አልቀመስ ያለው የዓለም ዋንጫ ተሳታፊ ብሔራዊ ቡድኖች የማሊያ ዋጋ

ኳታር እያስተናገደች ያለው የ2022 የፊፋ የዓለም ዋንጫ እጅግ ውድ የሆነው የዓለም ዋንጫ ብቻ አይደለም።
በዓለም ዙሪያ ያሉ ደጋፊዎች የሚወዷቸውን የብሔራዊ ቡድኖቻቸውን ማሊያ ለመግዛት ከፍተኛ ገንዘብ ማውጣት አለባቸው።
በአንዳንድ አገሮች አንድ ሰው በወር ከሚያገኘው ዝቅተኛ ደመወዝ ከአንድ ሦስተኛ በላይ ማውጣት ይጠበቅባቸዋል ማለት ነው።
ጃኒን ጋርሺያ የጎዳና ንግድ በሚደራበት የሪዮ ዴ ጄኔሮ ሰሜናዊ ክፍል ሳንስ ፔና አደባባይ ላይ ያለውን ድንኳን ስታይ ሁለት ጊዜ አላሰበችም። ከየአቅጣጫው በተንጠለጠሉ በመቶዎች በሚቆጠሩ የብራዚል ብሔራዊ ቡድን ማሊያዎች ያጌጠ ቢጫ እና ሰማያዊ መብራት ነበር።
የ42 ዓመቷ መምህርት እየሳቀች “ሰማያዊ ወሰድኩ (የብራዚል ሁለተኛ ማሊያ)። በጣም የሚያምር ስለነበር ብዙ የሥራ ባልደረቦቼ እና ጓደኞቼ እንድገዛላቸው ጠይቀውኛል” ብላለች።
ጋርሺያ ለማሊያው 14 ዶላር ነው ያወጣችው። ይህም በአሜሪካው ግዙፍ የስፖርት ትጥቅ አምራች ናይኪ ከሚሸጥበት ዋጋ አንድ አምስተኛ (65 ዶላር) ያህል ነው። በ2022 የዓለም ዋንጫ ላይ የብራዚል ተጫዋቾች ከለበሱት ማሊያ ጋር ተመሳሳይ የሆነ ፕሪሚየም ጥራት ያለው አለ፤ ይህ ግን 130 ዶላር ያስከፍላል።
በብራዚል ዝቅተኛው ደመወዝ 225 ዶላር አካባቢ ነው። የርካሹ ማሊያ የዚህን ደሞዝ 30 በመቶ የሚጠጋ ሲሆን ውድ የሆነው ማሊያ ደግሞ 58 በመቶ አካባቢ ነው።
የዋጋ ጭማሪ
“የእግር ኳስ ማሊያዎች ለእኛ የቅንጦት ዕቃ ሆነዋል” ትላለች ጋርሺያ።
በመስከረም ወር ላይ የብራዚል የቢዝነስ መጽሔት “ኤግዛሜ” ባወጣው መጣጥፍ፣ ከዓለም ዋንጫው በፊት ይፋ የሆነው አዲሱ የብራዚል ማሊያ ከአራት ዓመታት በፊት ከወጣው ዋጋው 40 በመቶ ጨምሯል ሲል ዘግቧል።
ነገር ግን የማሊያ ዋጋ መናር ግርምትን የፈጠረባት፣ ቅሬታ ያስነሳባት አገር ብራዚል ብቻ አይደለችም።
ትልቅ የኢኮኖሚ ቀውስ በተጋፈጠችው እንግሊዝም ለ2022 የዓለም ዋንጫ የተዘጋጀው ማሊያ እስካሁን ከተሸጡት ሁሉ እጅግ ውድ የሚባል ነው (መደበኛ የሚባለው ማሊያ 85 ዶላር ይሸጣል)። ቀደም ሲል የነበረው የዋጋ ጭማሪ የቀድሞ ጠቅላይ ሚኒስትር ዴቪድ ካሜሮንን ጨምሮ ከበርካታ ፖለቲከኞች ወቀሳ ደርሶበታል።
ካሜሮን እአአ በ2014 ለቢቢሲ “በጣም ውድ ነው። ወላጆች አዲሱን ማሊያ ለመግዛት ከፍተኛ ጫና ውስጥ ይገባሉ። እኛ መጠቀሚያ ልንሆን አይገባም” ሲሉ ገልጸው ነበር።
ያለፈው ውድድር አሸናፊ ፈረንሳይ ደጋፊዎች ለማሊያ 93 ዶላርአካባቢ ያወጣሉ ተብሎ ይጠበቃል። ለሁለቱም ቡድኖች ትጥቅ የሚያቀርበው ናይኪ ነው።
