በሕንድ እና በካናዳ መካከል ያለው ዲፕሎማሲያዊ ውጥረት አይሎ ሕንድ ለካናዳ ዜጎች ቪዛ መስጠት አቆመች

የፎቶው ባለመብት, Getty Images
የአንድ የሃይማኖት መሪ ግድያን ተከትሎ በሕንድ እና በካናዳ መካከል የተፈጠረው ዲፕሎማሲያዊ ውጥረት አይሎ ሕንድ ለካናዳ ዜጎች ቪቫ መስጠት አቆመች።
በካናዳ የሚገኘው የሕንድ ሚሲዮን ከዛሬ ሐሙስ መስከረም 10/2016 ዓ.ም. ጀምሮ ለካዳና ዜጎች የቪቫ አገልግሎት መስጠት አቁሚያለሁ ብሏል።
በሁለቱ አገራት መካከል ቁርሾ የተፈጠረው ጠቅላይ ሚንስትር ጀስቲን ትሩዶ የሕንድ የዘር ግንድ ያለው እና የካናዳ ዜጋ የሆነው የሲክ ሃይማኖት መሪ ካናዳ ውስጥ መገደሉን ተከትሎ ከግድያው ጀርባ የሕንድ መንግሥት እጅ አለበት ካሉ በኋላ ነው።
ሃርዲፕ ሲንግህ ኒጃር የተባለው ግለሰብ ሰኔ 2015 ላይ ብሪቲሽ ኮሎምቢያ በምትባለው የካናዳ ግዛት ውስጥ ነበር መኪናው ውስጥ በጥይት ተመትቶ ሞቶ የተገኘው።
ይህ የሲክህ ሃይማኖት መሪ ፊታቸውን በጭንብል በሸፈኑ ሁለት ግለሰቦች መገደሉን ፖሊስ በወቅቱ ይፋ ቢያደርግም በግድያው ተጠርጥሮ በቁጥጥር ሥር የዋለ የለም።
ግለሰቡ በሕንዷ ፑንጃብ ግዛት ከሃሊስታን የተሰኘች ራስ ገዝ የሲክህ ግዛት ለመፍጠር በሚያደርገው እንቅስቃሴ ምክንያት ከሕንድ ተሰድዶ በካናዳ ይኖር ነበር።
ከሕንድ ውጭ የሚገኙ የሲክህ እምነት ተከታዮች ከሃሊስታን የተሰኘ ግዛት ለመመስረት የሚያደርጉት ጥረት በሕንድ መንግሥት ቀይ መስመርን እንደ ማለፍ የሚቆጠር ሲሆን የሕንድ መንግሥት የዚህን እቅንስቃሴ አባላትን በሽብር ወንጀል ይከሳቸዋል።
ይህን የጠቅላይ ሚንስትር ጀስቲን ትሩዶ ክስ ሕንድ አጥብቃ የተቃወመች ሲሆን ለቀረበባት ክስ በሰጠችው መልስ የካናዳ ዲፕሎማትን ከአገሯ ከማባረሯም በላይ የሕንድ መንግሥትን ወክሎ ለካዳና ዜጎች ቪዛ ይሰጥ የነበረው ተቋም አገልግሎቱን እንዲያቆም አድርጋለች።
ሕንድ ለካናዳ ዜጎች ቪዛ መስጠት ማቆሟ ይፋ ከመደረጉ በፊት በሰሜን አሜሪካዊቷ አገር ሕንድ ጠል የሆኑ እንቅስቃሴዎች እና ፖለቲካዊ ይዘት ያላቸው የጥላቻ ወንጀሎች በመበራከታቸው ወደ ካናዳ የሚጓዙ ወይም በካናዳ የሚኖሩ ሕንዳውያን ጥንቃቄ እንዲያደርጉ የሕንድ መንግሥት መልዕክት አስተላልፎ ነበር።
ካናዳ ከአጠቃላይ ዜጎቿ 3.7 በመቶ ወይም 1.4 ሚሊዮን የሚሆኑት የሕንድ የዘር ግንድ እንዳላቸው እአአ 2021 ላይ የተካሄደ ጥናት ጠቁሟል። ከዚህ በተጨማሪም ለከፍተኛ ትምህርት 320ሺህ ሕንዳውያን ወደ ካናዳ ተጉዘዋል። ይህ ማለት ከአጠቃላይ የውጭ አገር ተማሪዎች 40 በመቶ የሚሆኑት ሕንዳውያን ናቸው።
ዴልሂ ትናንት በካናዳ “ጸረ-ሕንድ” የሆኑ አጀንዳዎችን በሚቃወሙ ሕንዳውያን እና የሕንድ ዲፕሎማቶች ላይ ማሰፈራሪያዎች ደርሰውባቸዋል ብላለች።

የፎቶው ባለመብት, SIKH PA
ይህ በእንዲህ እንዳለ የካናዳ ጠቅላይ ሚንስትር ጀስቲን ትሩዶ በሲህክ የሃይማኖት መሪው ግድያ የሕንድ መንግሥት የደኅንነት አባላት ተሳታፊ ስለመሆናቸው አስተዳደራቸው ምርመራ እያደረገ ነው ብለዋል።
“በካናዳ ግዛት የካናዳ ዜጋን በመግደል ውስጥ የውጭ መንግሥት ተሳትፎ ፈጽሞ ተቀባይነት የሌለው ሉዓላዊነታችንን የጣሰ ነው” ሲሉ ጠቅላይ ሚንስትሩ ለአገሪቱ ምክር ቤት ተናግረዋል።
ከሕንድ ውጭ ካናዳ በርካታ ሲህኮች የሚገኙባት አገር ስትሆን የቡድኑ አባላት እንደፈቃቸው በአደባባይ እየወጡ ድምጻቸውን ማሰማታቸው ሕንድን ሲያበሳጭ የቆየ ሲሆን በዚህም ምክንያት በሁለቱ አገራት መካከል ያለው ግንኙነት ሻክሯል።
ሃርዲፕ ኒጃር ወደ ካዳና እአአ 1997 ካመራ በኋላ በብሪቲሽ ኮሎምቢያ አንቱታን ያተረፈ የሲህክ መሪ መሆን ችሏል። ሕንድ ይህን ግለሰብ ከፑንጃብ ግዛት በመገንጠል ካሊስታን የተባለ ነጻ ግዛትን ለማቋቋም ከሚታገለው ካሊስታን ታይገር ፎርስ ጋር ግንኙነት አለው በማለት እአአ 2020 ላይ አሸባሪ ስትል ፈርጃው ነበር።












