የቲቪ ቀጥታ ሥርጭት እያስተላለፈች ያለች ጋዜጠኛ ላይ ወሲባዊ ትንኮሳ አድርሷል የተባለው ስፔናዊ ታሰረ

ኢሳ ባላዶ

የፎቶው ባለመብት, CUATRO

የምስሉ መግለጫ, ኢሳ ክስተቱ ሲፈፀም ማድሪድ ስለተከሰተ ዘረፋ የቀጥታ ሥርጭት ዘገባ እየሠራች ነበር

የስፔን ፖሊስ በቴሌቪዥን የቀጥታ ሥርጭት እያስተላለፈች ያለችኝ ጋዜጠኛ ላይ ወሲባዊ ጥቃት አድርሷል ያለውን ግለሰብ በቁጥጥር ሥር አውሏል።

ኢሳ ባላዶ ማክሰኞ ዕለት በማድሪድ ከተማ የተከተሰተን አንድ ዘረፋ በተለመከተ የቀጥታ ዘገባ እየሠራች ነበር።

በዚህ መሐል አንድ ግለሰብ ወደ ጋዜጠኛዋ አቅንቶ መቀመጫዋን ሲነካካ የተስተዋለ ሲሆን ኢሳ ግለሰቡን ስትጋፈጠው ድርጊቱን ክዷል።

ኢሳ የቀጥታ ሥርጭቷን ብትቀጥልም ስቱዲዮ የነበሩት የፕሮግራም አቅራቢዎች ሥርጭቱ እንዲቋረጥ አድርገዋል።

“ኢሳ ይቅርታ አድርጊልኛና ይህ ግለሰብ መቀመጫሽን ሲነካው አየው ልበል?” ሲል የፕሮግራሙ አቅራቢ ናቾ አባድ ጠይቋል።

ኢሳ “አዎ” የሚል ምልክት ስትሰጥ አቅራቢው ይህን “ደደብ” ካሜራ ላይ አቅርቢው ይላል።

ይሄኔ ነው ካሜራው ወደ ግለሰቡ ፊቱን ያዞረው። ግለሰቡ እንዲያም ሆኖ ከጋዜጠኛዋ አጠገብ ቆሞ ፈገግ ሲል ይታያል።

“የፈለገ ከየትኛዋ ጣቢያ እንደሆንን መጠየቅ ብትሻ መቀመጫየን መንካት ነበረብህ? የቀጥታ ሥርጭት እየሠራሁ ነው፤ ሥራ ላይ ነኝ” ስትል ኢሳ ጠይቃዋለች።

ግለሰቡ ግን ድርጊቱን አልፈፀምኩም ሲል ያስተባበለ ሲሆን ከካሜራው እየራቀ ሲሄድ ጭንቅላቷን ለመንካት ሲጥር ይታያል።

ፖሊስ ከዚህ ድርጊት በኋላ የቀጥታ ሥርጭት ላይ የነበረችው ጋዜጠኛ ላይ ወሲባዊ ጥቃት በማድረስ ጠርጥሬዋለሁ ያለውን ሰው በቁጥጥር ሥር ማዋሉን ገልጧል።

የስፔን ፖሊስ ግለሰቡ በቁጥጥር ሥር ማዋሉን ኤክስ [የቀድሞው ትዊተር] ላይ በለፈጠው ቪድዮ አረጋግጧል።

የዜና ጣቢያው ባለቤት የሆነው ሚድያሴት ኢስፓና ለኢሳ ያለውን ድጋፍ በመግለጫ አስደግፎ አሳውቋል።

ድርጅቱ ጋዜጠኛዋ “በፍፁም ልንታገሰው የማይገባ ድርጊት” ሰለባ ሆናለች “ማንኛውንም ዓይነት ትንኮሳ እና ጥሰት አንቀበልም” ብሏል።

የስፔን የሰው ኃይል ሚኒስትር ዮላንዳ ድርጊቱን የፈፀመው ግለሰብ ተገቢውን ቅጣት ሊከናነብ ይገባል ብለዋል።

ሚኒስትሯ፤ “ይህ ግልብተኛ የጡንቸኞች ባሕሪ ነው ጋዜጠኞች ለመሰል ትንኮሳዎች እንዲጋለጡ እያደረገ ያለው፤ እኒህ ጥሰት ፈፃሚዎች ካሜራ ላይ ታይተው እንኳ አያፍሩም” ሲሉ ሐሳባቸውን ኤክስ ላይ አስፍረዋል።

የስፔን እግር ኳስ ፌዴሬሽን ፕሬዝደንት የብሔራዊ ቡድን ተጫዋች የሆነችው ጄኒ ሄርሞሶን ከንፈሯ ላይ መሳማቸው ትልቅ መነጋገሪያ እንደነበር ይታወሳል።

ፕሬዝደንቱ በሴቶች ዓለም ዋንጫ ፍፃሜ ወቅት ያሳዩት ተግባር ታላቅ ነቀፌት ያስከተለባቸው ሲሆን፤ ከሥልጣናቸው እንዲወርዱና ፍርድ ቤት ቀርበው ቃላቸውን እንዲሰጡም ሆነዋል።