በጋምቤላ ቢያንስ 30 የውጭ አገር ስደተኞች በረሃብ እና በደረሱባቸው ጥቃቶች መሞታቸው ተገለጸ

የጋምቤላ ከተማ

የፎቶው ባለመብት, Gambella Press Secretariat Office

በጋምቤላ ክልል ቢያንስ 30 የውጭ አገር ስደተኞች በረሃብ፣ በምግብ እጦት እና በተሰነዘሩባቸው ጥቃቶች ሕይወታቸው ማለፉን የኢትዮጵያ ሰብዓዊ መብቶች ኮሚሽን (ኢሰመኮ) አስታወቀ።

ስደተኞቹ ምግብ ፍለጋ መጠለያ ካምፓቸውን ለቀው በሚወጡበት ወቅት ጥቃቶች እንደተሰነዘሩባቸውም ኢሰመኮ የስደተኞች እና ከስደት ተመላሽ አገልግሎት እና የስደተኞች ተወካዮችን ዋቢ አድርጎ መስከረም 9/ 2016 ዓ.ም ባወጣው መግለጫ አስታውቋል።

በክልሉ በሚገኙ የስደተኛ ጣቢያዎች ለወራት ያህል የምግብ እርዳታ በመቆሙም ስደተኞቹ ለከፋ የምግብ እጦት እና ረሃብ መዳረጋቸው አሳሳቢ እንደሆነም ኢሰመኮ ገልጿል።

400 ሺህ የሚጠጉ ስደተኞች መኖሪያ በሆነው ጋምቤላ ክልል የሚገኙትን ንጉኑየል፣ ቲርኪዴ እና ኩሌ የስደተኞች ጣቢያዎች የሰብዓዊ እርዳታ አቅርቦትን በተመለከተ ኢሰመኮ ክትትል አድርጓል።

ቢያንስ 112 ሺህ ስደተኞች በተጠለሉበት የንጉንየል ጣቢያ ከባለፈው ዓመት ግንቦት ወዲህ የምግብ እርዳታ ቀጥ ብሏል።

የንጉንየል ጣቢያ በጋምቤላ ከሚገኙት መጠለያ ጣቢያዎች ትልቁ ሲሆን በተለይም በአውሮፓውያኑ 2016 በደቡብ ሱዳን የተነሳውን ግጭት ሸሽተው ወደ ክልሉ የገቡ በርካታ ስደተኞችን አስጠልሏል።

ከ72 ሺህ ስደተኞች በላይ በያዘው ቲየርኪዴ እንዲሁም ከ52 ሺህ በላይ ስደተኞችን ባስጠለለው ኩሌ ጣቢያዎች ከሰኔ ጀምሮ ምንም አይነት የምግብ እርዳታ አለመድረሱንም ኢሰመኮ ተመልክቷል።

በዚህም በእነዚህ መጠለያ ጣቢያዎች እንዲሁም በክልሉ በሚገኙ ሌሎች ጣቢያዎች የሚገኙ ስደተኞች በገጠማቸው ከፍተኛ የምግብ እጥረት ምክንያት አደጋ ውስጥ ወድቀዋል ብሏል።

ስደተኞቹ በሌሎች መንገዶችም ምግብ ለማግኘት ተቸግረዋል ተብሏል።

ኮሚሽኑ የምግብ እርዳታው መቆሙ ስደተኞቹን ከረሃብ ጋር በተያያዘ ለሞት የዳረጋቸው ሲሆን በክልሉ ያለው የጸጥታ ችግርም የስደተኞቹን ፈተና የበለጠ አባብሶታል ብሏል።

Skip podcast promotion and continue reading
የቢቢሲ አማርኛ ዩቲዩብ ቻናል

ዜና፣ ትንታኔ እና ታሪኮችን በምሥል እና በድምጽ ለማግኘት

ይህንን በመጫን ሰብስክራይብ ያድርጉ

End of podcast promotion

ስደተኞቹ ምግብ ፍለጋ በሚል ከመጠለያዎቹ ውጭ በሚሄዱበት ወቅት ጥቃት እንደተፈጸማባቸውም የኢሰመኮ ሪፖርት ያስረዳል።

መጠለያ ጣቢያዎቹን ከአካባቢው መንደሮች እና ከተሞች ጋር በሚያገናኙ መንገዶች ላይ ስደተኞቹ ጥቃት እንደደረሰባቸው የጠቆመው የኢሰመኮ መግለጫ፣ ይህም ለበርካቶች ሕይወት መቀጠፍ ምክንያት ሆኗል።

