76 በመቶ፣ በኦስትሪያ 72 በመቶ፣ በፊንላንድ ደግሞ 63 በመቶ ነው።
“ይህ በኢዩ የሚኖሩ የበርካታ ሰዎች እውነታ ነው። አፍሪካዊ የዘር ግንድ ያላቸው ሰዎች ሥራና ቤት ሲያፈላልጉ በተደጋጋሚ ፍትሐዊ ያልሆነ እና መድልዎ ያለበት ክስተት ይገጥማቸዋል” ይላሉ የኤጀንሲው ኃላፊ ማይክል ኦፍላኸርቲ።
ባለፈው ዓመት ጀርመን ለመጀመሪያ ጊዜ የሾመቻቸው የፀረ-ዘረኝነት ከሚሽነሩ ሪም አላባሊ-ሪድቫንድ፤ ጥናቱ ምን ያክል በዘረኝነት የሚጎዱ ሰዎችን ማገዝ እንዳለብን የሚያሳይ ነው ብለዋል።
በጥናቱ መሠረት ፖላንድ፣ ስዊድን እና ፖርቹጋል ከ13 ሃገራት የወረደ የማግለል ድርሻ ያላቸው ሃገራት ናቸው።
በ2019 አንድ የኦስትሪያ ቀኝ ዘመም ምክትል ከንቲባ ከሌላ ሃገር የመጡ ሰዎችን ከአይጥ አነፃፅረው “ልናስወግዳቸው ይገባል” የሚል ግጥም መፃፋቸው ቁጣ ቀስቅሶ ነበር።
በያዝነው ዓመት ደግሞ የፊንላንድ ቀኝ ዘመሙ ፊንስ ፓርቲ አባል ቪልሄልም ጁኒላ በተደጋጋሚ የናዚ አቋም በማንፀባረቃቸው ከሥልጣናቸው እንዲወርዱ ሆኗል።
ከአንድ ወር በኋላ ደግሞ የፊንላንድ ገንዘብ ሚኒስትሯ ሪካ ፑራ ከ15 ዓመት በፊት በሰጡ ዘረኛ አስተያየት ምክንያት ይቅርታ እንዲጠይቁ ተደርገዋል።
በ2008 ባቡር ውስጥ ስለሚያጋጥሟቸው ወጣት ስደተኞች በተመለከተ “ሽጉጥ ቢሰጡኝ ባቡሩ ሬሳ በሬሳ ይሆን ነበር” ሲሉ ነበር የፃፉት።
የኤጀንሲው ኃላፊ የጥናቱ ውጤት “አስደንጋጭና አሳፋሪ ነው” ዘረኝነት በአውሮፓ ሕብረት ቦታ የለውም የሚል አስተያየት ሰጥተዋል።
አክለው ኤጀንሲያቸው “ሁሉም ሰው በእኩልነትና በክብር እንዲኖር ለማገዝ እንጥራለን” ብለዋል።












