በምዕራብ ጎጃም በተፈጸሙ የድሮን ጥቃቶች ‘ከ30 በላይ ሰላማዊ ሰዎች መገደላቸውን’ ነዋሪዎች ተናገሩ

በምዕራብ ጎጃም ዞን ደምበጫ ከተማ እና ቋሪት ወረዳ ከትናንት በስቲያ መስከረም 6/2016 ዓ.ም በተፈጸሙ የድሮን ጥቃቶች በርካታ ሰላማዊ ሰዎች መገደላቸውን የአካባቢው ነዋሪዎች ለቢቢሲ ተናገሩ።
ነዋሪነታቸው በቋሪት ወረዳ የሆኑ እና ለደህንነታቸው ሲባል ስማቸው እንዳይጠቀስ የጠየቁ የአካባቢው ነዋሪ ሁለት ስፍራዎች ላይ የድሮን ጥቃት ተፈጽሟል ብለዋል።
በአንደኛው ጥቃት “በብዛት ተሰባስበው ይጓዙ የነበሩ ሰላማዊ ሰዎች ኢላማ ተደርገዋል” ያሉት እኚህ ነዋሪ በጥቃቱ “ቢያንስ 30 ሰዎች ተገድለዋል” ሲሉም ለቢቢሲ ተናግረዋል።
የድሮን ጥቃት የተፈጸመባቸውን አካባቢዎችን እንደጎበኙም እኚሁ ነዋሪ ለቢቢሲ አስረድተዋል።
ጥቃቱ የደረሰው ውጊያ ከሚደረግበት አካባቢ የራቀ እና ለጊዜው የታጣቂዎች እንቅስቃሴ ባልነበረበት ቦታ መሆኑንም እኚሁ ነዋሪ አስረድተዋል።
በሁለተኛው ስፍራ የደረሰው የድሮን ጥቃት ግን ጉዳት አለማድረሱን ገልጸዋል።
“ለሁለተኛ ጊዜ የተደረገው ጥቃት ጫካ ላይ ነው ያረፈው፣ በመሆኑም በሰውም ሆነ በንብረት ላይ ጉዳት አልደረሰም” ብለዋል።
በሌላኛዋ የምዕራብ ጎጃም ከተማ ደምበጫ ከተማ ተፈጽሟል በተባለ የድሮን ጥቃት በተመሳሳይ ሰላማዊ ሰዎች ሰለባ መሆናቸውን ነዋሪዎች ለቢቢሲ ተናግረዋል።
ቢቢሲ ያነጋገራቸው የከተማዋ ነዋሪ ጥቃቱ የተፈጸመው ሚካኤል ቤተ ክርስቲያን አካባቢ ነው ብለዋል።
ነዋሪው ቢያንስ 18 ሰዎች መገደላቸውን ገልጸው በአካባቢው አስከሬን በማንሳት መሳተፋቸውንም ለቢቢሲ ተናግረዋል።
ቢቢሲ በቋሪት እንዲሁም በደምበጫ አካባቢ ተፈጽሟል ስለተባለው የድሮን ጥቃት መረጃ ለማግኘት የመንግሥት አካላትን ለማነጋገር ቢሞክርም ምላሽ አላገኘም።
ከአንድ ወር በፊት በፍኖተ ሰላም ከተማ በተፈጸመ የድሮን ጥቃት ቁጥራቸው 30 የሚደርሱ ሰላማዊ ሰዎች መገደላቸውን እና ከ50 በላይ የሚሆኑት ደግሞ ጉዳት መድረሱን ቢቢሲ ከዚህ ቀደም መዘገቡ ይታወሳል።
በኢትዮጵያ የርስ በርስ ጦርነት የተፈጸሙ ጥሰቶችን እንዲያጣራ በተባበሩት መንግሥታት የተቋቋመው የሰብዓዊ መብቶች የባለሙያዎች ቡድን ትናንት መስከረም 7/2015 ዓ.ም ባወጣው ሁለተኛው ሪፖርት በክልሉ ቢያንስ አንድ የድሮን ጥቃት ስለመፈጸሙ ሪፖርት ደርሶኛል ብሏል።
በከተማው መውጫ አካባቢ ከፋኖ ታጣቂዎች ጋር ተኩስ መኖሩን የተናገሩት እኚሁ ነዋሪ ጥቃቱ በተፈጸመበት አካባቢ ግን ምንም አይነት የታጣቂ እንቅስቃሴ አልነበረም ሲሉም አስረድተዋል።
የመከላከያ ሰራዊት አባላት ከከተማዋ ውጭ በሚገኙ የገጠር ቀበሌዎች በመንቀሳቀስ ነዋሪዎችን “መሣሪያ አምጡ” እያሉ በማስጨነቃቸው ምክንያት ጦርነቱ እንደገና ማገርሸቱንም እኚሁ ነዋሪ ይናገራሉ።
አሁንም በከተማዋ ምዕራባዊ አቅጣጫ ጦርነት እየተደረገ መሆኑን እና ከተማዋ ምንም አይነት እንቅስቃሴ እንደማይታይባት አክለው ገልጸዋል።
በአማራ ክልል በአንዳንድ አካባቢዎች “የጦር መሳሪያ ደብቃችኋል አምጡ” በሚል በመንግሥት የጸጥታ አካላት ከፍርድ ውጭ ግድያዎች መፈጸማቸውን የኢትዮጵያ ሰብዓዊ መብቶች ኮሚሽን (ኢሰመኮ) ከሰሞኑ መግለጹ ይታወሳል።
