የኢትዮጵያ ቀይ መስቀል ማኅበር በአማራ ክልል ተሽከርካሪው በታጣቂዎች እንደተወሰደበት ገለጸ

የፎቶው ባለመብት, Ethiopian Red Cross Society
የኢትዮጵያ ቀይ መስቀል ማህበር በአማራ ክልል ፍኖተ ሰላም ከተማ ከሚገኘው ጽህፈት ቤቱ ለሰብአዊነት ተግባር የሚጠቀመው አምቡላንስ በታጣቂዎች ‘በኃይል’ እንደተወሰደበት አስታውቋል።
ማህበሩ ትናንት መስከረም 9/2016 ምሽት በፌስቡክ ገጹ ባወጣው መግለጫ ንብረትነቱ የምዕራብ ጎጃም ዞን የቀይ መስቀል ማህበር ቅርንጫፍ የሆነ አምቡላንስ ማክሰኞ መስከረም 8/2016 ዓ.ም “ባልታወቁ የታጠቁ” ኃይሎች እንደተወሰደበት አመላክቷል።
“አምቡላንስ ተሸከርካሪው የተወሰደው በፍኖተ ሰላም ከተማ ከሚገኘው የቅርንጫፉ ጽ/ቤት ቅጥር ግቢ ውስጥ ሲሆን የተወሰደውም በአስገዳጅ ሁኔታ ነው” ሲልም አክሏል።
ይህንን ድርጊት የኮነነው ማህበሩ ተግባሩ ኢትዮጵያ ከፈረመቻቸው ዓለም አቀፍ ሥምምነቶች ጋር የሚፃረር እንደሆነም ጠቁሟል።
ድርጊቱ “ከማህበሩ ዓላማ ውጪ መሆኑን በመረዳት ድርጊቱን የፈፀሙት አካላት አምቡላንሱን ለማህበሩ በመመለስ ለማኅበረሰቡ የተለመደውን ሰብዓዊ አገልግሎት መስጠት እንድንችል እንድታደርጉ እንጠይቃለን” ሲልም ጥሪ አቅርቧል።
ማህበሩ አክሎም በመላው ኢትዮጵያ ለሰብዓዊ አገልግሎት የተሰማሩ የማህበሩ ሠራተኞች፣ በጎፈቃደኞችና አምቡላንስን ጨምሮ ተሽከርካሪዎች “በነፃነት ተንቀሳቅሰው መስራት እንዲችሉ፣ ደህንነታቸው እንዲጠበቅ፣ ታጣቂ ኃይሎች ከእንደዚህ አይነት ድርጊት እንዲቆጠቡና ማኅበረሰቡም መሰል ድርጊቶችን እንዲያወግዝ እንጠይቃለን” ብሏል።
ቀይ መስቀል ታጣቂዎች ያላቸውን አካል በስም ያልጠቀሰ ሲሆን በጉዳዩ ላይ ከመንግሥትም ሆነ ከታጣቂዎች የተባለ ነገር የለም። በክልሉ በመከላከያ ሰራዊት እና በፋኖ ታጣቂዎች መካከል እየተካሄደ ያለው ውጊያ ረገብ ብሎ እንደነበር የተዘገበ ቢሆንም ከአዲስ ዓመት በኋላ ግጭቱ ስለማገርሸቱ አንዳንድ መረጃዎች እየወጡ ይገኛሉ። በመከላከያ እና በፋኖ ታጣቂዎች መካከል ግጭቶች አሉባቸው ከተባሉ ስፍራዎች መካከል የምዕራብ ጎጃም አካባቢዎች ተጠቃሽ ናቸው።
የቀይ መስቀል ማህበር አምቦላንሶቹ በኃይል ሲወሰዱበት ይህ የመጀመሪያው አይደለም።
ባለፈው ዓመት መጋቢት ወር ላይ በኦሮሚያ ክልል ቄለም ወለጋ ዞን ሁለት አምቡላንሶች እንደተወሰዱበት የኢትዮጵያ ቀይ መስቀል ማህበር አስታውቆ ነበር።
የማህበሩ የሰብዓዊ ዲፕሎማሲ እና የግንኙነት ጉዳዮች ኃላፊ ዶ/ር ሰለሞን አሊ በቄለም ወለጋ ቅርንጫፍ ንብረት የሆኑና ማህበሩ ለሰብዓዊ አገልግሎት የሚጠቀምባቸው ሁለት አምቡላንሶች በስራ ላይ እያሉ መወሰዳቸውን በወቅቱ ለቢቢሲ ተናግረው ነበር።
ኃላፊውአምቡላንሶች መሰወር፣ በማይታወቁ ኃይሎች መወሰድ በተለያዩ ጊዜዎች እንደሚያጋጥሙ ጠቅሰው በተመሳሳይ አካባቢ ከዚህ ቀደም ሁለት አምቡላንሶች መቃጠላቸውን አስታውሰው ነበር።
በወቅቱ በትግራይ ያሉ ከ200 በላይ አምቡላንሶቻቸው የት እንዳሉ እንደማያውቁም ጠቅሰው ነበር።
በሌላ በኩል በትግራይ ጦርነት ከተቀሰቀሰ ከስድስት ቀናት በኃላ ከሁመራ ዳንሻ ባለው መስመር ሶስት አምቡላንሶች በአካባቢው በሚንቀሳቀሱ ታጣቂዎች ተኩስ ተከፍቶባቸው ጉዳት እንደደረሰ እኚሁ ኃላፊ ለቢቢሲ ገልጸው ነበር።
በዚህ ክስትት የማህበሩ ሰራተኞች ላይ የደረሰ ጉዳት አልነበረም።
የኢትዮጵያ ቀይ መስል ማህበር 45 ሺህ የሚሆኑ የሰለጠኑ በጎ ፈቃደኞች፣ በአጠቃላይ 200 ሺህ በጎ ፈቃደኞችና፣ ከስድስት ሚሊዮን በላይ አባላት አሉት። ኃላፊው ማህበሩ ከ550 በላይ አምቡላንሶች እንዳሉት በወቅቱ ተናግረው ነበር።












