የሱዳኑ መሪ ጦርነቱ ወደ ጎረቤት አገራት ሊስፋፋ ይችላል ሲሉ በተመድ ስብሰባ ላይ ተናገሩ

የፎቶው ባለመብት, SARAH YENESEL/EPA-EFE/REX/SHUTTERSTOCK
የሱዳኑ መሪ በሃገራቸው የተከሰተው ጦርነት ወደ ጎረቤት አገራት ሊስፋፋ ይችላል ሲሉ በተባባሩት መንግሥታት ድርጅት ጠቅላላ ጉባኤ ላይ ተናገሩ።
የሱዳን ጦር መሪ ጀነራል አብድል ፋታህ አል-ቡርሃን ዓለም አቀፉ ማሕበረሰብ በጀነራል ሐምዳን ዳጋሎ የሚመራውን ፈጥኖ ደራሽ ኃይል ሽብርተኛ ቡድን ብሎ እንዲፈርጀውም ጥያቄ አቅርበዋል።
በሌላ በኩል የፈጥኖ ደራሹ ኃይል መሪ ጀነራል ሃምዳን ደጋሎ የተኩስ አቁም ለማድረግ ዝግጁ መሆናቸውን ተናግረዋል።
ሱዳን ከባለፈው ሚያዚያ ጀምሮ በእርስ በርስ ጦርነት የተዘፈቀች ሲሆን በሺዎች የሚቆጠሩ ሰዎች ተገድለዋል፤ በሚሊዮን የሚቆጠሩት ደግሞ አገር ጥለው ተሰደዋል።
በአውሮፓውያኑ 2021 ሁለቱ መሪዎች ተባብረው መፈንቅለ መንግሥት ማወጃቸው ይታወሳል። ነገር ግን በሁለቱ መካከል ያለው የሥልጣን ሽኩቻ ጦር እንዲማዘዙ አድርጓቸዋል።
ሐሙስ ዕለት ለተባበሩት መንግሥታት ንግግር ያደረጉት ጀነራል አል ቡርሃን የሳቸው ፓርቲ የሰላም ስምምነት ለማድረግ ዝግጁ መሆኑን ገልጠዋል።
“ጦርነቱን ለማቆምና እና የሕዝባችንን ስቃይ ለመግታት ዝግጁ ነን” ነገር ግን ፈጥኖ ደራሽ ኃይሉ ፈቃደኛ አይደለም ብለዋል።
ነገር ግን በቅፅል ስማቸው ሄሜቲ ተብለው የሚታወቁት ተቀናቃኛቸው ጀነራል ደጋሎ ለተመድ በላኩት ተንቀሳቃሽ ምስል ግጭቱን በንግግር ለመፍታት ዝግጁ መሆናቸውን ተናግረዋል።
ሁለቱ የጦር ጀነራሎችን ልዩነቶቻቸውን በንግግር እንዲፈቱ አሜሪካ፣ ሳዑዲ አረቢያ እና ግብጽ ያደረጉት ጥረት ሳይሳካ ቀርቷል።
የፈጥኖ ደራሹ ኃይል አባላት በመላው ሱዳን መሰማራታቸውንና ጀነራል አል ቡርሃን እንደ ስጋት ማየታቸውን ተከትሎ ነው የሱዳን የእርስ በርስ ጦርነት ባለፈው ሚያዚያ የፈነዳው።
የመጀመሪያዋን ጥይት ማነው የተኮሰው የሚለው አከራካሪ ቢሆንም ግጭቱ በፍጥነት አይሎ በመላ ሃገሪቱ ተስፋፍቷል።
በጦርነቱ ምክንያት ቢያስን 7500 ሰዎች መገደላቸውን አክሌድ የተሰኘው መንግሥታዊ ያልሆነ ድርጅት ያወጣው መረጃ ያሳያል፤ በሚሊዮን የሚቆጠሩ ደግሞ ተፈናቅለዋል።
በአውሮፓውያኑ 2021 የተፈፀመውን መፈንቅለ መንግሥት ተከትሎ ጀነራል አል ቡርሃን የሱዳን መሪ ሆነው ሲያገለግሉ ቆይተዋል። ዓለም አቀፍ ዕውቅና ለማግኘት በመላው ዓለም ሲዘዋወሩም ከርመዋል።
ለተባበሩት መንግሥታት ባደረጉት ንግግራቸው ፈጥኖ ደራሽ ኃይሉ ከሩሲያ ቫግነር ቡድን ጋር ያለውን ግንኙነትም አንስተዋል።
ቅጠረኛው ቫግነር ቡድን በሱዳን ጨምሮ በማዕከላዊ አፍሪካ ሪፓብሊክ፣ ሊቢያ፣ ሞዛምቢክ እና ማሊ እንደሚንቀሳቀስ ይታመናል።
“የጦርነቱ አደጋ አሁን ለጎረቤት ሃገራትም እና ለመላው ዓለም ሰላምና ፀጥታ ስጋት እየሆነ ነው። አማፂያኑ ሕጋዊ ያልሆኑ እና ሽብርተኛ ከተባሉ ሃገራትና ድርጅቶች ድጋፍ እያገኙ ነው” ብለዋል።

የፎቶው ባለመብት, Getty Images
ጀነራል አል ቡርሃን የሄሜቲ ጦር “ግድያ፣ ማቃጠል፣ መድፈር፣ ማፈናቀል፣ ዝርፍያ፣ ስቃይ እና የጦር መሣሪያ በሕገ-ወጥ መንገድ ማዘዋወር፣ ቅጥረኛ ቡድኖች ጋር መተባበርና ሕፃናትን በጦርነት ማሳተፍ በመሳሰሉ ወንጀሎች ላይ ስለተሳተፈ” ሽብርተኛ ቡድን ተብሎ ሊፈረጅ ይገባል ብለዋል።
እሳቸው እንደሚሉት እኚህ ወንጀሎች ኃላፊነት ሊወሰድባቸው የሚገባና ቅጣት የሚያስከትሉ ናቸው።
ይሁን እንጂ አል ቡርሃንም ቢሆኑ በግጭቱ ወቅት በወሰዱት ወታደራዊ እርምጃ ይወቀሳሉ።
የተባበሩት መንግሥታት የሱዳን መልዕክተኛ የነበሩት ሶልከር ፐርዝስ መስከረም ወር ሥልጣን ሲለቁ ሁለቱም ጀነራሎች ወደ ጦርነት በማምራታቸው እጅግ ተችተው ነበር።
የቀድሞው መልዕክተኛ የፈጥኖ ደራሽ ኃይሉን ወሲባዊ ጥቃት በመፈፀም፣ በዝርፍያ እና በግድያ የወቀሱ ሲሆን የሱዳን ጦር ኃይል ደግሞ ሰላማዊ ዜጎች የሚኖሩበትን ሳይለይ የአየር ጥቃት ሰንዝሯል ብለዋል።
የሄሜቲ ተዋጊዎች ብዙውን ጊዜ በርካታ ሰዎች በሚኖሩባቸው ከተሞች የሚሰፍሩ ሲሆን የሱዳን ጦር እኒህ ሰፈሮች የጦርነት ዒላማ ናቸው ብሎ ያምናል።
ዩናይትድ ስቴትስ ጀነራል ደጋሎ ላይ ማዕቀብ ብትጥልም፤ ጀነራል አል ቡርሃን በመፈንቅለ መንግሥት ወደ ሥልጣን በመምጣታቸው በምዕራባዊያን ዘንድ ያላቸው ተቀባይነት እምብዛም አይደለም።












