በአወዛጋቢዋ ግዛት ያሉ የአርመን ኃይሎች ትጥቅ ለመፍታት መስማማታቸውን አዘርባጃን አወደሰች

የተፈናቀሉ አርመናውያን

የፎቶው ባለመብት, Russian Defence Ministry

አዘርባጃን በአወዛጋቢዋ ናጎሮኖ ካራባክ ግዛት በሚገኙ የአርመን ኃይሎች ላይ ለ24 ሰዓታት የፈጀ ወታደራዊ ጥቃት ማድረጓን ተከትሎ የአገሪቱ ሉዓላዊነት እንደተመለሰ ፕሬዚዳንቷ አስታወቁ።

የካራባክ የአርመን ኃይሎች ትጥቅ ለመፍታት እና እጅ ለመስጠት ከተስማሙም ከሰዓታት በኋላም ፕሬዚዳንት ኢልሃም አሊዬቭ የአዘርባጃንን ጦር ጀግንነት አወድሰዋል።

እስያንና አውሮፓን የሚያገናኘው፣ የሩሲያ ዛሮችን ጨምሮ፣ ሮማ፣ ቱርክ፣ የቀድሞዋ ፋርስ ሌሎች ሌሎች መሪዎችም የገዟት ናጎሮኖ ካራባክ 120 ሺህ የሚሆኑ አርመናውያን እንዲሁም የአዘሪ ነገድ አባላት ይኖሩበታል።

ተራራማዋ እና ባህር በር አልባዋ ግዛት ናጎሮኖ ካራባካህ ከአዘርባጃን በስተደቡብ ምዕራብ ትገኛለች።

ሁለቱ የቀድሞ የሶቪየት ህብረት አባል አገራት አርሜኒያና አዘርባጃን ግዛቲቷ የኔ ነው በሚልም ጦርነት ተማዘውባታል። በርካቶች አልቀውባታል።

በአውሮፓውያኑ 2020 ለስድስት ሳምንታት የዘለቀው ጦርነት ለብዙ ሺህ ሰዎች ሞት ምክንያት ቢሆንም ነገር ግን አዘርባጃን በቱርክ በመደገፍ ግዛቲቷን እንድትቆጣጠር አድርጓታል። ይህም ሁኔታ በስፍራው የሚኖሩ አርመናውያን እንዲነጠሉ አድርጓቸዋል።

በአለም አቀፍ ደረጃ ምዕራባውያኑ ናጎሮኖ ካራባክን በአዘርባጃን ግዛትነት ዕውቅና ሰጥተዋታል።

ነገር ግን በአርመን መንግሥት የሚደገፉት የካራባክ ኃይሎች ግዛቲቷን ከአዘርባጃን ገንጥለው ነጻ አገር መመስረታቸውንም በተመለከተ ድጋፍ ሆነ ተቃውሞ አላሰሙም።

አዘርባጃን ይህችን የተገነጠለችውን ግዛት ሙሉ በሙሉ በቁጥጥሯ ስር ለማዋልም አቅዳለች።

የአዘርባጃን ወታደራዊ ኃይል በያዝነው ሳምንት ማክሰኞ የካራባክ ጦር ነጭ ሰንደቅ አላማ እንዲያውለበልብ እና “ህገወጥ አገዛዙን” እንዲያፈርስ ለማድረግ በሚል የ”ጸረ-ሽብር” ዘመቻ መክፈቱን አስታውቆ ነበር።

ላለፉት ዘጠኝ ወራት አዘርባጃን ከአርመኒያ ወደ ካራባክ የሚወስደውን የላቺን ኮሪዶር በመባል የሚታወቀውን ብቸኛ መንገድ በመዝጋትም የአርመንን ኃይል ለማንበርከክ ተጠቅማበታለች።

ተነጥለው የሚኖሩት አርመኖች ምግብ፣ መድኃኒት እና ሌሎች መሰረታዊ ፍጆታዎች እጥረት የገጠማቸው ሲሆን አርመንም መርዳት አልቻለችም።

የአዘርባጃን ጦር ባደረገው ወታደራዊ ዘመቻ ቢያንስ 32 ሰዎች መገደላቸውንና እና 200 ሰዎች መቁሰላቸውን የአርመን ባለስልጣናት አስታውቀዋል።

ሆኖም ተገንጣይ የአርመንያ የሰብዓዊ መብት ባለስልጣን እንደተናገሩት ቢያንስ 200 ሰዎች መገደላቸውንና ከ400 በላይ ቁስለኞች መኖራቸውን ነው።

ቢቢሲ በተለያዩ አካላት የተነገሩ አኃዞችን ማረጋገጥ አልቻለም። በትናንትናው ዕለት በሺዎች የሚቆጠሩ ሰልፈኞች በአርሜኒያ ዋና ከተማ ዩሬቫን የአደባባይ ተቃውሞ አሰምተዋል። የአርመን ጠቅላይ ሚኒስትር ኒኮል ፓንሺያን ከግዛቲቱ ጋር በተፈጠረው ቀውስ ከስልጣን እንዲለቁ ጠይቀዋል።

በሩሲያ ሰላም አስከባሪ አማካኝነት ግጭት የማቆም ስምምነት ከመደረሱ በፊት የአዘርባጃን ጦር ከአርመን ኃይሎች ከ90 በመቶ በላይ ግዛቶችን ተቆጣጥሬያለሁ ብሎ ነበር። የአዘርባጃን እና የሩሲያ የሰላም አስከባሪ ባረቀቁት ስምምነቱ መሰረት የካራባክ አርመን ኃይሎች ሙሉ በሙሉ ይበተናሉ እንዲሁም ትጥቅ ይፈታሉ።