ምግብ ቤቶች የባለቤትነት ጥያቄ ለፍርድ ቤት ያቀረቡበት የሕንድ ‘የዶሮ ወጥ’ አዘገጃጀት

በተር ቺክን የተሰኘው ምግብ

የፎቶው ባለመብት, Getty Images

የምስሉ መግለጫ, በተር ቺክን የተሰኘው ምግብ

አንዳንድ ምግቦች ከፈጠሯቸው ማኅበረሰቦች አልፈው በመላው ዓለም ተወዳጅነትን ያገኛሉ።

በዚህ ዘርፍ የሕንድ ዶሮ፣ የኢትዮጵያው እንጀራ፣ የጃፓን ሱሺ፣ የቻይና ኩንግ ፓዎ፣ የሜክሲካውያኑ ታኮ ተጠቃሾች ናቸው።

በተለይ በበርካታ ቅመሞች የሚታወቀው የሕንዳውያን ምግቦች አገር እና ቋንቋ ሳይገድባቸው ባሕር አቋርጠው ኢትዮጵያን ጨምሮ በበርካታ አገራት ይገኛሉ።

ምናልባት ሕንድን ባይጎበኙም እጅ ያስቆረጥማል የሚባለውን ‘በተር ቺክን’ ቀምሰው ይሆናል።

በዓለም ዙሪያ በጣፋጭነቱ የሚታወቀው ‘በተር ቺክን’ (‘ዶሮ በቅቤ’ እንበለው ) ባለቤትነቱ ላይ የሕንድ ሁለት ጥንታዊ ሬስቶራንቶች በፍርድ ቤት እየተከራከሩበት ይገኛሉ። የምግብ ቤቶቹ ባለቤቶች የምግቡ የፈጠራ ባለቤትነት ይሰጠን በሚልም አንደኛው አንዱን ፍርድ ቤት ገትሮታል።

በሕንድ ውስጥ ታዋቂውን ‘በተር ቺክን’ ከሚያቀርቡት ሬስቶራንቶች ጉላቲ የተሰኘው ሬስቶራንት ሁልጊዜም በደንበኞች እንደተሞላ ነው።

ከጫፍ እስከ ጫፍ የተነገረለትን ‘በተር ቺክን’ ለማግኘት ወረፋ እና ሰልፍ ይጠብቅዎታል።

ቢቢሲም በስፍራው በተገኘበት ወቅት ደንበኞችን ለማስተናገድ አስተናጋጆች ሲራወጡ አይቷል። ሕንዳውያን ብቻ ሳይሆኑ አገሪቷን ሊጎበኙ የመጡ ቱሪስቶች በመዲናዋ ደልሂ የሚገኘውን ይህንን ሬስቶራንት ሳይረግጡ እና ብዙ የተባለለትን ‘በተር ቺክን’ ሳይቀምሱ አይወጡም።

በሕንድ ሰርጎች ላይ ዋነኛ የድግስ ምግብ የሆነው እና መነሻውን የምግቡን ባለቤትነት በተመለከተ ፍርድ ቤት ብይን እንዲሰጥበት የተጠየቀበት ‘በተር ቺክን’ ሕንድን ለሁለት ከከፈላት ታሪካዊ ክስተት ጋር ጠንካራ ግንኙነት አለው።

ትንሽ ታሪካዊ ዳራውን እንመልከት። ከጨቋኙ የብሪታንያ ቅኝ ግዛት ነጻ የወጣችው ሕንድ በአውሮፓውያኑ 1947 ለሁለት ተከፈለች። ፓኪስታን እና ሕንድ በሚል። በኋላ ደግሞ ምሥራቃዊ ፓኪስታን፣ ባንግላዴሽ በሚል ሌላ አገር ተመሠረተች።

ግን ይህ ሁሉ ከመሆኑ በፊት ሕንድ አንድ አገር እያለች ሞክሃ ሲንግ የሚባል አንድ ግለሰብ በአሁኑ ወቅት በፓኪስታን ውስጥ በምትገኘው ፔሻዋር ከተማ አንድ ሬስቶራንት ነበረው። የፓኪስታንን በአገርነት መመሥረት ተከትሎ ሲንግ አብረውት ይሠሩ ከነበሩ ሦስት ሠራተኞች ጋር አንድ ምግብ ቤት በደልሂ ከፈቱ።

ሦስቱ ሠራተኞችም ኩንዳን ላል ጉጅራል፣ የጉጅራል የአጎት ልጅ ኩንዳን ላል ጃጊ እና ታኩር ዳስ ማጎ ናቸው።

በደልሂ፣ ዳሪያጋንጅ ተብሎ በሚታወቀው ሰፈር ነው ፔሽዋር እያሉ ይሠሩት የነበረው። ምግቡንም [‘በተር ቺክን’] በቲማቲም መረቅ፣ ቅቤ እና በቅመሞች ያበደ አድርገው መሥራት የጀመሩት። ምግቡ መነሻው ታንዱሪ ቺክን ከሚባለው የዶሮ ጥብስ እንደሆነ ይነገራል።