ዋጋው በእነዚህ አገራት በደጋፊዎች ኪስ ላይ ያለው ተጽእኖ ከአንዳንድ ቡድኖች ጋር ሲወዳደር አነስተኛ ነው። በእንግሊዝ ዝቅተኛው የአንድ ሰዓት ሥራ ክፍያ 11.50 ዶላር ገደማ ሲሆን፣ ይህም በወር 1,750 ዶላር አካባቢ ይደርሳል። በፈረንሳይ ዝቅተኛው የወር ደሞዝ ወደ 1,400 ዶላር ገደማ ነው።
በጋና ያለው የመግዛት አቅም እዚህ ግባ የሚባል አይደለም። ለዚህም ነው በዚህ ዓመት መጀመሪያ ላይ በአገሪቱ ያሉ ደጋፊዎች በማኅበራዊ ሚዲያ ላይ ቅሬታቸውን የገለጹት። ምክንያት ሲባሉ በጀርመኑ ፑማ ኩባንያ የተሰራው የ“ጥቋቁር ከዋክብቱ” የዓለም ዋንጫ ትጥቅ ዋጋ 94 ዶላር ገደማ መሆኑ ነው።
“ፎርጂዱ ማልያ እስካሁን ገበያ ላይ አልዋለም?" ሲል አንድ ደጋፊ ጠይቋል።
እንደ የሥራ እና የሠራተኛ ግንኙነት ሚኒስቴር ከሆነ በጋና ያለው ሕጋዊ ዝቅተኛ የደመወዝ ጣሪያ በሰዓት 0.95 ዶላር ነው። በወር 145 ዶላር አካባቢ ማለት ነው።
የወቅቱ የአፍሪካ ሻምፒዮና በሆነችው ሴኔጋል ሐሰተኛ ማልያዎች የዋና ከተማዋ ዳካርን ጎዳናዎች አጥለቅልቀዋል። የአገሪቱ እግር ኳስ አስተዳዳሪ “ብሔራዊ ቡድኑን ለመደገፍ” ሲባል ደጋፊዎች በፑማ የተሠራውን ዋናውን ማሊያ እንዲገዙ ጠይቋል።
እስከ ቅርብ ቀን ድረስ ዋናው ማሊያ በ71 ዶላር እየተሸጠ ነበር። ይህም ከ75 በመቶ በላይ ከሚሆኑ የሴኔጋል ወርሃዊ ዝቅተኛ ደሞዝ ጋር ተመሳሳይ ነው።
“ዋናው ማሊያ በጣም ውድ ነው። ጥሩ ማሊያ ነው፣ እዚህ ያሉ ሰዎች ግን ምንም ገንዘብ የላቸውም” ሲል ሴኔጋላዊው የጎዳና ላይ ነጋዴ ማሊክ ለሬዲዮ ፍራንስ ኢንተርናሽናል ተናግሯል።
“ብዙ ደንበኞች እያገኘሁ ነው” ካለ በኋላ ሴኔጋል ለጥሎ ማለፍ ብትበቃ ደግሞ በከፍተኛ ሁኔታ እሸጣለሁ ሲል ተስፋ ሰንቋል።

የፎቶው ባለመብት, Getty Images
የማሊያ ኢኮኖሚክስ
የእግር ኳስ ቡድኖችን ማሊያ ለማምረት የሚወጣው ወጪ ውድ አይደለም። በባርሴሎና ዮሃን ክራይፍ የስፖርት ማኔጅመንት ኢንስቲትዩት መምህር የሆኑት ሪቻርድ ዴንተን እንደሚገምቱት አንድ ማሊያ ለማምረት የሚያስፈልገው ወጪ ከ10 ዶላር በታች ነው።
“በእርግጠኝነት የገበያ ዋጋውን ተመጣጣኝ እንዳይሆን ከማድርግ ባለፈ ለዚህ ምንም ማረጋገጫ የለም ብሎ ለመከራከርም በር ሊከፍት ይችላል” ሲሉ ዴንተን ይናገራሉ።
“ለአንድ ሰው ምክንያታዊ ያልሆነው ዋጋ ለሌላው ምክንያታዊ ሊሆን ይችላል፤ ምክንያቱም ሌሎች ወጪዎች እና ኢንቨስትመንቶች በመጨረሻው ዋጋ ላይ ተጽዕኖ ያሳድራሉና” ብለዋል።
በእግር ኳስ ቢዝነስ ላይ የተካኑት የምጣኔ ሃብት ባለሙያው ሴሳር ግራፊቲ በበኩላቸው የእግር ኳስ ማሊያ ዋጋ በዋናነት በምርቱ ዋጋ ብቻ የሚገለጽ እንዳልሆነ ያስረዳሉ። ታክስ፣ የሎጂስቲክስ ወጪዎች እና ትራንስፖርትን ጨምሮ ከፍተኛ ተጽዕኖ አላቸው።
