ገላን በሚገኝ ጊዜያዊ ማቆያ ጣቢያ በተስቦ በሽታ የ3 ሰዎች ሕይወት ማለፉ ተነገረ

EHRC

የፎቶው ባለመብት, EHRC

በኦሮሚያ ክልል ሸገር ከተማ ገላን ክፍለ ከተማ በሚገኝ ጊዜያዊ ማቆያ ማዕከል ውስጥ ተላላፊ በሽታ ተከስቶ የ3 ሰዎች ሕይወት ማለፉን የኢትዮጵያ ሰብዓዊ መብቶች ኮሚሽን (ኢሰመኮ) አስታወቀ።

ኮሚሽኑ ዛሬ ማክሰኞ መስከረም 8/2016 ዓ.ም. ባወጣው መግለጫ፣ የጎዳና ተዳዳሪዎች ተገድደው እንዲቆዩ በሚደረጉበት ‘ሲዳ አዋሽ’ ተብሎ በሚታወቅ አካባቢ በሚገኘው ማዕከል በተባይ የሚተላለፍ የተስቦ በሽታ ምክንያት፣ 190 ሰዎች ሆስፒታል ገብተው እንደነበረ እና 3 ሰዎች በጽኑ ታምመው ነበር ብሏል።

ባለፉት ቀናት ይህ በሸገር ከተማ፣ ገላን ክፍለ ከተማ ይገኛል የተባለው ማቆያ ጣብያ ብዙ ውዝግቦችን ሲያስነሳ ቆይቷል።

ተቃዋሚ የሆኑ ግለሰቦች እና ሲቪል ማኅበር ማቆያ ጣቢያው በአማራ ክልል ከተፈጠረው ግጭት ጋር በያያዘ ሰዎች በማንነታቸው ተለይተው በጅምላ እንዲታሰሩ የተደረጉበት ቦታ ነው ሲሉ ነበር።

የአስቸኳይ ጊዜ አዋጁን ለማስፈጸም የተቋቋመው ጠቅላይ መምሪያ ግን፣ እስካሁን ያዘጋጃቸው የማቆያ ቦታዎች 5 ብቻ መሆናቸውን ገልጾ እነዚህ ኮምቦልቻ፣ ጎንደር፣ ባሕር ዳር፣ ሸዋ ሮቢት እና አዋሽ አርባ እንደሆኑ አስታውቋል።

ሆኖም የእስረኞች አያያዝ እየተከታተለ የሚገኘው የአስቸኳይ ጊዜ አዋጁ የምርመራ ቦርድ በአዲስ አበባም ጭምር የታሰሩ ሰዎች እንደሚገኙ ጠቁሞ ነበር።

የኢትዮጵያ ሰብዓዊ መብቶች ኮሚሽን በዛሬው መግለጫው፣ በሸገር ከተማ በሚገኘው ጊዜያዊ ማቆያ ጣቢያ ጉብኝት አደርጎ፣ በማዕከሉ ያሉ ሰዎቸን አነጋግሮ፣ የሚመለከታቸውን የመንግሥት ኃላፊዎች እና የማዕከሉ አስተባበሪዎች ጠይቆ በማቆያ ማዕከሉ የሚገኙት ሰዎች ውሎ እና አዳራቸውን በጎዳና ላይ ያደረጉ ሰዎች ናቸው ብሏል።

በዚህ ማቆያ ጣቢያ ሕጻናት እና አረጋውያን ጨምር እንደሚገኙ የተገለጸ ሲሆን ቁጥራቸውም በተለያየ ጊዜ ለውጥ እንዳለው ገልጾ አሁን ላይ በመቶዎች እንደሚቆጠሩ አብራርቷል።

ኢሰመኮ የማቆያ ማዕከሉ አስተባባሪዎች የጊዜያዊ ማዕከሉ ዋነኛ ዓላማ ከጎዳና እንዲነሱ የተደረጉት ሰዎች በመልሶ ማቋቋም ወደ መጡባቸው አካባቢዎች እንዲመለሱ እና ከጎዳና ላይ ውሎና አዳር እንዲወጡ ማድረግ መሆኑን ነግረውኛል ብሏል።

ኢሰመኮ በማቆያ ማዕከል ለሚገኙ ሰዎች፣ በቀን 3 ጊዜ ምግብ እና የመጠጥ ውሃ ቢቀርብም ማቆያ ማዕከሉ ለሰዎች መጠለያ ተብሎ የተዘጋጀ ባለመሆኑ መሠረተ ልማቶች አልተሟሉለትም ብሏል።

የሰዎች ሕይወት ማለፍ

የኢትዮጵያ ሰብዓዊ መብቶች ኮሚሽን በመግለጫው ማቆያ ጣብያው የተሟላ መሠረተ ልማት የተሟላለት ባለመሆኑ በጣብያው የሚገኙ ሰዎችን ሰብዓዊ ክብር የጠበቀ አያያዝ አስቸጋሪ አድርጎታል ብሏል።

መጠለያ ጣብያው በቂ አየርና የፀሐይ ብርሃን የማያገኝ ከመሆኑ በላይ መጸዳጃ ቤት፣ ንጽሕና መጠበቂያ ውሃ፣ የመኝታ አልጋ፣ ፍራሽና አልባሳት ባለመኖራቸው ከፍተኛ የንጽሕና ጉድለት በቦታው አለ ብሏል።

በዚህም ምክንያት በማቆያ ማዕከሉ በቅርቡ በተባይ የሚተላለፍ የተስቦ በሽታ መከሰቱን ተከትሎ የ3 ሰዎች ሕይወት ማለፉን እና 3 ደግሞ በጽኑ ታምመው እንደነበረ አስታውቋል።

ኢሰመኮ በዚህ ተላላፊ በሽታ የተጠቁ 190 ሰዎች ወደ ሆስፒታል ተወስደው የሕክምና አገልግሎት እንዲያገኙ መደረጉን ጨምሮ ገልጿል።

የሰብዓዊ መብቶች ኮሚሽን ሰዎችን ያለፍላጎታቸው ወደ ማይፈልጉበት አካባቢ እንዲሄዱ ማስገደድ የሰብዓዊ መብቶች ጥሰት በመሆኑ መንግሥት ዜጎችን ወደ መልሶ ማቋቋም ፕሮግራም ማስገባት ያለበት ፈቃደኝነት ላይ ተመስርቶ መሆን አለበት ብሏል።

የሰብዓዊ መብት ኮሚሽኑ ሰዎች ወደ መሰል ማቆያ ጣቢያዎች እንዲገቡ ከመደረጋቸው በፊትም ሌሎች አስፈላጊ ቅድመ ሁኔታዎች መሟላታቸው መረጋገጥ አለባቸው ብሏል።

ኮሚሽኑ በአሁኑ ወቅት በዚህ ማቆያ ማዕከል የሚገኙ ሰዎችን አያያዝ ለማሻሻልና ሰብዓዊ ክብርና አያያዝን ለማረጋገጥ የሚያስችል በቂ የምግብ፣ የውሃ፣ የመኝታ፣ የንጽሕና እና የሕክምና አገልግሎቶችን በአፋጣኝ ሊሟሉ ይገባል ብሏል።