ዩክሬን እና ኬንያ ለምስራቅ አፍሪካ ‘የእህል ማዕከል’ ለማቋቋም ማቀዳቸውን ገለጹ

የኬንያ እና የዩክሬን መሪዎች

የፎቶው ባለመብት, Kenya Presidency

ዩክሬን አህጉሪቱ እየገጠማት ያለውን የምግብ ዋስትና ችግር ለመቅረፍ በኬንያ እና በሌሎች የአፍሪካ አገራት “የእህል ማዕከላት” እንደምታቋቁም አስታወቀች።

የዩክሬኑ ፕሬዚዳንት ቮሎድሚር ዘለንስኪ ከኬንያ እና ደቡብ አፍሪካ አቻዎቻቸው ጋር በኒውዮርክ ከተገናኙ በኋላም ነው ጽህፈት ቤታቸው ይህንን እቅዱን ያስታወቀው።

ዩክሬን ለአፍሪካ አገራት ዋነኛ እህል አቅራቢ ነች።

ዩክሬን በጥቁር ባህር በኩል ደህንነቱ በተጠበቀ ሁኔታ እህል ማጓጓዝ የሚያስችላትን በተባበሩት መንግሥታት ጥላ ስር ከተደረሰው ስምምነት ሩሲያ መውጣቷን ተከትሎ በአህጉሪቱ የእህል እጥረት ያጋጥማል የሚል ስጋት ገጥሟል።

ሩሲያ ዩክሬን ላይ የፈጸመችው ወረራን ተከትሎ የዓለም የእህል ዋጋ ጭማሬ አሳይቷል።

ፕሬዚዳንት ዘለንስኪ ማክሰኞ በተባበሩት መንግሥታት ድርጅት ጠቅላላ ጉባኤ ላይ ባደረጉት ንግግር ሩሲያ ከምግብ እስከ ኃይል ያለውን በመሳሪያነት እየተጠቀመችበት ነው ሲሉም ከሰዋል።

ፕሬዚዳንቱ በኒውዮርክ ቆይታቸውም ከኬንያው ፕሬዚዳንት ዊሊያም ሩቶ እና ከደቡብ አፍሪካ ሲሪል ራማፎሳ ጋር ተገናኝተዋል።

ፕሬዚዳንት ሩቶ ግንኙነታቸውን አስመልክቶ በሰጡት መግለጫ የዩክሬኑ ፕሬዚዳንት በምስራቅ አፍሪካ ያለውን የምግብ እጥረት ለመቅረፍ በኬንያዋ የባህር ዳርቻ ከተማ ሞምባሳ “የእህል ማዕከል” ለማቋቋም ቁርጠኛ መሆናቸውን ተናግረዋል።

ነገር ግን ፕሬዚዳንት ሩቶ እህሉ እንዴት ይደርሳል የሚሉ እና ሌሎች ጉዳዮችን በተመለከተ ተጨማሪ ዝርዝር አልሰጡም።

ሩስያ በዩክሬን ወረራ መፈጸሟን ተከትሎ ከዩክሬን ጎን ከቆሙት መካከል ኬንያ አንዷ ተጠቃሽ ናት።

በአንጻሩ ደቡብ አፍሪካ ገለልተኛ አቋም እንዳላት የምትገልጽ ሲሆን ባለፈው ዓመት ሰኔ ወርም ፕሬዚዳንት ራማፎሳ ለጦርነቱ ሰላማዊ እልባት ለማግኘት በሚል የአፍሪካ የሰለም ልዑካንን ወደ ዩክሬን እና ሩሲያ መርተዋል።

ፕሬዚዳንት ራማፎሳ ከዩክሬኑ አቻቻው ጋር በሰላሙ ጉዳይ ላይ መወያየታቸውን ተናግረዋል። በተጨማሪም በጥቁር ባህር በኩል ዩክሬን እህል መላክ የሚያስችላትን የእህል ስምምነት የሚታደስበትን ሁኔታ ማንሳታቸው ተጠቅሷል።