የካርቱም መለያ የሆነው ግዙፉ ሕንጻ በእሳት ተያይዞ ታየ

በእሳት የተያያዘው ህንጻ

የፎቶው ባለመብት, AFP

በሱዳን መዲና ካርቱም በአገሪቱ ጦር እና በፈጥኖ ደራሹ ኃይል መካከል ከፍተኛ ውጊያ ተካሂዶ በካርቱም መሃል ከተማ የሚገኙ ሕንጻዎች በእሳት ተያያዙ።

ከእነዚህ ሕንጻዎች መካከል የካርቱም መለያ ተደርጎ የሚወሰደው የግሬተር ናይል ፔትሮሊየም ኩባንያ ሕንጻ በእሳት ተያይዞ ታይቷል።

የሕንጻው ዲዛይን የሰሩት ታግሪድ አብዲን በኤክስ [የቀድሞው ትዊተር] ከገጻቸው “ይህን መመልከት በጣም ያሳምማል” ብለዋል።

ከናይል ወንዝ አቅራቢያ የሚገኘው ባለ 18 ፎቁ ሕንጻ የካርቱም ቀዳሚው መገለጫ ተደርጎ ይወሰዳል።

ይህ ሕንጻ እንዴት በእሳት ሊያያዝ እንደቻለ እስካሁን ግልጽ አይደለም። በተጨማሪም በእሳቱ ምክንያት በሕንጻውም ሆነ በሰው ላይ ስለደረሰው ጉዳት የተባለ ነገር የለም።

በሁለቱ ጦር ጀነራሎች መካከል የሚካሄደው ውጊያ ተጠናክሮ የቀጠለ ሲሆን በካርቱም እና በሌሎች ከተሞች በጦር ጀቶች የተደገፉ ውጊያ እየተካሄዱ ነው።

ሚያዚያ 2015 ዓ.ም. የሱዳን ግጭት ከተቀሰቀሰ ጀምሮ ከሚሊዮን የማያንሱ ሰዎች አገር ጥለው ለመሰደድ መገደዳቸውን የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት ይገልጻል።

የአገሪቱ ጦር መሪ ጀነራል አብደል ፋታህ አል-ቡርሃን እና የፈጥኖ ደራሽ ኃይሉ መሪ ጀነራል ሞሐመድ ሐምዳን ዳጋሎ መካከል አለመግባባት ተፈጥሮ አገሪቱ ወደለየለት የእርስ በእርስ ጦርነት ከገባች ሰባት ወራት አልፈዋል።

ሱዳን ወደለየለት የእርስ በእርስ ግጭት የገባችው የሠራዊቱ መሪ ጄኔራል አብዱልፈታህ አል ቡርሃን እና የፈጥኖ ደራሹ ኃይል መሪ ጄኔራል መሐመድ ሐምዳን ደጋሎ በመከላከያ ሠራዊት የወደፊት ጥምረት ላይ ባለመግባባታቸው የተጀመረ ነበር።

በጦርነቱ ምክንያት በአገሪቱ መንግሥት አለ ማለት የማይቻልበት ደረጃ ላይ ተደርሷል። የፖሊስ ኃይል ተበትኗል። እስር ቤቶች ተሰብረው ወንጀለኞች ነጻ ሆነዋል እንዲሁም ፍርድ ቤቶች አገልግሎት እየሰጡ አይደለም።

የሱዳንን ግጭት በቅርብ የሚከታተለው ሱዳን ዋር ሞኒተር የተሰኘው ድረ-ገጽ ከትናንት በስቲያ ቅዳሜ የፈጥረኖ ደራሽ ኃይሉ በአገሪቱ ጦር ላይ ድንገተኛ ጥቃቶችን ከከፈተ በኋላ በርካታ ሕንጻዎች በእሳት ተያይዘዋል ብሏል።

የአገሪቱ ጦር ይዞታዎች በሆኑ ሕንጻዎች ላይ በፍጥኖ ደራሽ ኃይሉ የተከፈቱት ጥቃቶች እስከ እሁድ ድረስ መቀጠላቸውን የዓይን እማኞች ለፈረንሳዩ የዜና ወኪል ኤኤፍፒ ተናግረዋል።

ግጭት የካርቱም አካባቢ 3 ኪሎ ሜትሮችን እርቃ የምትገኘው ነዋል ሞሐመድ በከፍተኛው ፍንዳታ ምክንያት የቤተሰቦቿ የበር እና መስኮት መስተውቶች መሰባበራቸውን ተናግራለች።

ነዋል እንደምትለው ከሆነ ቅዳሜ እና እሁድ የነበረው ፍንዳታ ጦርነቱ ከጀመረ ወዲህ ከፍተኛው ነው።

እነዚህ ጥቃቶች በመንግሥታዊ መሠረተ ልማቶች ላይ ከፍተኛ ጉዳት ያስከተሉ ሲሆን በካርቱም እና ዳርፉ የሚገኙ ዋነኛ የመንግሥት ሆስፒታሎች ከአገልግሎት ውጭ መሆናቸውን የጤና ባለስልጣናት አስታውቀዋል።

አብዛኛውን የካርቱም አካባቢዎችን ይዞ የሚገኘው የጀነራል ዳጋሎ የፈጥኖ ደራሽ ኃይሉ ከተማዋን ሙሉ በሙሉ ለመያዝ ሲዋጋ ቆይቷል። የአገሪቱ መከላከያ ደግሞ የፈጥኖ ደራሽ ኃይሉ መቀመጫዎችን በአየር ይደበድባል።

ግጭቱ እስካሁን ድረስ ከ7ሺህ 500 ያላነሱ ሰላማዊ ሰዎችን የገደለ ሲሆን ከአምስት ሚሊዮን በላይ የሚሆኑትን ደግሞ አፈናቅሏል።