ከፕሪቶሪያው የሰላም ስምምነት በኋላም የጦር ወንጀሎች እየተፈጸሙ ነው- ተመድ

የፎቶው ባለመብት, Getty Images
ለሁለት ዓመታት የዘለቀውን ደም አፋሳሽ ጦርነት የቋጨው የፕሪቶሪያው ግጭትን በዘላቂነት የማቆም ስምምነት ተከትሎም የጦር ወንጀሎች እና በሰብዓዊነት ላይ የሚፈጸሙ ወንጀሎች መቀጠላቸውን የተባበሩት መንግሥታት መርማሪ ኮሚሽን በሪፖርቱ ይፋ አደረገ።
በፌደራሉ መንግሥት እና በህወሃት መካከል የተፈረመው ስምምነት አስር ወራት ገደማ ቢያስቆጥርም ጥሰቶች መቀጠላቸውን ነው በኢትዮጵያ የርስ በርስ ጦርነት የተፈጸሙ ጥሰቶችን እንዲያጣራ በተባበሩት መንግሥታት ሰብዓዊ መብቶች ምክር ቤት የተቋቋመው የሰብዓዊ መብቶች የባለሙያዎች ቡድን ትናንት መስከረም 7/2015 ዓ.ም ባወጣው ሁለተኛው ሪፖርት ያተተው።
የሰብዓዊ መብቶች የባለሙያዎች ቡድን ከዚህ ቀደም የመዘገባቸው የጅምላ ግድያ፣ መድፈር፣ ረሃብ፣ አስገዳጅ መፈናቀል እና የጅምላ እስር ከስምምነቱም በኋላ ቀጥሏል ብሏል።
ቡድኑ ለተባበሩት መንግሥታት ድርጅት የሰብዓዊ መብቶች ምክር ቤት ባቀረበው የቅርብ ጊዜ ሪፖርቱ እንዳረጋገጠው የኤርትራ ወታደሮች እና የአማራ ኃይሎች እና ሚሊሻዎች በትግራይ ክልል መዋቅራዊ የሆነ የሆነ መድፈርን ጨምሮ ሌሎች ጥሰቶችን እየፈጸሙ ነው ብሏል።
በምዕራብ ትግራይ በአስር ሺዎች የሚቆጠሩ የትግራይ ተወላጆች ከስምምነቱም በኋላ ከቀያቸው እንዲፈናቀሉ መደረጉንም ነው ቡድኑ የመዘገበው።
በተለይም የኤርትራ ኃይሎች አስከፊ የሚባለውን ወሲባዊ ጥቃቶች በድንበር አካባቢ ስለመፈጸማቸውም ሪፖርቱ ጠቅሶ በነዚህ ኃይሎች ላይ ምንም አይነት የተጠያቂነት ሁኔታ አለመዘርጋቱ አሳሳቢ ነው ብሏል።
ከስምምነቱ በኋላ የኤርትራ ወታደሮች በትግራይ እንደ ጦር ወንጀል እና በሰብዓዊነት ላይ የሚፈጸም ወንጀል ሊቆጠሩ የሚችሉ ወሲባዊ ባርነት፣ ግድያዎችን እና ሌሎች ከባድ ጥሰቶች መፈጸማቸውን ዓለም አቀፉ የሰብዓዊ መብት ተቆርቋሪው አምነስቲ ከሰሞኑ ማስታወቁ ይታወሳል።
“የኤርትራ ወታደሮች በኢትዮጵያ ውስጥ መኖራቸው እና ለፈጸሙት ጥሰቶች ተጠያቂነት አለመስፈኑ ግልጽ ምልክት ብቻ ሳይሆን መሰል ጥሰቶችን እንዲኖሩ የፌደራል መንግሥት ያለውን ድጋፍ እና ቻይነት ያሳያል” ብለዋል የቡድኑ ሊቀ መንበር መሃመድ ቻንዴ ኦትማን
