የትራምፕ አስተዳደር ጥቁር አሜሪካዊቷን የገደለውን ፖሊስ ለአንድ ቀን ብቻ እንዲታሰር ጠየቀ

የፎቶው ባለመብት, Getty Images
የትራምፕ አስተዳደር አንዲት ጥቁር አሜሪካዊትን በቤቷ ውስጥ ሳለች የገደለውን የቀድሞ የኬንታኪ ፖሊስ በአንድ ቀን እስራት እንዲቀጣ ጠየቀ።
የፌደራል ዳኛ የቀድሞው የፖሊስ መኮንን ብሬት ሃንኪሰን ከልክ ያለፈ ኃይል በመጠቀም የቴይለርን የሲቪል መብቶች በመጣስ ጥፋተኛ ብሎታል።
በዚህ ክስ ከፍተኛው ቅጣት የእድሜ ልክ እስራት ነው።
ዳኛው በአሜሪካ የፍትህ ቢሮ የውሳኔ ሃሳብ ከተስማሙ ሃንኪሰን አንድ ቀን ብቻ በእስር ቤት እንደሚቆይ እና ይህንንም አስቀድሞ በማጠናቀቁ የሚለቀቅ ይሆናል።
የቴይለር ቤተሰብን የሚወክሉ ጠበቆች ድርጊቱን "ለብሬኦና ቴይለርን ሕይወት ስድብ" ሲሉ ተቃውመዋል።
የቴይለር ቤተሰብ ጠበቆች በሰጡት መግለጫ "በሕግ እኩል ፍትህ አለ ብሎ የሚያምን አሜሪካዊ ሁሉ ሊቆጣ ይገባል" ብለዋል።
"አንድ ቀን ብቻ በእስር ቤት እንዲቆይ የሚል የውሳኔ ሃሳብ ማቅረብ ነጭ የፖሊስ መኮንኖች የጥቁር አሜሪካውያን ዜጎች መብትን ቢጥሱ ምንም ቅጣት እንደማይገጥማቸው የማያሻማ መልዕክት ያስተላልፋል።"
ከዚህ ግድያ ጋር በተያያዘ የተከሰሰው እና የተፈረደበት ብሬት ሃንኪሰን ብቻ ነው።
የፌደራል ዐቃቤ ሕጎች የዳኞች ብይን ሃንኪሰን እንደገና የፖሊስ መኮንን መሆን እንደማይችል ስለሚል ተጨማሪ የእስር ጊዜ መጣል "በዚህ ሁኔታ ላይ ኢ-ፍትሃዊ ይሆናል" ብለዋል።
ከአንድ ቀን ቅጣት በተጨማሪ የፍትህ ቢሮው የፖሊስ መኮንኑ ተለቅቆ ለሦስት ዓመት ክትትል እየተደረገበት እንዲቆይ ሲሉ ዳኛውን ጠይቀዋል።
ፖሊስ የሟችን ቤት በሚበረብርበት ወቅት "የፍተሻ ማዘዣውን በመፈጸም" ውስጥ የተሳተፈ ቢሆንም፣ ቴይለር ላይ አልተኮሰም "ለሞቷም ተጠያቂ አይደለም" ሲል አቃቤ ሕግ ተከራክሯል።
ቴይለር ከተገደለች በኋላ የጆርጅ ፍሎይድን ግድያ ተከትሎ በ2020 የተቀሰቀሰው 'የብላክ ላይቭስ ማተር' የተቃውሞ ሠልፍ ላይ መፈክር ሆና ነበር።
ቴይለር የተገደለችው ሲቪል ልብስ የለበሱ መኮንኖች በቤቷ ውስጥ የፍተሻ ማዘዣ ይዘው ቤቷን ለመበርበር ከገቡ በኋላ ነው።
ፖሊሶች ወደ አፓርታማዋ የገቡት እሷ እና የወንድ ጓደኛዋ ኬኔት ዎከር ተኝተው ባሉበት ወቅት ነው።
ባለሥልጣናቱ የቴይለር የቀድሞ የወንድ ጓደኛ ቤቷን አደንዛዥ ዕፅ ለመደበቅ እንደሚጠቀምበት እንደሚያምኑ ተናግረዋል።
ፖሊሶች በሩን ገንጥለው ሲገቡ ዎከር አንድ ጥይት ተኩሶ አንዱን የፖሊስ ባልደረባ እግሩን መትቶታል።
ዎከር ፖሊሶች ማንነታቸውን ሳያሳውቁ ወደ መኖርያ ቤቱ ሲገቡ ሌቦች መስለውኝ ነው ሲል ተናግሯል።
ሦስቱ ፖሊሶች ለዎከር ተኩስ ምላሽ በመስጠት 32 ጥይቶችን ተኩሰዋል።
ሃንኪንሰን ባልደረቦቹን ለመከላከል 10 ጊዜ መተኮሱን ለችሎቱ አስረድቷል።
የትኛውም የሃንኪሰን ጥይት ማንንም አልመታም፤ ነገር ግን አንዲት ነፍሰ ጡር ሴት፣ የአምስት ዓመት ሕጻን እና አንድ ወንድ ተኝተው ወደነበሩበት ቤት ዘልቀው ገብተዋል።
ሃንኪሰን በሰኔ 2020 ከሉዊስቪል ሜትሮ ፖሊስ መምሪያ ተባርሯል።
ዳኛው በሚቀጥለው ሳምንት የቅጣት ውሳኔ ለመስጠት በተያዘው ቀጠሮ ወቅት የመንግሥትን ጥያቄ ይመለከታሉ።















