በሊቢያ ባጋጠመው የጎርፍ አደጋ ከአንድ ከተማ ብቻ የ1ሺህ ሰዎች አስክሬን ተነሳ

የፎቶው ባለመብት, Getty Images
በሊቢያ ባጋጠመ የጎርፍ አደጋ በምስራቅ የአገሪቱ ክፍል ከምትገኘው ደርና ከተማ ብቻ የሟቾች ቁጥር ከ1ሺህ በላይ መሆኑን አካባቢውን የጎበኙ ከፍተኛ ባለስልጣን አስታወቁ።
“የሰዎች አስክሬን በየቦታው ወድቆ ይገኛል” ብለዋል መቀመጫውን ምስራቃዊ ሊቢያ ያደረገው መንግሥት ሚንስትር።
100ሺህ ነዋሪ ባላት ደርና ከተማ ውስጥ የነበሩ ሁለት ግድቦች እና አራት ድልድዮች ከተደረመሱ በኋላ ከተማዋ ሙሉ ለሙሉ ሊባል በሚችል መልኩ በውሃ ተውጣለች።
የቀይ መስቀል ማኅበር በወደብ ከተማዋ ደርና እስካሁን ድረስ 10ሺህ ነዋሪ የገቡበት አለመታወቁ ሪፖርት ተደርጓል ብሏል።
እሁድ ዕለት የዘነበው ከፍተኛ ዝናብ ቤንጋዚ፣ ሶውሳ እና አል-ማርጅ ከተሞችን ጨምሮ በምስራቅ ሊቢያ ከፍተኛ ጉዳት አስከትሏል።
“እስካሁን የ1ሺህ ሰዎች አስክሬን ተነስቷል። የከተማዋ ሩብ ክፍል ሙሉ በሙሉ ጠፍቷል ብል ማጋነን አይሆንም። በጣም ብዙ ብዙ ሕንጻዎች ፈርሰዋል” ብለዋል የአቪዬሽን ሚንስትሩ እና የአስቿኳይ ድጋፍ አስተባባሪ ኮሚቴ አባሉ ሂቼም ቻኪኦት።
በሊቢያ የቀይ መስቀል ኃላፊ የሆኑት ታሚር ራማዳን በጎርፍ አደጋው ምክንያት የሟቾች ቁጥር እጅግ ከፍተኛ ሊሆን እንደሚችል ለጋዜጠኞች ተናግረዋል።
ኃላፊው ከጎረቤት አገር ቱኒዚያ ሆነው፤ “የሥራ ባልደረቦቻችን ተጎጂዎችን ለመርዳታ የተቻላቸውን ሁሉ እያደረጉ ነው። አሁን የሟቾችን ቁጥር በተመለከተ ትክክለኛው አሃዝ የለንም። እስካሁን ድረስ ግን አድራሻቸው የጠፉ ሰዎች ቁጥር ከ10ሺህ ተሻግሯል” ብለዋል።
ቀደም ሲል በመቀመጫውን ምስራቅ ሊቢያ ያደረገው መንግሥት ጠቅላይ ሚንስትር የሆኑት ኦሳማ ሃማደ ለአንድ የአካባቢው የቴሌቪዥን ጣቢያ ሲናገሩ የሟቾች ቁጥር ከ2ሺህ በላይ ሆኗል ብለው ነበር።
“የደርና እና የአካባቢው ነዋሪዎች በጎርፍ ተወስደዋል” ብለዋል።
በዚህ የጎርፍ አደጋ ከምስራቅ ሊቢያ ከተሞች በተጨማሪ በምዕራብ ሊቢያ የምትገኘው ሚስራታ ከተማም በጎርፍ አደጋው ጉዳት ደርሶባታል።
የሊቢያ የረዥም ጊዜ መሪ ሙዓመር ጋዳፊ ከስልጣን ከተወገዱ በኋላ አገሪቷ በተለያዩ መንግሥታት እየተመራች ትገኛለች። የአገሪቱ ምስራቅ ከፍል በጦር ጀነራሉ ካሊፍ ሃፍታር ቁጥጥር ስር የሚገኝ ሲሆን ዓለም አቀፍ እውቅና ያለው መንግሥት ደግሞ መቀመጫውን በመዲናዋ ትሪፖሊ አድርጎ ይገኛል።
አቡበከር አሳድ የተባለ ሊቢያዊ ጋዜጠኛ እንደሚለው ከሆነ ባለስልጣናት ለአደጋው ፈጣን ምላሽ እየሰጡ ባለመሆኑ የተጎጂዎች ቁጥር ሊጨምር ይችላል።
“የአደጋ ጊዜ ሠራተኞች የሉም። በሊቢያ የሰለጠኑ የአደጋ ጊዜ ሠራተኞችን ማግኘት አይቻልም። ባለፉት 12 ዓመታት በሊቢያ የነበረው ጦርነት ብቻ ነበር። ሁለት መንግሥታት ናቸው በሊቢያ ያሉት በዚህ ምክንያት ወደ አገሪቱ የሚመጡ እርዳታዎችንም እያዘገየ ነው ያለው” በማለት ለቢቢሲ ተናግሯል።
አሜሪካ፣ ግብጽ፣ ጀርመን፣ ኢራን፣ ጣሊያን፣ ኳታር እና ቱርክ ድጋፍ ለማድረግ ዝግጁ ነን ካሉ አገራት መካከል ይገኙበታል።












