ቭላድሚር ፑቲን እና ኪም ጆንግ ኡን ሳተላይት በጦር መሳሪያ ሊቀያየሩ ነው ተባለ

ኪም እና ፑቲን

የፎቶው ባለመብት, Getty Images

የሩሲያ ፕሬዝዳንት ቭላድሚር ፑቲን ከሰሜን ኮሪያው አቻቸው ኪም ጆንግ ኡን ጋር በተገናኙበት ወቅት ሞስኮ ሳተላይቶችን ለፒዮንግያግ እንደምትሰጥ ቃል ገቡ።

ኪም ጆንግ ኡን ወደ ሩሲያ አቅንተው በምስራቅ ሩሲያ በሚገኘው ቮስቶቺነይ ኮስሞደድሮም የጠፈር ምርምር ማዕከል ከቭላድሚር ፑቲን ጋር ከእአአ 2019 ወዲህ ለመጀመሪያ ግዜ በአካል ተገናኝተዋል።

ፑቲን የሰሜን ኮሪያው መሪ የአገራቸውን የጠፈር ምርመር ፕሮግራም የማሳደግ ፍላጎት እንዳላቸው ገልጸው ሩሲያ ሳተላይቶችን ለሰሜን ኮሪያ ለማቅረብ ዝግጁ መሆኗን ተናግረዋል።

ፑቲን በንግግራቸው ሞስኮ ለፒዮንግያንግ ምን አይነት ሳተላይቶችን እንምትሰጥ ያሉት ነገር ባይኖርም ሳተላይቶቹ የደኅንነት ቅኝት የሚያደርጉ ሊሆኑ እንደሚችሉ የብዙዎች ግምት ነው።

ሰሜን ኮሪያ ከዚህ ቀደም ሁለት የስለላ ስራ የሚሰሩ ሳተላይቶችን ለማምጠቅ ያደረገችው ጥረት ሳይሳካ ቀርቷል።

በተቃራኒው ሩሲያ በዩክሬን እያደረገች ባለችው ጦርነት ግብዓት የሚሆናትን የጦር መሳሪያ ከሰሜን ኮሪያ ልትቀበል እንደምትችል የዘርፉ ባለሙያዎች ይገልጻሉ።

መቀመጫውን ደቡብ ኮሪያ ያደረገው የኖርዝ ኮሪያን ስተዲስ ዩኒቨርሲቲ መምህር የሆኑት ፕሮፌሰር ኪም ጎንግ-ዩፕ ጥይቶች፣ ሞስኮ የከባድ መሳሪያ ተተኳሾች እንዲሁም የሶቪዬት ኅብረት ስሪት የሆኑ ሚሳኤሎችን እና ሮኬቶችን ከፒዮንግያንግ ልትቀበል ትችላለች ብለዋል።

እአአ 1953 ካበቃው የሁለቱ ኮሪያዎች ጦርነት በኋላ በምንም አይነት ጦርነት ተሳትፋ የማታውቀው ሰሜን ኮሪያ በሚሊዮኖች የሚገመት የሮኬቶች እና ተተኳሾች ክምችት እንዳላት ይገመታል።

ፕሮፌሰር ኪም ጎንግ-ዩፕ እንደሚሉት ሰሜን ኮሪያ ከዚህ የጦር መሳሪያ ክምችቷ ለሩሲያ የተወሰነውን አንስታ ብትሰጥ በወታደራዊ አቅሟ ላይ ልዩነት አይፈጥርም ይላሉ።

ፕሮፌሰሩ ጨምረውም በቅርቡ ሰሜን ኮሪያ ባሳየቻቸው ወታደራዊ ትዕይንቶች ላይ የአገሪቱ ጦር በአዲስ እና ዘመናዊ ጦር መሳሪያዎች መታጠቁን አሳይቷል ይላሉ።

ኪም ለፑቲን “ለሩሲያ ጉብኝታችን ከፍተኛ ትኩረት ስለሰጡት አመሰግናለሁ። ኢምፔሪያሊዝምን በመታገል አብረን እንቆማለን ብዬ አምናለሁ” ማለታቸው ተዘግቧል።

ኪም እና ፑቲን

የፎቶው ባለመብት, KREMLIN

የፑቲን እና ኪም ውይይት ሲጀመር ፑቲን “ስላየሆትና ሩሲያ ስለመጡ ደስ ብሎኛል” ብለዋል።

ሰሜን ኮሪያ “ለሮኬት ምኅንድስና” ትኩረት መስጠቷን ፑቲን ቢናገሩም ሰሜን ኮሪያ ማዕቀብ የተጣለባቸው የኒውክሌር መሳሪያ ሙከራዎች ማድረጓ ሲተች ነበር።

ሁለቱ አገራት የጦር መሳሪያ ስምምነት ሊያደርጉ ይችሉ እንደሆነ ከጋዜጠኛ ጥያቄ የቀረበላቸው የክሬምሊን ቃለ አቀባይ ሲመልሱ፣ ፒዮንግያንግ እና ሞስኮ ሚስጥራዊ በሆኑ ጉዳዮች ዙሪያ ትብብር እንደሚያደርጉና ይህም ለሕዝብ ይፋ እንደማይሆን ገልጸዋል።

ሁለቱ ከምዕራባውያን የተለያየ ማዕቀብ የተጣለባቸው አገራት የጦር መሳሪያን በሰብአዊ እርዳታ ለመለዋወጥ ስምምነት ሊያደርጉ እንደሚችሉ ይጠበቃል።

የቻይና የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር በቀጣይ ሳምንት ሞስኮን እንደሚጎበኙም ተገልጿል።

በሁለቱ አገራት መሪዎች ውይይት ላይ የኪም እህት የሆኑት ተጽዕኖ ፈጣሪዋ ኪም ኦ ጆንግም መገኘታቸው ተዘግቧል።

ኪም እና ፑቲን

የፎቶው ባለመብት, EPA

ሁለቱ መሪዎች ከረፋድ በኋላ ውይይታውን ካጠናቀቁ በኋላ ኪም ጆንግ ኡን ወደ ሰሜን ኮሪያ የሚወስዳቸውን ባቡር ተሳፍረዋል።

ኪም ከፑቲን ጋር ባደረጉት ቆይታ የሞስኮ ኃይሎች በጠላቶቹ ላይ “ድል እንደሚቀዳጅ” እምነቴ ነው ብለዋል።

“የሩሲያ ጦርና ሕዝብ የሰይጣኖችን ስብስብ እንደሚያሸንፍ ሙሉ በሙሉ እንተማመናለን” ብለዋል ኪም።