አሜሪካ ዜጎቿን ነጻ ለማውጣት ስትል የኢራን 6 ቢሊዮን ዶላር እንዲለቀቅ ፈቀደች

የፎቶው ባለመብት, EPA
አሜሪካ በኢራን በእስር ላይ የሚገኙ አምስት ዜጎቿን ነጻ ለማውጣት ስትል እንዳይንቀሳቀስ ተደርጎ የነበረው የኢራን 6 ቢሊዮን ዶላር እንዲለቀቅ ተስማማች።
የአሜሪካ የውጭ ጉዳይ ሚንስትር አንቶኒ ብሊንከን በአሜሪካ ማዕቀብ ምክንያት በደቡብ ኮሪያ ተይዞ የነበረው የኢራን ገንዘብ ወደ ኳታር ማዕከላዊ ባንክ እንዲተላለፍ ማዕቀብ ለማንሳት መስማማቷን ለኮንግረሱ ተናግረዋል።
አሜሪካ አምስቱን ግለሰቦች ነጻ ለማውጣት ገንዘቡ እንዲለቀቅ ከመፍቀዷም በተጨማሪ በአሜሪካ በእስር ላይ የነበሩ አምስት ኢራናውያንን ለመልቀቅ ተስማምታለች።
ይህን የፕሬዝዳንት ጆ ባይደን አስተዳደር ውሳኔን ተቃዋሚዎቹ ሪፓብሊካኖች ተችተዋል።
አንድ የአሜሪካ የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት አባል የባይደን አስተዳደር “በዓለም ላይ ሽብር በመደገፍ ለሚታወቅ መንግሥት የእገታ ማስለቀቂያ ገንዘብ እየሰጠ ነው” ሲሉ ውሳኔውን ተችተዋል።
ብሊንከን ኢራን ከዚህ ገንዘብ የምታገኘው ጥቅም የተገደበ ነው ይላሉ። እንደ ብሊንከን ገለጻ ከሆነ ኢራን ወደ ኳታር ማዕከላዊ ባንክ የሚገባውን ገንዘብ መጠቀም የምትችለው የሰብዓዊ እርዳታ አቅርቦት ወጪዎችን ለመሸፈን ብቻ ይሆናል።
የውጭ ጉዳይ ሚንስትሩ ኢራን ይህን ገንዘብ በቀጥታ ወጪ ማድረግ እንደማትችል እና አሜሪካም በገንዘቡ ላይ ቁጥጥር እንደምታደርግ ለኮንግረሱ አብራርተዋል።
ኢራን በመላው ዓለም ከነዳጅ ሽያጭ ማግኘት የነበረባትን ገንዘብ ሳትሰበስብ እአአ 2018 ላይ የቀድሞ ፕሬዝዳንት ዶናልድ ትራምፕ ምዕራባውያኑ ከኢራን ጋር ደርሰውት የነበረውን የኒውክለር ስምምነት ጥለው መውጣታቸው ተከትሎ በቢሊዮን ዶላር የሚገመት ገንዘብ ሳይከፈላት ቀርቷል።
የአሜሪካ መንግሥት ጥሎት የነበረውን ማዕቀብ ማንሳቱ በአውሮፓ፣ ኢሲያ እና መካከለኛው ምስራቅ የሚገኙ ባንኮች የኢራንን ገንዘብ ወደ ኳታር ማዕካለዊ ባንክ እንዲያዘዋውሩ ይፈቅድላቸዋል ማለት ነው።
ሪፓብሊካኖቹ ግን አምስት ዜጎችን ለማስፈታት ይህ ገንዘብ ለኢራን ኢንዲለቀቅ ማድረግ ጨርሶ እንደ አማራጭ መቅረብ አልነበረበትም ይላሉ።
የሪፓብሊካን የምክር ቤቱ የውጭ ጉዳይ ኮሚቴ አባል ማይክል ማክኮውል አሜሪካውያኑ ምንም ወንጀል ሳይፈጽሙ በኢራን ታፍነው የተያዙ በመሆናቸው በአስቸኳይ መለቀቅ ይኖርባቸዋል እንጂ የማስለቀቂያ ገንዘብ ለኢራን መከፈል የለበትም ብለዋል።
ይህ በእንዲህ እንዳለ የኢራን የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ቃል አቀባይ ናስር ካናኒ የእስረኞች ልውውጡ በአጭር ግዜ እንደሚፈጸም ባለሙሉ ተስፋ ነን ብለዋል።












