በተመኘው ዩኒቨርሲቲ ለመማር 4ሺህ ኪሎ ሜትር በብስክሌት የተጓዘው ወጣት

የፎቶው ባለመብት, MAMADOU BARRY
የተመኘውን ዩኒቨርሲቲ ለመቀላቀል የምዕራብ አፍሪካ አገራትን አቆራርጦ 4ሺህ ኪሎ ሜትሮችን በሳይክል የተጓዘው ተማሪ ሕልሙ ሰምሮለት በግብጹ ዩኒቨርሲቲ ነጻ የትምህርት ዕድል አገኘ።
ማማዱ ሶፋዩ ቤሪ ከትውልድ አገሩ ጊኒ ተነስቶ ለአራት ወራት ግብጽ ለመድረስ ባደረገው ጉዞ ሃሩር በረሃዎችን በሳይክሉ አቆራርጧል፤ ድንበር ላይ ታስሯል፤ ተጎሳቁሏል። በመጨረሻ ግን ጥረቱ ፍሬ አፍርቷል።
የ25 ዓመቱ ወጣት ግብጽ ለመድረስ ጽንፈኛ እስላማዊ ታጣቂዎች የሚቆጣጠሯቸውን አካባቢዎች ማለፍ እና መፈንቅለ መንግሥት የተካሄደባቸውን የአፍሪካ አገራት ድንበር መሻገር ነበረበት።
ማማዱ ከብዙ ጥረት በኋላ የግብጹ ጥንታዊ አል-አዝሃር ዩኒቨርሲቲ ነጻ የትምህርት እድል ሲሰጠው ዕድሉን በማግኘቱ “በጣም በጣም ደስተኛ ነኝ” ሲሉ ለቢቢሲ ተናግሯል።
የ25 ዓመቱ ወጣት በግብጹ ዩኒቨርሲቲ እላማዊ ትምህርት ለመከታተል ክፍያ መፈጸም እንደማይችል፤ ወደ ግብጽ ለመጓዝም የአየር ቲኬት ለመቁረጥ ገንዘብ ስለሌለው በሳይክል አደገኛውን ጉዞ ለማድረግ መወሰኑን ይገልጻል።
ባለ ትዳር እና የአንድ ልጅ አባት የሆነው ተማሪ በተመኘው ዩኒቨርሲቲ የፈቀደውን ትምህርት ለመከታተል ማሊ፣ ቡርኪና ፋሶ፣ ቶጎ፣ ቤኒን፣ ኒጀር እና ቻድ በሳይክል አቆራርጧል።
አል-አዝሃር ዩኒቨርሲቲ በሱኒ እስላማዊ ጥናት በዓለማችን ተጽእኖ ፈጣሪ ተቋማት መካከል አንዱ ነው። የትምህርት ተቋሟ ከተመሠረት ከ1ሺህ ዓመታት በላይ አስቆጥሯል።
ማማዱ በጉዞ ወቅት ብዙ አስቸጋሪ ነገሮች እንዳጋጠሙት ለቢቢሲ ተናግሯል።
እንደ ማሊ፣ ቡርኪና ፋሶ እና ኒጀር ያሉ አገራት ውስጥ መጓዝ ደኅንነታቸው የተረጋገጠ ስላልሆነ አደጋው ከፍ ያለ ነው ይላል ተማሪው።
“በጣም ብዙ ችግሮች አሉባቸው (አገራቱ) ሕዝቡም ስጋት ውስጥ ነው። በማሊ እና ቡርኪና ፋሶ ሰዉ እንደ መጥፎ ሰው ሲመለከተኝ ነበር። ወታደሮችንም ከእነ መኪኖቻቸው እና ትልልቅ መሳሪያዎቻቸው ጋር ስመለከት ነበር” ይላል።

የፎቶው ባለመብት, NAHLA ELSEIDY/FACEBOOK
ተማሪው እንደሚለው በቡርኪና ፋሶ ሁለት ጊዜ፤ በቶጎ ደግሞ አንድ ጊዜ ታስሮ እንደነበረ ይናገራል።
ይሁን እንጂ ማማዱ ቻድ ሲደርስ ከአንድ ጋዜጠኛ ጋር ስለጉዞው ቃለ መጠይቅ ማድረጉ መልካም አጋጣሚን ፈጠረለት።
ጋዜጠኛው የማማዱን ታሪክ ካሳተመ በኋላ አንድ በጎ ፍቃደኛ ከቻድ እስከ ግብጽ ያለውን ቀሪውን ጉዞ በአውሮፕላን እንዲያደርግ የአየር ቲኬት ገዝቶለታል።
ይህ ማለት ማመዱ በእርስ በርስ ግጭት እየታመሰች ያለችውን ሱዳንን በሳይክል እንዳያቋርጥ ረድቶታል።
በመጨረሻም ወጣቱ ነሐሴ 30/2015 ዓ.ም. ግብጽ ካይሮ ከደረሰ በኋላ የዩኒቨርሲቲውን ኃላፊዎች አግኝቶ ማነጋገር ችሏል።
የዩኒቨርሲቲው የእስላማዊ ጥናቶች ትምህርት ክፍል ኃላፊ የሆኑት ዶ/ር ናሃላ ኤልሴዲ ከማማዱ ጋር ከተነጋገሩ በኋላ ሙሉ ወጪው ተሸፍኖለት ትምህርቱን እንዲከታተል ዕድል ሰጥተውታል።