ምግብ ያጡት አንዳንድ ስደተኞች ከመጠለያው ውጭ ከቆሻሻ መጣያዎች በፍለጋ እና በመስረቅ ምግብ ለማግኘት ሲሞክሩም ሕይወታቸውን ማጣታቸውንም ነው ኢሰመኮ በመግለጫው ያሰፈረው።

የምግብ እርዳታ መቆሙ እንዲሁም የተመጣጠነ የምግብ እጥረት ተደማምሮ ህጻናትን ጨምሮ የበርካቶች ሕይወት ላይ ስጋት ጋርጧል ብሏል።

ኢሰመኮ በተለያዩ የአገሪቱ አካባቢዎች ያሉ ስደተኞች እንዲሁም የተፈናቀሉ ዜጎች ሰብዓዊ ሁኔታ በእርዳታ መቆም እና በቀጠሉ ግጭቶች ምክንያት እያሽቆለቆለ መምጣቱ በእጅጉ እንዳሳሰበውም ገልጿል።

ስደተኞችን የሚያስተናግዱ አገሮች በግዛቶቻቸው ውስጥ ያሉ ስደተኞችን ደኅንነት የማረጋጋጥ ኃላፊነት ቢኖርባቸውም፣ ሸክሙንና ኃላፊነቱን ለመጋራት ዓለም አቀፍ ትብብርን ማጠናከር እንደሚያስፈልግ ኢሰመኮ አጽንኦት በመስጠት ገልጿል።

የኢትዮጵያ መንግሥት፣ የሚመለከታቸው የረድዔት ተቋማት በተለይም የአሜሪካ ዓለም አቀፍ የልማት ተራድዖ ድርጅት (ዩኤስኤይድ)፣ የተባበሩት መንግሥታት የዓለም የምግብ ፕሮግራም እርዳታውን በአስቸኳይ እንዲጀምሩም ኮሚሽኑ ጥሪውን አቅርቧል።

በጋምቤላ እንደ አዲስ የተቀሰቀሰው ግጭት የሰዎች ሕይወት መቅጠፉንም ተከትሎ የክልሉ መንግሥት ከሐምሌ 13/2015 ዓ.ም ጀምሮ ተግባራዊ የሚሆን ላልተወሰነ ጊዜ የሚቆይ ክልላዊ የሰዓት እላፊ መጣሉን ማስታወቁ ይታወሳል።

ከሁለት ዓመት ገደማ በፊት የጋምቤላ ሕዝብ ነጻነት ግንባር እና የኦሮሞ ነጻነት ሠራዊት በጋራ በመሆን በጋምቤላ ከተማ ላይ ጥቃት በመክፈት ከተማዋ ለቀናት ከተለመደ እንቅስቃሴዋ ውጪ ሆና እንደቆየችና ከ40 በላይ ሰዎችም መገደላቸው ይታወሳል።

ከደቡብ ሱዳን ጋር የሚዋሰነው የጋምቤላ ክልል ከቅርብ ወራት ወዲህ ተደጋጋሚ ጥቃቶችን አስተናግዷል።

ክልሉ በተለያዩ ጊዜያት ብሔርን መሠረት ያደረጉ ተደጋጋሚ ጥቃቶችና ግጭቶች ያጋጠሙት ሲሆን፣ በተጨማሪም ከደቡብ ሱዳን ሰርገው የሚገቡ ታጣቂዎችም ጥቃት ይፈጽሙበታል።

እንደ የተባበሩት መንግሥታት የስደተኞች ድርጅት መረጃ ከሆነ ክልሉ ከ300 ሺህ በላይ የደቡብ ሱዳን ስደተኞች መኖርያ ነው።