ኢትዮጵያዊው ሕገ-ወጥ ሰው አዘዋዋሪ በኬንያ የ31 ዓመት እስር ተፈረደበት

የፎቶው ባለመብት, Getty Images
በኬንያ በሕገ-ወጥ የሰዎች ዝውውር ተጠርጥሮ በቁጥጥር ስር ውሎ የነበረው ኢትዮጵያዊ 31 ዓመታትን በእስር እንዲያሳልፍ በናይሮቢ የሚገኝ ፍርድ ቤት ብይን መስጠቱን የአገሪቱ መገናኛ ብዙሃን ዘግበዋል።
ይበቃል ጌታቸው የተባለው ግለሰብ ከሁለት ዓመታት በፊት በቁጥጥር ስር ከዋለ በኋላ በመኖሪያ ቤቱ እጃቸው በሰንሰለት የታሰሩ 12 ስደተኛ ኢትዮጵያውያን ተገኝተው ነበር።
ፖሊስ አዲናን ሞሐመድ ጋላኖ በሚል ተጨማሪ ስም በሚታወቀው ይበቃል ጌታቸው መኖሪያ ቤት በአንድ ጠባብ ክፍል ውስጥ ታጉረው የተገኙት ስደተኞች ወደ ሦስተኛ አገር እስኪዘዋወሩ እየተጠባበቁ ነበር ብሏል።
ዘ ስታር የተሰኘው ጋዜጣ ይበቃል ጌታቸው ጥቅምት 24/2014 ዓ.ም. በናይሮቢ ንጎማ ተብሎ በሚጠራ ስፍራ በቁጥጥር ሥር መዋሉን አስታውሶ ግለሰቡ ከሕገ-ወጥ የሰዎች ዝውውር በተጨማሪ በሰንድ ማጭበርበር ተጨማሪ የአንድ ዓመት እስር ተላልፎበታል።
እንደ ጋዜጣው ከሆነ ይበቃል ጌታቸው የኬንያ መንግሥት ለውጭ አገር ዜጎች የሚሰጠውን ሐሰተኛ መታወቂያ ይዞ ሲንቀሳቀስ ነበር።
ጥፋተኛ ተብሎ በተፈረደበት ግለሰብ መኖሪያ ቤት ውስጥ የተገኙት ኢትዮጵያውያን ወደ ትውልድ አገራቸው እንዲመለሱ መደረጉም ተዘግቧል።
የኬንያ የወንጀል ምርመራ ዳይሬክተር የሆኑት ሞሐመድ አሚን መዳረሻቸውን ደቡብ አፍሪካ እና መካከለኛው ምስራቅ ማድረግ የሚፈልጉ ኢትዮጵያውያን ኬንያን መሸጋገሪያ እያደረጉ መሆኑን ጠቅሰው በግለሰቡ ላይ የተላለፈው ብይን ሌሎች ሕገ-ወጥ አዘዋዋሪዎች ከመሰል ተግባራቸው እንዲቆጠቡ የሚያሳስብ ነው ስለማለታቸው ደግሞ የዘገበው ናይሮቢ ኒውስ ነው።
የፖሊስ አለቃው ከቅርብ ግዜ ወዲህ ከፍተኛ ቁጥር ያላቸው ሰነድ አልባ የሆኑ ስደተኞች ኬንያን እንደ መሸጋገሪያ እየተጠቀሙ መሆኑን በማስታወስ ሕብረተሰቡ አጠራጣሪ ሁኔታ ሲመለከት ለፖሊስ ጥቆማ እንዲሰጥ ጠይቀዋል።
ይህ በእንዲህ እንዳለ በኬንያ መዲና ናይሮቢ ኢስሊ ተብሎ በሚጠራ አካባቢ ፖሊስ 30 ሰነድ አልባ ስደተኞችን በቁጥጥር ስር ስለማዋሉ ሪፖርት ተደርጓል።
20 ወንዶች እና 10 ሴቶች መዳረሻቸው እስካሁን ወዳልተገለጸ ቦታ ሊዘዋወሩ ሲሉ እንደተያዙ የኬንያን ፖሊስ ዋቢ አድርጎ ስታንዳርድ የተባለው ጋዜጣ ዘግቧል።
ከአንድ ወር በፊት ደግሞ በማቻኮስ ግዛት አቲ ሪቨር ተብሎ በሚጠራ አካባቢ በሕገ-ወጥ መልኩ ኬንያ የገቡ ኢትዮጵያውያን በቁጥጥር ሥር ውለው ነበር።












