በሊቢያ በጎርፍ አደጋ የሞቱ ሰዎች በጅምላ መቃብር እየተቀበሩ ነው

የፎቶው ባለመብት, REUTERS
በምሥራቃዊ ሊቢያ ደርና በምትባለው የወደብ ከተማ በደረሰው አስከፊ የጎርፍ አደጋ ሳቢያ የሞቱ ሰዎች አስክሬን በጅምላ መቃብር እየተቀበሩ ነው።
ቢያንስ 2 ሺህ 300 ሰዎች በሱናሚ መሰሉ ጎርፍ ሕይወታውን አጥተዋል። 10,000 የደረሱበት ያልታወቀ ሲሆን፣ የሟቾች ቁጥር ሊጨምር እንደሚችልም ተሰግቷል።
በደርና ግዛት የበጎ ፈቃድ አገልግሎት የሚሰጠው መሐመድ ቃማቲ አሁንም አስክሬን እየፈለጉ እንደሚገኙ ገልጿል።
“ወጣት ሊቢያውያንና የሕክምና ባለሙያዎች እንዲረዱን እንማጸናለን” ብሏል።
ከግብፅና ሌሎችም አገራት እርዳታ እየተላከ ነው።
አሜሪካ፣ ጀርመን፣ ኢራን፣ ጣልያን፣ ኳታርና ቱርክም እርዳታ ከሰጡ አገራት መካከል ናቸው።
የውሃ ምኅንድስና ባለሙያዎች ለቢቢሲ እንደገለጹት፣ 12 ኪሎ ሜትር ግድብ ከፈረሰ በኋላ ውሃው ከተማውን አጥለቅልቋል።
እሑድ የወጣ ቪድዮ እንደሚያሳየው ውሃው በደርና ውስጥ ሲፈስ ነበር። በከተማው 100,000 ያህል ሰዎች ይኖራሉ።
መኪኖች በጎርፉ ተንሳፈውም ነበር። ነዋሪዎች በጭቃ ውስጥ ሆነውም ታይቷል።
ሰዎች ወደ ባሕር በውሃው ተገፍተው ሲወሰዱ የታየበትም ቪድዮ አለ።
በሊቢያ ምሥራቃዊ አስተዳደር የሚሠሩት ሒሻም ቺኮት “ባየሁት ነገር ደንጋጫለሁ። ሱናሚ ነው የሚመስለው” ብለዋል።
የሊቢያ ጤና ሚኒስትር ኦትማን አብዱልጃላል ለአሶሽየትድ ፕረስ እንደተናገሩት፣ በደረሰው ጉዳት ተደናግጠዋል።
“ጉዳቱ ከደርና መንግሥት አቅም በላይ ነው” ብለዋል።
ሶሳ፣ አል ማራጅ እና ሚስራታ የተባሉት ከተሞችም ተጎድተዋል።
በ2011 ጋዳፊ ከሥልጣን ወርደው ከተገደሉ በኋላ ሊቢያ ቀውስ ውስጥ ነው የምትገኘው።
ከትሪፖሊ የሚመራው መንግሥት ዓለም አቀፍ ዕውቅና ሲሰጠው፣ ሊቢያን ከምሥራቅ ግዛት የሚያስተዳድረው ኃይል ደግሞ ተገዳዳሪ ነው።
ልዩነቱ እንዳለ ሆኖ የትሪፖሊው መንግሥት 14 ቶን መድኃኒት፣ አስክሬን መጠቅለያ ላስቲክ እንዲሁም 80 የሕክምና ባለሙያዎችን ልኳል።
ከጋዳፊ መውደቅ በኋላ ከተማዋ የኢስላሚክ ስቴት ታጣቂዎች ወደ ሊቢያ የገቡ ስትሆን፣ ከተወሰኑ ዓመታት በኋላ የጀነራል ካሊፋ ሀፍጣር ወታደሮች አስወጥተዋቸዋል።
ጀነራሉ እንደገለጹት በጎርፉ የደረሰውን ጉዳት መዝነው መንገድ መልሶ ለመገንባትና መብራት ለመዘርጋት ጥረት ይደረጋል።












