አሜሪካ ከ500 በላይ ፖሊሶች አሰማርታ ስታድነው የነበረው ታራሚ ከሁለት ሳምንታት በኋላ ተያዘ

ከአሜሪካ ፔንስልቪንያ እስር ቤት አምልጦ ሲታደን የነበረው ታራሚ ከሁለት ሳምንታት በኋላ በቁጥጥር ስር ዋለ።
የ34 ዓመቱ ዳኔሎ ካቫልካንቴ በቁጥጥር ስር የዋለው ፖሊሶች ክትትል ሲያደርጉበት በነበረ ጫካ ውስጥ እንደሆነም የህግ አስከባሪ ምንጭ ለቢቢሲ ገልጸዋል።
የብራዚል ዜግነት ያለው ታራሚ ከሁለት ሳምንታት በፊት ከእስር ቤት ያመለጠ ሲሆን እሱንም አድኖ ለመያዝ ከ500 በላይ የፖሊስ መኮንንኖች ተሰማርተው ነበር።
ግለሰቡ ከሁለት ዓመታት በፊት የቀድሞ ፍቅረኛውን በሁለት ህጻናት ልጆቿ ፊት በመግደል ወንጀል እስር የተበየነበት ባለፈው ወር ነበር።
ፖሊስ በሚሰጠው ጋዜጣዊ መግለጫም ላይ ግለሰቡ የተያዘበትን ዝርዝር ሁኔታም ያካፍላል ተብሎ ይጠበቃል።
ታራሚው በፖሊስ መኪና ውስጥ ሲጫን የሚያሳዩ ቪዲዮዎችን የአገር ውስጥ ሚዲያዎች አጋርተዋል።
ዳኔሎ ከዚህ ግድያ በተጨማሪም በትውልድ አገሩ በተፈጸመም ግድያ ጋርም በተያያዘ እንደሚፈለግም ተገልጿል።
ባለፈው ሳምንት መጨረሻ ላይ ፖሊስ ከቦት ከነበረው ስፍራም ማምለጡም ተዘግቧል።
የቼስተር ካውንቲ ነዋሪዎችም ግለሰቡ በተደጋጋሚ በአካባቢው ታይቷል መባሉ ጋር ተያይዞ ስጋት ገብቷቸው እንደነበርም ተገልጿል።
ፖሊስ ከማረሚያ ቤት ያመለጠው ነፍሰ ገዳይ 22 ካሊበር ጠመንጃ ከአንድ መኖሪያ ቤት ውስጥ ሰርቋል ሲልም በዚህ ሳምንት ማክሰኞ አስጠንቅቆ ነበር።
ነገር ግን የፔንስልቬንያ አስተዳዳሪ ቆይተውም ተልዕኮው እንደተጠናቀቀ እና ታራሚውም እጅ እንዲሰጥም አሳስበው ነበር።
የሟቿ ዲቦራ ብራንዶ ቤተሰቦች ግለሰቡ ሊያጠቃቸው ይችላል በሚል ስጋትም ፖሊስ የ24 ሰዓት ክትትል ሲያደርግላቸው ቆይቷል።
የታራሚው እናት ከኒውዮርክ ታይምስ ጋር ባደረጉት ያልተለመደ ቃለ ምልልስ ልጃቸው በህይወት ለመቆየት እየታገለ እንደሆነ እና “ለማንም ስጋት አይደለም” ሲሉ ተናግረዋል።
"ልጄ ያደረገው ስህተት እንደሆነ አውቃለሁ። ልጄ ለጥፋቱ መክፈል እንዳለበት አውቃለሁ" በማለት እናቱ ኢራሴማ ካቫልካንቴ ተናግረዋል።
“ሆኖም ልጄ ለስህተቱ በክብር እንዲከፍል እፈልጋለሁ። በህይወቱ መክፈል የለበትም” ሲሉም ተደምጠዋል።
ታራሚው የቀድሞ ፍቅረኛውን ዲቦራን ከመግደል በተጨማሪ በአውሮፓውያኑ 2017 በብራዚል ባልተከፈለ ዕዳ ምክንያት አንድ ጓደኛውንም በመግደል ክስ ቀርቦበታል።