በተር ቺክን የተሰኘው ምግብ

የፎቶው ባለመብት, Gulati

Skip podcast promotion and continue reading
የቢቢሲ አማርኛ ዩቲዩብ ቻናል

ዜና፣ ትንታኔ እና ታሪኮችን በምሥል እና በድምጽ ለማግኘት

ይህንን በመጫን ሰብስክራይብ ያድርጉ

End of podcast promotion

ወደ አሁኑ ወቅት እንመለስ የጉጅራል የልጅ ልጆች የዶሮ አዘገጃጀቱን እንዳለ ይዘው አሻራውንም ለበርካታ አስርት ዓመታት አስቀጠሉ።

ሆኖም በአውሮፓውያኑ 2019 ከሦስቱ ሠራተኞች አንዱ የነበረው የጃጊ የልጅ ልጅ ዳርያጋንጅ የሚባል በርካታ ቅርንጫፎች ያሉት ተቀናቃኝ የምግብ ቤቶች ሰንሰለት ከፈተ። ይህም ብቻ አይደለም የምግብ ቤቶቹን መለያ “የበተር ቺክን” ፈጣሪዎች በሚል ነበር ያስተዋወቀው።

ከጥቂት ወራት በፊትም የሞቲ ማሃል ዴሉክስ ባለቤት የሆነው የጉጅራል የልጅ ልጅ ሞኒሽ በዚህ ዳርያጋንጅ በተሰኘው ሬስቶራንት ላይ ክስ መሠረተ።

ክሱ እንደሚያሳየው ‘በተር ቺክን’ን የፈጠረው የሞኒሽ አያት ጉጅራል ብቻውን እንደሆነ እና ምግብ ቤቶቹ ምግቡን ፈጥረናል ብለው በማስተዋወቃቸው ጉዳት አድርሰዋል የሚል ነበር።

የዳርያጋንጅ ሬስቶራንቶች ዋና ሥራ አስፈጻሚ የሆነው ባጋ የ’በተር ቺክን’ ፈጣሪዎች የሚለውን መለያ የመጠቀም መብት እንዳላቸው አጥብቆ ይከራከራል።

ባጋ እንደ መከራከሪያ የሚጠቅሰውም በአውሮፓውያኑ 2018 ይህንን መለያ የሚያረጋግጥ የንግድ ሰርቲፊኬት ነው።

ሌላኛው ደግሞ የሚጠቅሰው ምግቡ የተፈጠረበት ሬስቶራንት ባለቤቶቹ ጉጅራል እና ጃጊ በጋራ መሆኑን የማስረጃ ውል አለ ይላል።

በተር ቺክንን የፈጠረው የማን አያት ነው የሚለው ላይ እርግጠኛ መሆን አይቻልም የሚለው ባጋ ምናልባትም በትብብር አዘገጃጀቱን እንዳመጡት ያምናል።

“ጃጊን ከመሞቱ በፊት እንዴት እንደፈጠሩት ጠይቄው፤ አስበውበት ሳይሆን በድንገት እንደሠሩት ተናግሯል። እናም በአጋጣሚ የተፈጠረ ነው” ይላል።

ሕንድ ለሁለት ከመከፈሏ በፊት፣ ከስምንት አስርታት ዓመት በፊት የተፈጠረው ይህ የዶሮ አዘገጃጀት በአስደናቂ ሁኔታ ተሻሽሏል። በርካታ ነገሮች ተጨምረውበታል። እሱ ብቻ አይደለም በበተር ቺክን ተነሳስተው አዳዲስ የምግብ ዓይነቶችን ተፈጥረዋል።

ባለፈው ዓመት በሙምባይ አንድ ባር የበተር ቺክን ኮክቴል (የአልኮል ድብልቆች መጠጥ) አዘጋጅቶ መነጋገሪያ ሆኖ ነበር።

የበተር ቺክን መረቅ ጣዕም ያለው ይህ መጠጥ ቅመም እና ቮድካም አለው።

ይህ ብቻ አይደለም በደልሂ ‘በተር ቺክን ፒዛ’ የሚያቀርቡ ሬስቶራንቶች ስፍር ቁጥር የለውም።

በደልሂ የሚገኘው ሻንግሪ ላ ኢሮስ የተሰኘው ሆቴል ደግሞ በበተር ቺክን ላይ አዲስ ፈጠራ ጨምሮበት ሳምቡሳ ያበስላል።

“ዋናው ነገር የቲማቲም ጣዕሙ ነው” የሚሉት የሆቴሉ ዋናው ሼፍ ጋግንዲፕ ሲንግ ሳውህነይ አዳዲስ ፈጠራዎች መጨመራቸው ላይ ቢስማሙም “ትክክለኛውን ጣዕም መጠበቅ መሠረታዊ ነው” ይላሉ።