የፌደራል መንግሥት የአገሪቱን የግዛት አንድነት እንዲሁም የሰብዓዊ መብቶችን ለማስጠበቅ የገባውን ቃል የጣሰ እንደሆነም ቡድኑ በትናንትናው ዕለት በጄኔቫ በሰጠው ጋዜጣዊ መግለጫ አመልክቷል።
በጦርነቱ ቢያንስ 10 ሺህ የሚሆኑ ሴቶች መደፈር እና ወሲባዊ ጥቃቶች እንደደረሰባቸው ይፋ ያደረገው ሪፖርቱ ስምምነቱ እነዚህን ጥቃቶች ሊያስቆም አልቻለም ብሏል።
“ስምምነቱ መፈረሙ ባብዛኛው የጠመንጃ አፈሙዞችን ጸጥ ቢያሰኝም በሰሜኑ የአገሪቱ ክፍል በተለይም በትግራይ ያለውን ጦርነት ሊፈታው አልቻለም፤ ወይም አጠቃላይ ሰላም ሊያመጣም አልቻለም። በኢትዮጵያ ያለው ሁኔታ እጅግ አሳሳቢ ነው” ሲሉ መሃመድ ቻንዴ ኦትማን ተናግረዋል።
የከፉ ጥሰቶች አደጋ
አገሪቱ በአሁኑ ወቅት በተለያዩ ማዕዘኖች ግጭቶች እያስተናገደች ከመሆኗ ጋር ተያይዞም የከፉ ሰብዓዊ መብት ጥሰቶች ሊከሰቱ እንዲሚችሉ እና የምስራቅ አፍሪካንም የጸጥታ ሁኔታ አደጋ ሊከት እንደሚችል የሰብዓዊ መብቶች ባለሙያዎች ቡድን ኮሚሽን አስጠንቅቋል።
በአማራ ክልል እንዲሁም በሌሎች ክልሎች እንደ አስፈላጊነቱ ተፈጻሚ ይሆናል የተባለው የአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ ጋር ተያይዞ በክልሉ ነዋሪዎች በጅምላ መታሰራቸው ቢያንስ አንድ የድሮን ጥቃት እንዲሁም በርከት ያሉ ጥሰቶች ስለመፈጸማቸው አሳማኝ ሪፖርቶች ደርሰውኛል ብሏል።
የአማራ የጸጥታ ሁኔታ እያሽቆለቆለ መምጣቱ መንግሥት በአማራ ክልል የደነገገው ወታደራዊ ኮማንድ ፖስት የሲቪል አካላትን ያላካተተ መሆኑም ጋር ተያይዞ የከፉ ጥሰቶችን የሚያስከትል እንደሆነም ገልጿል።
ኮሚሽኑ በአሮሚያ ክልል ውስጥ የመንግሥት ኃይሎች በሰላማዊ ዜጎች ላይ ስቅይት እና እንግልትን ጨምሮ እስሮችም እያካሄዱ መሆኑንም ነው በትናንትናው ዕለት ያስታወቀው።
ቡድኑ በዚህ ሪፖርቱ መጠነ ሰፊ ጥሰቶች በአገሪቱ ሊፈጸሙ እንደሚችሉም አመላካች ሁኔታዎች እንዳሉም ጥልቅ ስጋቶች አሉ ብሏል።
“በኦሮሚያ፣ በአማራ፣ በትግራይ እና በሌሎች የአገሪቱ ክፍሎች ያለው ሁኔታ፣የቀጠሉ የመብት ጥሰቶች፣ ለወንጀሎች ተጠያቂነት አለመምጣት በአገሪቱ ሌሎች ጥሰቶች እና ወንጀሎች እንደሚፈጸሙ አደጋ ለማንዣበቡ ማሳያ ነው” ሲሉም አስጠንቅቀዋል።
