የሰሜን ኮሪያው መሪ ወደ ሩሲያ በአውሮፕላን መሄድ የፈሩት ለምንድነው?

የፎቶው ባለመብት, KOREA SUMMIT PRESS POOL
የሰሜን ኮሪያው ኪም ጆንግ ኡን ወደ ሩሲያዋ ቭላዲቮስቶክ የወደብ ከተማ ፑቲንን ለማግኘት እየተጓዙ ነው።
እርሳቸው የተሳፈሩበት ‘የጦር ባቡር’ ከ20 በላይ ጥይት የማይበሳቸው መኪናዎች ተጭነውበት ጉዞው አዝጋሚ ሆኗል።
ይህ ኪም የተሳፈሩበት ባቡር ራሱ ጥይት አይበሳውም። ልዩ ልዩ ዘመናዊ የቅኝት መሣሪያዎችም ተገጥመውለታል።
የሰሜን ኮሪያ መሪዎች ለጉዞ ለምን ባቡር እንደሚመርጡ ግልጽ አይደለም። ምናልባት ከደኅንነት አንጻር ሊሆን እንደሚችል ግን ይገመታል።
አሁን ኪም ጆንግ ኡንን ያሳፈረው ባቡር ከፒዯንጊያንግ ሩሲያ ለመግባት 20 ሰዓታት ይወስድበታል። ይህ ዘገባ ሲጠናቀር ጉዞውን አጋምሰውታል።
ጠቅላላ ርቀቱ 1180 ኪሎ ሜትር ነው። ባቡሩ ደግሞ ቀሰስተኛ ነው።
በሰዓት 50 ኪሎ ሜትር ነው የሚጓዘው።
ይህ ከለንደን ፈጣን ባቡር ሲነጻጸር በጣም ቀርፋፋ ነው።
የለንደን ባቡር በሰዓት 200 ኪሎ ሜትር ይበራል። የጃፓን ሺንካንሰን ማግኔቲክ ባቡር ደግሞ በሰዓት 320 ኪሎ ሜትር ይከንፋል።
የኪም ባቡር ቀሰስተኛ ይሁን እንጂ ራሱን የቻለ ተንቀሳቃሽ ቤተ መንግሥት ነው ቢባል ይቀላል።
ውድ የፈረንሳይ ወይን መጠጦች፣ ዘመናዊ መጸዳጃ ቤቶች፣ ሬስቶራንቶች፣ የስብሰባ አዳራሽ፣ ባር ወዘተ አሉት።
ይህ ልዩ የጦር ባቡር ስሙ ታይያንጎ ነው። በኮሪያ ቋንቋ ‘ፀሐዩ’ እንደማለት ነው። የኮሪያን አባት ኪም ኢል ሱንግን ለማስታወስ ነው ፀሐዩ የተባለው። የኪምን አያት ማለት ነው።

የፎቶው ባለመብት, GETTY IMAGES
የኪም አያት ኢል ሱንግም እንዲሁ በባቡር ረዥም ርቀት ይሄዱ ነበር።
እርሳቸው እንዲያውም ቅርብ ሩሲያ ብቻ ሳይሆን እስከ ቬትናም አንዳንዴም እስከ ምሥራቅ አውሮፓ በባቡራቸው ነበር የሚጓዙት።
የሚጓዙባቸው ባቡሮች በከፍተኛ ሁኔታ በደኅንነት ሰዎች ጥብቅና ጥልቅ ፍተሻ ይደረግላቸዋል።
በጉዞው ላይ ተቀጣጣይ ፈንጂ እንዳይኖር ቀድሞ ሐዲድ መስመሩ ላይ ጽዳት ይደረግ ነበር።
የኪም ጁንግ ኡን አባት ኪም ጆንግ ኢል ሰሜን ኮሪያን እንደ አውሮፓዊያኑ ከ1994 እስከሞቱበት 2011 ድረስ መርተዋታል።
በዚህ ሁሉ ዘመን ግን አንድም ቀን በአውሮፕላን ሄደው አያውቁም።
ይህን ሁሉ ዘመን በመኪናና በባቡር ተጉዞው ነው የሞቱት።
ኪም ጆንግ ኢል በ2001 ዓ/ም ረዥም ጉዞ ማለትም 10 ቀናትን በባቡር ተጉዘው ፑቲንን አግኝተው ያውቃሉ።