ከኮሮናቫይረስ ወረርሽኝ ወዲህ ባለው የምርቶች ግብአት የአቅርቦት ችግር የእቃ ዋጋ ጨምሯል። በዩክሬን ያለው ጦርነትም ዓለም አቀፍ የነዳጅ ወጪ እንዲንር አድርጓል።
ግራፊቲ አክለውም “ለክለቦች እና ለብሔራዊ እግር ኳስ ፌዴሬሽኖች ከፍተኛ ገንዘብ መክፈል ስላለባቸው ትጥቅ አምራች ኩባንያዎች ከማልያ ሽያጭ ብዙ ገንዘብ አያገኙም” ይላሉ።

የፎቶው ባለመብት, Getty Images
“የኃያላኑ” ፍልሚያ
እንደ ናይኪ እና የጀርመን ተቀናቃኙ አዲዳስ ያሉ ግዙፍ አምራቾች ስም ያላቸው ቡድኖች ትጥቆቻቸውን እንዲለብሱ ለማድረግ ብዙ ወጪ ያፈሳሉ።
በዘንድሮው የዓለም ዋንጫ ናይኪ ከ32ቱ ተሳታፊ ቡድኖች ለ13ቱ ትጥቅ አቅራቢ ነው። አዲዳስ የአራት ጊዜ የዓለም ሻምፒዮናዋን ጀርመንን፣ የሁለት ጊዜ ሻምፒዮን የሆነችውን አርጀንቲናንና ለውድድሩ ትልቅ ግምት የተሰጣትን ስፔንን ጨምሮ ለሰባቱ ትጥቅ ያቀርባል።
ሁለቱ አምራቾች በጋራ በመሆን እንደ አርጀንቲና፣ ብራዚል፣ እንግሊዝ፣ ፈረንሳይ፣ ጀርመን፣ ጣሊያን እና ስፔን ላሉ ቡድኖች ትጥቅ ያቀርባሉ። ለብሔራዊ ፌዴሬሽኖቻቸውም በአጠቃላይ በዓመት 275 ሚሊዮን ዶላር እንደሚከፍሉ የስፖርት ቢዝነስ ላይ የሚሰራው ስፖርትስፕሮ ዘግቧል።
“አዲዳስ ወይም ናይኪ ከእግር ኳስ ቡድኖቹ ጋር በሚደረጉ ስምምነቶች ውስጥ ያንን ኢንቨስትመንት ካላስመለሱ የማይደሰቱ ባለአክሲዮኖች አሏቸው” ሲሉ ዴንተን ይገልጻሉ።
“ነገር ግን ማሊያው ውድ ነው ወይስ አይደለም የሚለውን በራሳችን መወሰን አለብን። ለዚህም ነው አንዳንድ ሰዎች ርካሽ ወይን ሲጠጡ ሌሎች ደግሞ ውድ ወይን የሚጠጡት።”
ቢቢሲ አስተያየት እንዲሰጡት አዲዳስ፣ ፑማ እና ናይኪን ጠይቋል። ይህ ዘገባ እስከተጠናቀረበት ጊዜ ድረስ ምላሽ የሰጠው አዲዳስ ብቻ ነው። ኩባንያው በሰጠው ምላሽም ዋጋው ማሊያዎቹን ለመሥራት ጥቅም ላይ ከሚውለው የጨርቅ ጥራት እና ከዘላቂነቱ ጋር የሚያያዝ መሆኑን ገልጿል።
“የእኛ ማሊያዎች በሜዳ ላይ ከሚለበሱት ጋር ተመሳሳይ በሆነ ጨርቅ ያዘጋጃሉ። ደጋፊዎች ለዓመታት በኩራት እንዲለብሷቸውም ነው የተዘጋጁት። ዋጋው ወደ ማሊያነት የሚያመጣውን ዘላቂነት እና የፈጠራ ደረጃን የሚያንፀባርቅ ነው” ብሏል።
ጃኒን ጋርሺያ እና ጓደኞቿ ከዋናው ማሊያ እየወጡ ነው። ሁሉም ሰው በዋጋው መወደድ የራቀ አይመስልም። የናይኪ ተወካዮች እንዳሉት ለዘንድሮው የኳታር ውድድር የተዘጋጀው ማሊያ በ26 ዓመታት ውስጥ በኩባንያው እና በብራዚል እግር ኳስ አስተዳዳሪ አካል (ሲቢኤፍ) መካከል በነበረው ሽርክና በመሸጥ ቀዳሚው ነው።
ጋርሺያ ግን በዚህ ሃሳብ አትስማማም።
“ማን እንደሚገዛቸው ማወቅ እፈልጋለሁ” ትላለች።
“ሁሌም እንደሚለበሱት እንደ ዲዛይነር ቦርሳ ወይም ልብስ አይደሉም።”












