በታንዛኒያ በመኪና አደጋ 9 ኢትዮጵያውያን ስደተኞች ሲሞቱ ሰባቱ ጉዳት ደረሰባቸው

ስደተኞች

የፎቶው ባለመብት, IOM

የምስሉ መግለጫ, በርካታ ኢትዮጵያውያን ወደ ደቡብ አፍሪካ በሚያደርጓቸው ሕገወጥ ፍልሰቶች ምክንያት ለችግር ይዳረጋሉ

ታንዛኒያ ውስጥ ኢትዮጵያውያን ናቸው የተባሉ ስደተኞችን አሳፍሮ በሚሄድ መኪና ላይ በደረሰ የትራፊክ አደጋ የሰባቱ ሕይወት ሲያልፍ ዘጠኙ ጉዳት እንደ ደረሰባቸው ዓለም አቀፉ የስደተኞች ድርጅት አስታወቀ።

የመንግሥታቱ ድርጅት የስደተኞች ድርጅት ሐሙስ መስከረም 17/2016 ዓ.ም. ስለ አደጋው ባወጣው መግለጫ ላይ እንዳስታወቀው አደጋው የደረሰው በታንዛኒያዋ ንጆምቤ ክልል ውስጥ ነው።

አደጋው ከሁለት ሳምንት በፊት መስከረም 03/2016 ዓ.ም. የደረሰ ቢሆንም ለድርጅቱ ሪፖርቱ የደረሰው ከአደጋው ከበርካታ ቀናት በኋላ ነው።

በደቡባዊ የታንዛኒያ ግዛት ንጆምቤ ውስጥ አደጋው የደረሰበት ተሽከርካሪ ኢትዮጵያውያን ናቸው የተባሉ 29 ስደተኞችን አሳፍሮ እየተጓዘ ነበር ተብሏል።

መኪናው ኢትዮጵያውያኑን አሳፍሮ ከጎረቤት ዛምቢያ ጋር ወደ ምትዋሰነው ዛምቢያ እየተጓዘ ሳለ ነው አሰቃቂው አደጋ የደረሰበት። በአደጋው ሰባት ሰዎች ሰዎች ሲሞቱ፣ 9 ደግሞ ጉዳት የደረሰባቸው ሲሆን የቀሩት 13ቱ ያሉበት ሁኔታ አለመታወቁን ድርጅቱ አመልክቷል።

በስደተኞቹ ላይ በደረሰው አደጋ የተሰማውን ጥልቅ ሐዘን የገለጸው ዓለም አቀፉ የስደተኞች ድርጅት (አይኦኤም)፣ ታንዛኒያ ውስጥ የሚገኙ ሠራተኞቹ እና የኢትዮጵያ ኤምባሲ ባልደረቦች በአደጋው ስፍራው ተገኝተው መረጃዎችን እና ድጋፍ በመስጠት ላይ ናቸው ብሏል።

አይኦኤም እንዳለው እንዲህ ያለው አሰቃቂ ሁኔታን ለማስቆም ከአፍሪካ ቀንድ ወደ ደቡብ አፍሪካ በሚደረገው ፍልሰት ስደተኞች የሚገጥሟቸውን ውስብስብ ፈተናዎች ለመቅረፍ አጠቃላይ መፍትሄ እንደሚያስፈልግ አመላካች ነው።

ባለፉት በርካታ ዓመታት ከፍተኛ ቁጥር ያላቸው ኢትዮጵያውያን በኬንያ፣ በታንዛኒያ፣ በዛምቢያ እና በማላዊ አድርገው በሕገወጥ መንገድ በሚያደርጓቸው ጉዞዎች ምክንያት ለተለያዩ ችግሮች ሲዳረጉ መቆየታቸው ይታወቃል።

ባለፈው ዓመት ጥቅምት ወር ላይ በማላዊ ውስጥ የ25 ኢትዮጵያውያን ስደተኞች የጅምላ መቃብር ምዚምባ በሚባለው የማላዊ ሰሜናዊ ግዛት በሚገኝ ደን ውስጥ መገኘቱን የአገሪቱ ፖሊስ ማስታወቁ ይታወሳል።

እንዲሁም በኅዳር ወር ላይ ኢትዮጵያውያን ናቸው የተባሉት የ27 ሰዎች አስከሬን በዛምቢያ መዲና ሉሳካ አቅራቢያ በሚገኝ መንገድ ዳር “ተጥለው” መገኘታቸው አይዘነጋም።

ከዚህ ባሻገርም የተለያየ ቁጥር ያላቸው ኢትዮጵያውያን ስደተኞች በሚያደርጓቸው ሕገወጥ ጉዞዎች ምክንያት በምሥራቃዊ እና ደቡባዊ አፍሪካ አገራት ውስጥ ለጉዳት እና ለከእስር እየተዳረጉ ነው።

በርካታ ኢትዮጵያውያን ወጣቶች የተሻለ ሕይወትን ፍለጋ በሕገወጥ መንገድ አደገኛ በሆነ ሁኔታ በርካታ አገራትን በማቆራረጥ ደቡብ አፍሪካ ለመግባት ይሞክራሉ።

የኬንያ፣ የታንዛኒያ፣ የማላዊ እና የዛምቢያ ፖሊሶች በሕገ ወጥ የሰዎች አዘዋዋሪዎች ድንበር ያቋረጡ ናቸው ያሏቸውን በርካታ ኢትዮጵያውያንን መያዛቸውን በተደጋጋሚ ሲዘገብ ቆይቷል።

አሁንም ድረስ በርካቶች የአገራቱን ድንበሮች በሕገወጥ መንገድ በመሻገር ክስ ተመስርቶባቸው በእስር ላይ ይገኛሉ።

ከዚህ ባሻገርም በርካታ ኢትዮጵያውን ስደተኞች በረሃብ እና በውሃ ጥም፣ በአውሬ በመበላት እና አሁን እንዳጋጠመው በርካታ ሆነው ተጨናንቀው በድብቅ በሚጓዙባቸው ተሽከርካሪዎች ውስጥ ታፍነው ለሞት ተዳርገዋል።

የተባበሩት መንግሥታት የስደተኞች ድርጅት (አይኤምኦ) እንደሚለው ከአውሮፓውያኑ 2014 አንስቶ በአፍሪካ ውስጥ 12ሺህ የሚሆኑ ስደተኞች የደረሱበት እንደማይታወቅ መዝግቧል።