የኖርዌይ ልዕልት ከጥቁር አሜሪካዊው ጋር በትዳር ልትጣመር ነው

የኖርዌይ ልዕልት ማርታ ሉዊስ እና ዱረክ ቬሬት

የፎቶው ባለመብት, Getty Images

የምስሉ መግለጫ, የኖርዌይ ልዕልት ማርታ ሉዊስ እና ዱረክ ቬሬት

የኖርዌይ ልዕልት ማርታ ሉዊስ ከጥቁር አሜሪካዊው ዱረክ ቬሬት ጋር ትዳር ልትመሰርት መሆኑን አስታወቀች።

የኖርዌይ ንጉሥ ሃራልድ አምስተኛ ጥንዶቹን እንኳን ደስ ያላችሁ ያሉ ሲሆን፣ ዱረክ ቬሬት እንደ ቤተሰብ አድርጌ ለመቀበል ደስተኛ ነኝ ብለዋል።

ከመደበኛ ሕክምና ይልቅ ሰዎች ጤናቸውን ለመጠበቅ የሕይወት ዘይቤያቸውን መቀየር አለባቸው በሚል አቋማቸው የሚታወቁት ጥንዶቹ፣ ከአንድ ዓመት በፊት በፍቅር ግንኙነት ውስጥ እንዳሉ ይፋ አድርገው ነበር።

ጥቁር አሜሪካዊው ዱረክ ቬሬት እንደ ካንሰር ያለ በሽታ ሰዎችን የሚይዘው፣ በሚመርጡት የሕይወት ዘይቤ የተነሳ ስለሆነ "ካንሰር ምርጫ ነው" በማለቱ ይታወቃል።

ቬሬት በሳይንስ ማረጋገጫ ያልተሳጣቸው የሕክምና መንገዶችን በማበረታታት የሚታወቅ ሲሆን፣ በኮቪድ-19 ወረርሽኝ ወቅት ሰዎችን ከወረርሽኙ ይከላከላሉ ያላቸውን አንገት ላይ የሚጠለቁ ጌጦች በኢንተርኔት አማካኝነት ሲሸጥ ነበር።

ቬሬት ከዚህም በላይ ከሞት የተነሳሁ ነኝ የሚል ሲሆን፣ በአሜሪካ በሁለቱ መንትያ ሕንጻዎች ላይ በእአአ 9/11 የደረሰው የሽብር ጥቃት ቀድሞ ተንብዮ እንደነበረ ይናገራል።

ጥቁር አሜሪካዊው ቬሬት በዚህ አመለካከቱ በርካታ ትችቶች ይደርሱበታል። ቬሬት ግን ትችቶቹ የሚሰነዘሩብኝ በቆዳ ቀለሜ ምክንያት ነው በማለት ይከራከራል።

ልዕልት ማርታ ሉዊስም ብትሆን እንዲሁ አወዛጋቢ በሆኑ ንግግሮቿ ትታወቃለች። ልዕልቷ በአንድ ወቅት ከመላዕክት ጋር መነጋገር እችላለሁ ብላ ነበር።

ሁለቱ ጥንዶች ሠርጋቸውን በተባበሩት መንግሥታት የትምህርት፣ ሳይንስ እና ባሕል ድርጅት (ዩኔስኮ) የዓለም ቅርስ ተብሎ በተመዘገበው ውብ መልካዓ ምድር ባለው ጌአራንጋር ከተማ ይፈጸማሉ።

“ሠርጋችንን በውቧ ጌአራንጋር ከተማ ማድረጋችን ከፍተኛ ደስታን ይፈጥርልናል። እጅግ ታሪካዊ እና ውብ በሆነው ስፍራ ወዳጅ ዘመዶቻችንን በአንድ ቦታ መሰብሰብ መቻላችን ለእኛ ትልቅ ነገር ነው” ብለዋል ጥንዶቹ በጋራ ባወጡት መግለጫ።

የኖርዌይ ንጉሥ እና ንግሥት በተመሳሳይ ባወጡት የጋራ መግለጫ፣ በጥንዶቹ መጋባት ደስታ እንደተሰማቸው አስታውቀዋል።

ቬሬት ከልዕልቷ ጋር ትዳር ከመሰረተ በኋላ ኑሮውን ጠቅልሎ ኖርዌይ እንደሚያደርግ ተዘግቧል።

ቬሬት ከልዕልቷ ጋር በትዳር ይጣመር እንጂ፣ በንጉሥውያን ቤተሰብ ውስጥ የማዕረግ ስም እንደማይሰጠው የኖርዌይ ብሔራዊ ቴሌቪዥን ጣቢያ ዘግቧል።

የ51 ዓመቷ ልዕልት ማርታ ከዚህ ቀደም፣ አሪ ቤን ከተባለ ጸሐፊ ጋር ትዳር መስርታ ነበር።

ይሁን እንጂ ይህ ትዳራቸው እአአ 2017 ላይ ከፈረሰ በኋላ አሪ ቤን ከፍተኛ ድባቴ ውስጥ ገብቶ እአአ 2019 ማብቂያ የገና በዓል ዕለት ራሱን አጥፍቷል።

ልዕልት ማርታ ምንም እንኳ የንጉሥ ሃራልድ የመጀመሪያ ልጅ ብትሆንም እራሷን ከንጉሥውያን ቤተሰቦች ኃላፊነቶች በማግለሏ ንጉሥ ሃራልድን የሚተካው ታናሽ ወንድሟ ልዑል አልጋ ወራሽ ሃኮን ይሆናል።