ቢቢሲ የዳርያጋንጅ ሰንሰለት አንዱ በሆነው የኤሮሲቲ ምግብ ቤት ተገኝቶ ነበር። በሕንዳዊ የሥነ ሕንጻ፣ እና ጥበቦች ያሸበረቀውን ይህንን ሬስቶራንት የጎበኙ ታዋቂ ዘፋኞች እና ፖለቲከኞች ፎቶዎች ተሰቅለዋል።

ታዋቂውን በተር ቺክን ያዘዙት የቢቢሲ ጋዜጠኞች እጅ የሚያስቆረጥመውን ምግብ አጣጥመው፣ ባለቤቶቹም እንዴት መፍጫዎች በሌሉበት ጊዜ ይሠራ ከነበረው ጋር ለማመሳሰል እና ዋና ይዘቱ ሳይቀየር ለመጠበቅ እንደሚያበስሉ አስረዷቸው።

የዳርያጋንጅ ሬስቶራንት

የፎቶው ባለመብት, Tamara Hinson

በመቀጠል ደግሞ የጉጅራል የልጅ ልጅ ምግብ ቤት ወደ ሆነው ሞቲ ማሃል ዴሉክስ አቀኑ። በዚያም የቀረበላቸው በተር ቺክን ጣዕሙ ግሩም ነበር፣ ደስ የሚልም የሚያቃጥል ስሜት አለው። ሁለቱ ሬስቶራንቶች ምግባቸው ጣፋጭ ቢሆንም የመረቁ አሠራር ግን ልዩነት አለው።

ስለ አዘገጃጀቱ ዝርዝር የሞቲ ማሃል ዴሉክስ ባለቤቶች በተጠየቁበት ወቅት መጀመሪያ ላይ ቢስማሙም በኋላ ላይ ውድቅ አደረጉት።

የሬስቶራንቱ ቃል አቀባይ በፍርድ ቤቱ ክስ ምክንያት ስለ ምግቡ መናገር እንደማይችል አስታወቀ። የሞቲ ማሃል ዴሉክስ ባለቤቶች የማያሸንፉትን ክስ መሥርተው ተጸጽተው ይሆን የሚል ጥያቄ መፍጠሩ አልቀረም።

ማንኛውም ግለሰብ አንድን ምግብ ባለቤትነቱ የእኔ ነው ወይም ፈጥሬዋለሁ የሚለውን ሃሳብ ለመቀበል ከባድ ነው የሚሉት በሼፈልድ ዩኒቨርስቲ በደቡብ እስያ የባህል ታሪክ እና የምግብ ታሪክ ተመራማሪ የሆኑት ዶክተር ኔሃ ቬርማኒ ናቸው።

የሕንድ መከፈልን ተከትሎ ከፔሽዋር ማቄን ጨርቄን ሳይሉ የተሰደዱ ሂንዱ ፑንጃቢዎችም ይህንኑ ምግብ ይሠሩ እንደነበር ይጠቀሳል።

እንደ በተር ችክን ያሉ ምግቦችን አንድ ሰው ሆን ብሎ ፈጠረው የሚለው እሳቤ የሌሎችን አስተዋጽኦ የሚያደበዝዙ እና የሚያጠፉ እንደሆነ ዶክተር ኔሃ ያስረዳሉ።

“የትኛውንም ምግብ እኔ ነኝ የፈጠርኩት ማለት የሚችል ሰው የለም” የሚሉት ተመራማሪዋ “የምግብ ታሪክ የሚያስተምረን አንደኛው ጉዳይ ምግቦች እና የምግቦች አዘጋጃጀቶች ከጊዜ ወደ ጊዜ ፈጠራ እየተጨመረባቸው፣ እየተሻሻሉ እና እየተቀየሩ ይመጣሉ።

“ለዚህም በርካታ ሰዎች፣ ማኅበረሰቦች በክፍለ ዘመናት ውስጥ አሻራቸውን ጥለዋል። በተር ቺክንን በምናይበት ወቅት አትላንቲክን ተሻግረው ይነግዱ የነበሩ ሰዎች ቲማቲምን ወደ ደቡብ እስያ ባያመጡት ኖሮ ምግቡንም አናየውም ነበር። ይህንን ፍሬ ተቀብለው እንዲበቅል ያደረጉ ማኅበረሰቦችም መጠቀስ አለባቸው” ይላሉ።

ይህ በእንዲህ እንዳለ ወደ ባጋ እንመለስ “የፍርድ ቤቱ ክስ የማን አያት በተር ቺክንን ፈጠረ የሚለው ነው። ነገር ግን የትኛው እንደፈጠረው ማን ያውቃል” ሲልም ይጠይቃል።

ከክሱ ጋርም ተያይዞ የምግብ ቤቶቹ ስም በዓለም አቀፍ ሚዲያዎች ርዕሰ ዜና መሆኑን ተከትሎ ሽያጫቸው በከፍተኛ ሁኔታ እንደጨመረ ነው ባጋ የሚናገረው። የማስታወቂያ መጥፎ የለውም እንደሚባለው ለዚያ ይሆናል ባጋ ጉዳዩን በበጎ የተመለከተው።