ቬንዙዌላ በአደገኛ ወንበዴዎች የተያዘባትን እስር ቤት መልሶ ለመቆጣጠር 11 ሺህ ወታደሮችን ላከች

የፎቶው ባለመብት, Getty Images
ቬንዙዌላ በአደገኛ የወንጀለኛ ቡድኖች የተያዘባትን ትልቅ እስር ቤት መልሶ ለመቆጣጣር 11 ሺህ ወታደሮችን ላከች።
በአገሪቷ ሰሜናዊ ክፍል የሚገኘው ቶኮሮን እስር ቤት ለዓመታት ትሬን ዲ አራጓ በሚባሉ አደገኛ የወንጀለኛ ቡድኖች ቁጥጥር ሥር ነበር።
ይህ አደገኛ የወንጀለኛ ቡድን በርካታ አባላት እንዳሉት ይነገራል።
የአገሪቷ ውስጥ መገናኛ ብዙኃን እንደዘገቡት የቡድኑ አባላት የመዋኛ ገንዳ፣ የምሽት ክለብ፣ አነስተኛ የእንስሳት ፓርክን ጨምሮ ልክ እንደ ሆቴል የተለያዩ አገልግሎቶች ባሉት እስር ቤቱ አካባቢ እንደልባቸው ሲንቀሳቀሱ ነበር።
ሌሎች ሰላማዊ ነዋሪዎችም ከፍርደኛ ታሳሪዎች ጋር አብረው በእስር ቤቱ ውስጥ ይኖሩ እንደነበርም ተገልጿል።
እስር ቤቱ ከወንበዴዎች ቁጥጥር ነጻ ከወጣ በኋላ 6 ሺህ የሚሆኑት እስረኞች ወደ ሌላ እስር ቤት እንደሚዛወሩ ባለሥልጣናት ተናግረዋል።
ባለሥልጣናት እስረኞቹ ወደ ሌላ እስር ቤት ሊዛወሩ እንደሚችሉ ከገለጹ በኋላም፣ የታሳሪ ዘመዶች ወዴት እንደሚወስዷቸው እርግጠኛ ባለመሆናቸው ደጅ ላይ ሆነው ሲያለቅሱ ታይተዋል።
ግላዲየስ ሔርናንዴዝ የተባለች ግለሰብ “ ባለቤቴን ወዴት እንደሚወስዱት ለማወቅ እየጠበቅኩ ነው። እዚያ ነበር የምንኖረው። አሁን ከዚያ አስወጡን” ስትል ለኤኤፍፒ የዜና ወኪል ተናግራለች።
የጸጥታ አካላትም ከእስር ቤቱ ሞተር ሳይክሎችን፣ ቴሌቪዥኖችን እና ማይክሮዌቮችን ሲያወጡ ጋዜጠኞች ተመልክተዋል።
የቬንዙዌላ የውስጥ ጉዳይ ሚኒስቴር በኤክስ (X) የማኅበራዊ ሚዲያ ገጹ ላይ ባሰፈረው ጽሑፍ የጸጥታ አካላት እስር ቤቱን መልሰው በመቆጣጠራቸውና "የሴራ እና የወንጀል ማዕከል" የነበረውን እስር ቤት በመበተናቸው የእንኳን ደስ ያላችሁ መልዕክት አስተላልፏል።
እስር ቤቱ የአገር በቀል አደገኛ የወንጀለኛ ቡድኑ አባላት ታስረው የሚገኙበት ሲሆን የቡድኑ ዋና መስሪያ ቤት ተደርጎም ይታሰባል።
ከእስረኞቹ መካከል የትሬን ዲ አራጓ ወንበዴ ቡድን መሪ ሔክተር ጉሬሮ ፍሎርስ ይገኝበታል።
ሔክተር በግድያ እና በእጽ ማዘዋወር ክስ የ17 ዓመት እስር ተፈርዶበት በእስር ቤቱ ያሳልፍ ነበር።
መሪው አደገኛ የነበረ ሲሆን ፍርደኛ እስረኛ ከመሆኑ በፊት እስር ቤቱ እየገባ እና በነጻ እየወጣ መቆየቱን የቬንዙዌላ እስር ቤት ተቆጣጣሪው ዊንዶው ኦፍ ፍሪደም አስተባባሪ የሆኑት ካርሎስ ኔቶ ተናግረዋል።