በአማራ ክልል በአንዳንድ አካባቢዎች ከቀጠለው ግጭት ጋር ተያይዞ በመንግሥት የጸጥታ አካላት ከፍርድ ውጭ የተፈጸሙ ግድያዎች እጅግ አሳሳቢም እንደሆነ የኢትዮጵያ ሰብዓዊ መብቶች ኮሚሽን (ኢሰመኮ) መስከረም 4/2015 ዓ.ም ባወጣው መግለጫ አስታውቋል።
በመንግሥት የጸጥታ አባላት ከህግ ውጭ የተፈጸሙት ግድያዎች በአዴት፣ ደብረማርቆስ፣ ደብረታቦር፣ ጅጋ፣ ለሚ፣ ማጀቴ፣ መራዊ፣ መርጦ ለማርያምና ሸዋ ሮቢት ከተሞች ከሐምሌ 24- ጳጉሜን 4 ቀን 2015 ዓ.ም ድረስ ተስፋፍተው የተፈጸሙ መሆኑም ተጠቅሷል።
የግድያዎቹ ሰለባዎች ከሆኑት መካከል ቤት ለቤት በተደረገ ፍተሻ የተያዙ፣ በግጭቱ ወቅት መንገድ ላይ የተገኙ እና ያልታጠቁ ሰዎች፣ “ የጦር መሳሪያ ደብቃችኋል አምጡ” በሚል የተያዙ ሰዎች ይገኙበታል ብሏል።
ወራትን ባስቆጠረው የአማራ ክልል ግጭት በተለያዩ አካባቢዎች ሰላማዊ ሰዎች ኢላማ እየተደረጉ መሆናቸውን እና የሰብዓዊ መብት ጥሰት እየተፈጸመ መሆኑን የመብት ተሟጋች ድርጅቶች በተደጋጋሚ መግለጻቸው ይታወሳል።
የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት ባወጣው ሪፖርት በክልሉ በተቀሰቀሰው ግጭት ምክንያት ከ180 በላይ ንጹሃን ዜጎች መገደላቸውን ገልጿል።
በአዲሱ ዓመት መባቻ ለተወሰነ ጊዜ የተረጋጋ መስሎ የነበረው የአማራ ክልል ግጭት ሰሞኑን እንደገና አገርሽቶ በተለያዩ አካባቢዎች ውጊያ እየተካሄደ ነው።
ኢሰመኮ በአማራ ክልል ግጭቱ ወደ ክልሉ ልዩ ልዩ ወረዳዎችን መስፋፋቱን ከነዋሪዎች፣ ከተጎጂዎች፣ ከተጎጂ ቤተሰቦች እና ከዓይን እማኞች መረጃዎችን ሰብስቤያለሁ ሲል ከሰሞኑ ባወጣው መግለጫ ማስታወቁ ይታወሳል።
በደብረ ማርቆስ፣ በአዴትና መራዊ፣ በደብረ ታቦር፣ በማዕከላዊ ጎንደር ዞን ደልጊ፣ በማጀቴ፣ በሸዋ ሮቢት እና አንጾኪያ ከተሞች ከነሐሴ 19 እስከ ነሐሴ 30 በደረሱ ግጭቶች የንጹሃን ህይወት መቀጠፉንም ኢሰመኮ ገልጿል።
በእነዚህ ከተሞች አንዳንድ የገጠር ቀበሌዎች በተኩስ ልውውጥ ወይም በከባድ መሳሪያ ተኩስ በርካታ ሰላማዊ ነዋሪዎች መሞታቸውን፣ ለአካል ጉዳት መዳረጋቸውን እና ንብረት መውደሙን የገለጸው ኢሰመኮ ምን ያህል ሰዎች እንደሞቱ ግን ያለው ነገር የለም።
ከሳምንታት በፊት የኢትዮጵያ መከላከያ ሰራዊት ኢታማዦር ሹም ብርሃኑ ጁላ “የፋኖ ታጣቂዎችን ስጋት ወደማይሆኑበት ደረጃ አድርሰናቸዋል” ብለው ነበር። የአማራ ክልል መንግሥትም ሁሉም አካባቢዎች ወደ ሰላማዊ እንቅስቃሴ መመለሳቸውን ገልጾ ነበር።
በክልሉ በመከላከያ ሰራዊት እና በፋኖ ታጣቂዎች መካከል እየተካሄደ ያለው ውጊያ ረገብ ብሎ እንደነበር የተዘገበ ቢሆንም ከአዲስ ዓመት በኋላ ግጭቱ ስለማገርሸቱ አንዳንድ መረጃዎች እየወጡ ይገኛሉ።
ግጭቱን ተከትሎ እስካሁን በመንግሥት በኩል የተባለ ነገር የለም። የፋኖ ታጣቂዎች ደጋፊ የሆኑ ብዙሃን መገናኛዎች ፋኖ አንዳንድ ከተሞችን መልሶ መቆጣጠሩን እየገለጹ ቢሆንም ቢቢሲ መረጃውን ከገለልተኛ ወገን ማጣራት አልቻለም።












