ኢንዶኔዢያ ከጋብቻ ውጪ የሚፈጸም ወሲብን በእስር የሚያስቀጣ ወንጀል ልታደርግ ነው

የፎቶው ባለመብት, HOTLI SIMANJUNTAK/EPA-EFE/REX/SHUTTERSTOCK
የኢንዶኔዢያ ምክር ቤት ከጋብቻ በፊት የሚደረግን ወሲባዊ ግንኙነት አስከ አንድ ዓመት በሚደርስ እስር የሚያስቀጣውን አዲሱን የአገሪቱን የወንጀለኛ መቅጫ ሕግ ሊያጸድቅ ነው።
ሕጉን በማርቀቅ የተሳተፉት አንድ የአገሪቱ ፖለቲከኛ እንደተናገሩት የወንጀለኛ መቅጫ ሕጉ በሚቀጥለው ሳምንት ለፓርላማው ቀርቦ ይጸድቃል።
ምር ቤቱ አዲሱን የወንጀለኛ መቅጫ ሕግ ሲያጸድቀው፣ በአገሪቱ ውስጥ በሚገኙ ኢንዶኔዢያውያንም ሆኑ በሌሎች አገራት ዜጎች ላይ በተመሳሳይ ተግባራዊ ይሆናል።
ይህ ቅጣት የሚፈጸመው የዝሙት ድርጊቱ መፈጸሙን በተመለከተ ለሚመለከታቸው ባለሥልጣናት ክስ ያቀረቡ ወገኖች ሲኖሩ ነው።
በጋብቻ ውስጥ ያሉ ሰዎች ዝሙት ከፈጸሙ፣ ክሱን ማቅረብ የሚችሉት ድርጊቱን ፈጽመዋል የተባሉት ግለሰቦች ባል ወይም ሚስት ይሆናሉ።
በተጨማሪም ጋብቻ ያለመሰረቱ ሰዎች በዝሙት ድርጊት ላይ ተገኝተዋል ከተባሉ ክሱ የሚመሰረትባቸው በወላጆቻቸው አማካይነት ነው።
ሕጉ ጥንዶች ከጋብቻ ውጪ አብረው እንዳይኖሩ የሚከለክል ሲሆን፣ ይህንን ተላልፈው የሚገኙ ካሉም እስከ ስድስት ወራት በሚደርስ እስር ሊቀጡ ይችላሉ።
ሮይተርስ የዜና ወኪል እንደዘገበው ይህ ሕግ የኢንዶኔዢያን የመዝናኛ እና የኢንቨስትመንት ዘርፍ ገጽታን ሊያበላሽ ይችላል ሲሉ በንግድ ዘርፍ ላይ የተሰማሩ ቡድኖች ስጋታቸውን ገልጸዋል።
የኢንዶኔዢያ ቀጣሪዎች ማኅበር ምክትል ሊቀመንበር እንዳሉት “የሕጉ ተግባራዊ መሆን በኢንቨስተሮች ዘንድ ሕጋዊ ስጋትን በመፍጠር በኢንዶኔዢያ ውስጥ ያላቸውን መዋዕለ ነዋይ የማፍሰስ ዕቅድ መልሰው እንዲያጤኑ ያደርጋል።”
የዚህ ሕግ ረቂቅ ከሦስት ዓመት በፊት እንዲጸድቅ ለአገሪቱ ምክር ቤት ቀርቦ የነበረ ሲሆን፣ ነገር ግን በመላዋ አገሪቱ በአስር ሺዎች የተሳተፉባቸው የተቃውሞ ሰልፎች እንዲካሄዱ ምክንያት ሆኖ ነበር።
ተማሪዎችን ጨምሮ በርካቶች በዋና ከተማዋ ጃካርታ እና በአገሪቱ ባሉ ሌሎች ከተሞች ውስጥ ለተቃውሞ አደባባይ ወጥተው ግጭት ተከስቶ ነበር።
ተቃዋሚዎች በፖሊስ ላይ ድንጋይ በመወርወር ጥቃት የሰነዘሩ ሲሆን፣ ፖሊስም በተቃዋሚዎቹ ላይ አስለቃሽ ጋዝ እና ውሃ በመርጨት ለመበተን ሞክሯል።
አሁን በኢንዶኔዢያ ይጸድቃል የተባለው አይነት በወሲብና በግንኙነት ዙሪያ ጥብቅ ሕግ ማውጣት ብዙሃኑ ሙስሊም በሆነባቸው የአገሪቱ ክፍሎች ውስጥ ከዚህ በፊት አጋጥሟል።
አቼ የተባለችው ግዛት ጥብቅ የሆነ እስላማዊ ሕግን ተግባራዊ በማድረግ ቁማር፣ አልኮል መጠጣት እና ከተቃራኒ ጾታ አባላት ጋር በአንድ ላይ መገናኘት የሚያስቀጣ ጥፋት እንዲሁን አድርጋለች።
በዚህም ሳቢያ አንዲት ሴት እና ወንድ በጣም ተጠጋግተው ተገኝተዋል በሚል 20 ጊዜ በጅራፍ ተገርፈዋል። በተመሳሳዕ ሁለት ወንዶች አልኮል ጠጥተዋል ተብለው 40 ጅራፍ ተገርፈዋል።












