"አባቴ ዶናልድ ትራምፕ መሞታቸውን ስገልፅ በታላቅ ሀዘን ነው" - የተጠለፈው የትራምፕ ልጅ ገፅ

የፎቶው ባለመብት, Getty Images
መረጃ ጠላፊዎች የትራምፕ ጁኒየር የኤክስ ገፅን ሰብረው ገብተው ፕሬዝደንት ዶናልድት ትራምፕ ሞተዋል የሚል መልዕክት አስፍረዋል።
ረቡዕ ዕለት የትራምፕ ልጅን የኤክስ ገፅ ሰብረው የገቡት ጠላፊዎች የተለያዩ መልዕክቶች ሲለጥፉ አምሽተዋል።
ከቀድሞው ትዊተር ከአሁኑ ኤክስ እንዲጠፉ የተደረጉት መልዕክቶች ዶናልድ ትራምፕ ሞተዋል ከሚል ፅሑፍ ባለፈ ፕሬዝደንት ባይደንን የሚዘልፍ መልዕክት አስፍረዋል።
ከአንድ ሰዓት ላነሰ ጊዜ የተጠለፈው የትራምፕ ጁኒየር የኤክስ ገፅ 10 ሚሊዮን ተከታዮች አሉት።
የትራምፕ ድርጅት የዶናልድ ልጅ ገፅ መጠለፉን ይፋ አድርጓል።
ከተለጠፉት መልዕክቶች አንዱ “አባቴ ዶናልድ ትራምፕ ከዚህች ዓለም በሞት መሰናበቱን ስናገር በታላቅ ሀዘን ነው። ለ2024 ምርጫ እኔ እወዳደራለሁ” ይላል።
ሌላኛው መልዕክት ደግሞ “ሰሜን ኮሪያን አመድ ልናደርጋት ነው” ይላል።
ጠላፊዎቹ በአንደኛው መልዕክታቸው በወሲባዊ ጥቃት የተወነጀለው ጄፍሪ ኤፕስታይንን የተመለከ ፅሑፍ ያዘለ ነው።
በክሪፕቶከረንሲ ማጭበርበር ተጠርጥሮ ክስ ሊቀርብበት እየተሰናዳ ስላለው ሪቻርድ ኸርት እና ስለዩቲዩበሩ ሎጋን ፖልም መልዕክት ሰፍሯል።
የትራምፕ ጁኒየር ገፅ የተጠለፈው በሃገሪቱ ሰዓት አቆጣጠር ከሰዓት 9፡00 ገደማ ነው።
ትሩዝ ሶሻል የተሰኘውን ማሕበራዊ ሚድያ የሚጠቀሙት ፕሬዝደንት ዶናልድ ትራምፕ የልጃቸው ገፅ በተጠለፈ ወቅት ሌላ ይዘት ያላቸው ፅሑፎች ሲለጥፉ ነበር።
“የዶን ገፅ ተጠልፏል” ሲል የትራምፕ ጁኒየር ቃል አቀባይ አንድሪው ሱራቢያን በኤክስ ገፁ አሳውቋል።
አክሎ “እንደምታውቁት እየተለጠፉ ያሉት መልዕክቶች ሐሰተኛ ናቸው” ብሏል።
ትራምፕ ጁኒየር ገፁን ከጠላፊዎቹ መልሶ ካገኘ በኋላ ስለገፁ መጠለፍ ምንም ባይልም ይህን ዜና ያሰማን አንድ ገፅ “ላይክ” አድርጓል።
ኤክስ ስለጉዳዩ ሐሳብ እንዲሰጥ ቢጠየቅም ከኩባንያው የመጣ ምላሽ “አሁንም ሥራ በዝቶብናል፤ እባክዎ ቆየት ብለው ያናግሩን” ይላል።
ትራምፕ ጁኒየር አሁንም የኢላን መስክ ንብረት የሆነው ኤክስን ይጠቀማል።
አባቱ ፕሬዝደንት ትራምፕ ግን በአውሮፓዉያኑ 2021 ግጭት አነሳስተዋል ተብለው ገፃቸው ከታገደ በኋላ ተጠቅመው አያውቁም።
ትራምፕ ገፃቸው ሲታገድ ነው ትሩዝ ሶሻል የተሰኘውን ማሕበራዊ ሚድያ አቋቁመው እሱን መጠቀም የጀመሩት።
ኤክስ ባለፈው ኅዳር በርካታ ሚሊዮን ተከታዮች ያሉት የፕሬዝደንት ትራምፕ ገፅን እግድ አንስቷል።
በ2022 ወርሃ ጥቅምት በ44 ቢሊዮን ዶላር ትዊተርን የገዛው ኢላን መስክ ስሙን ቀይሮ ኤክስ ብሎታል።