በዚያ ዘመን ኪም ጆንግ ኢልን በጉዞው አጅበዋቸው የነበሩት የሩሲያ ኮማንደር ፑሊኮቭስኪ ማስታወሻ መጽሐፍ ጽፈዋል።
ትዝታቸውን ሲያወጉ ‘በዚያ ባቡር ውስጥ ማንኛውንም ምግብ ማዘዝ ይቻላል። ለምሳሌ የሩሲያ፣ የቻይና፣ የኮሪያ የጃፓን የፈረንሳይ ምግቦች ተሟልተው ይገኙ ነበር።’ ብለዋል።
ከፓሪስ ልዩ ልዩ ወይኖች እንዲሁም ትኩስ ሎብስተር በባቡሩ ውስጥ ለእንግዶች ይቀርባል።
እኚህ ኮማንደር፣ ‘እንዲህ ዓይነት ምቾት በፑቲን የግል ባቡር ውስጥ እንኳ አይገኝም’ ሲሉ ጽፈዋል።
ሌላው የሩሲያ ዲፕሎማት ጂዯርጂ ቶሎራያ በ2019 ይህን የኪምን አባት የ10 ቀናት ረዥም የባቡር ጉዞ ሲያስታዉሱ፣ ‘ጣፋጭ የአህያ ስጋ ይቀርብ እንደነበረ ትዝ የለኛል’ ብለዋል።
የሚገርመው ኪም ጆንግ ኢል የሞቱት በሚወዱት ባቡር እየተጓዙ በልብ ድካም ነው።
ይህ የነ ኪም ልዩ ወታደራዊ ባቡር 90 የሚሆኑ ፎርጉዎች አሉት። የስብሰባ ማዕከል፣ ምቹ መኝታ ክፍሎች፣ ሳተላይት ቴሌቪዥን መመልከቻዎችም ተገጥመውለታል።
ኪም ጆንግ ኡንን ለጊዜው አንተ እንበለውና እንደ አባቱ በአውሮፕላን መብረር የሚፈራ ሰው አይደለም።
ሩሲያ ሰራሽ በሆነው የግል ጄቱ ከዚህ ቀደም በተደጋጋሚ በሯል። ሆኖም እንደ አያቱና አባቱ ባቡርን ይመርጣል።
አሁን ወደ ሩሲያ እያቀናበት ያለው የኪም ጆንግ ኡን ልዩ የጦር ባቡር ፒንክ የሌዘር ሶፋዎች ያሉት ሲሆን 21 ፉርጎዎች ይከተሉታል።
ኪም ጆንግ ኡን የተማረው በስዊዘርላንድ አዳሪ ትምህርት ቤት ነው።በአውሮፕላን በተደጋጋሚ ተጉዟል። ከሥልጣን በኋላ ለመጀመርያ ጊዜ በአውሮፕላን የተጓዘው ደግሞ ወደ ቻይና ነበር።
በመጋቢት 2018 ቻይና ቤጂንግ ተጉዞ ነበር በባቡር። ሆኖም ከባቡር ሲወርድ የተቀበሉት ዝነኛዎቹ መርሰዲስ ኤስ ተሽከርካሪዎች ናቸው።
እነዚህ መኪናዎች ኪም በየትኛው አገር ሲጓዙ ተጭነው ይወሰዳሉ።
እያንዳንዳቸው 1.8 ሚሊዯን ዶላር የሚያወጡ ቅንጡ መኪናዎች ናቸው።
ኪም እነዚህ መኪናዎች ውስጥ ሲሳፈር አጃቢዎቹ በሶምሶማ ግራና ቀኝ ሆነው ይሮጣሉ።አሯሯጣቸው ደግሞ ዜማ አለው። አይዛነፍም።
እነዚህ የኪም ብቻ የሆኑት መርሰዲስ ኤስ ተሽከርካሪዎች ቅንጡ መጸዳጃ ቤቶች የተገጠሙላቸው ናቸው።
ኪም ዛሬ ወይም ነገ 20 ሰዓታትን ከፈጀ የባቡር ጉዞ በኋላ ፑቲንን አግኝቶ በጦር መሣሪያ ዙርያ ያወጋል።
ምዕራቡ ዓለም የፑቲንን የኪምን ግንኙነት ትንፋሹን ውጡ እየተከታተለ ነው።
ሩሲያ ኪም ለሚያርብላት የጦር መሣሪያ ከገንዘብ ባሻገር የኑክሊየር እውቀት ሽግግር ለማድረግ እንዳትስማማ ነው ፍርሃቱ።