ከዚህ ቀደም 19 ገጾች ባሉት የመጀመሪያው ግኝት ሪፖርት በጦርነቱ መደፈር፣ ወሲባዊ ጥቃቶች፣ የዘፈቀደ ግድያ እና ረሃብ እንደ ጦር መሳሪያ ጥቅም ላይ መዋላቸውን ይፋ ያደረገው የባለሙያዎች ቡድን የዕድሜ የመራዘም ሁኔታ ባልታወቀበት ጊዜ ነው ይህንን ሪፖርት ያወጣው።
ከመቋቋሙ ጀምሮ ተቃውሞ እያቀረበ ያለው የኢትዮጵያ መንግሥት የተመድ የሰብዓዊ መብቶች የባለሙያዎች ቡድን የስራ ጊዜ እንዲጠናቀቅና በአገሪቱ ማዕቀፍም ጥሰቶች እንዲታዩ ከፍተኛ ጫናም ሲያደርግ ቆይቷል።
ትርጉም ያለው ተጠያቂነት እና ፍትህ
ኮሚሽኑ በበኩሉ የኢትዮጵያ መንግሥት ጥሰቶችን በብቃት መከላከልም ሆነ ለመርመር እንደተሳነው እና በምትኩ አካታች እና ግልጽነት የሚጎድለውና ችግር ያለበትን የሽግግር ሂደት መጀመሩን ገልጿል።
ሂደቱ መንግሥት ያወጣውን የዘፈቀደ ቀነ ገደብም ለማሟላት በሚል በጥድፊያ የተፈጸመ ሲሆን ጥሰት የደረሰባቸውን ተጎጂዎችን ያገለለ ነው ሲልም ተችቶታል።
ኢትዮጵያ የሽግግር ፍትህ ሂደቱን ያቋቋመችው ዓለም አቀፍ ምርመራዎችን ለማምለጥ ነውም ብሏል ቡድኑ።
“በኢትዮጵያ ውስጥ ያለውን የሽግግር ፍትህ ጅማሮ ስንታዘብ መንግሥት አገራዊ ማዕቀፎችን በመፍጠር አለም አቀፍ ምርመራን ለማምለጥ ሆን ተብሎ የሚደረግ ጥረት እያደረገ እንደሆነ የሚያሳዩ ማስረጃዎች አሉ” ሲልም በመግለጫው አትቷል።
እንዲሁም በሂደቱ አለም አቀፍ ጫናዎችን ለማስወገድ እና እንዲሁም ጠንካራ አለም አቀፋዊ ምርመራ እንዳይካሄድ ለማድረግ እንደሆነም የጠቀሰው ኮሚሽነሩ “በመላው ኢትዮጵያ በመቶ ሺዎች ለሚቆጠሩ የግፍ ሰለባዎች ስንል ይህ እንዲቀጥል መፍቀድ አይቻልም” ሲልም ቡድኑ አቋሙን አስታውቋል
“ተአማኒ፣ አካታች እና ትርጉም ያለው የእውነት፣ የእርቅ እና የፍትህ ሂደት አስፈላጊነት" ከመቼውም ጊዜ የበለጠ አስፈላጊ እንደሆነም ተናግረዋል።
የፌደራል መንግሥቱ በጦርነቱ የተፈጸሙ ጥሰቶች በሽግግር ፍትህ እልባት እንዲያገኙ ለማድረግ እየሰራ መሆኑም ከዚህ ቀደም መግለጹ ይታወሳል።
“የሽግግር ፍትህ አገራት ያለፉበትን ግፍና ሰቆቃዎችን እንዲገነዘቡ ለመርዳት ያለመ ነው። ሆኖም በመቶዎች ከሚቆጠሩ ተጎጂዎች፣ ቤተሰቦቻቸው እና ተወካዮች ጋር ባደረግነው ውይይት በኢትዮጵያ መንግሥትም ሆነ ተቋማት እምነት እንደሌላቸው ነው” ሲልም አትቷል።
ቡድኑ ከኢትዮጵያ መንግሥት በኩል ትብብር እንዳላገኘ ጠቅሶ የኤርትራ መንግሥት ወታደሮቹ በትግራይ ስለፈጸሙት ጥሰቶች ምላሽ አልሰጠም ብሏል።












