በአማራ ክልል በሠልጣኝ ሚሊሻዎች ላይ በተፈጸመ ጥቃት "ቢያንስ 39 ሰዎች" መገደላቸውን እማኞች ተናገሩ

ተፈናቃዮች የሰፈሩበት ጃራ መጠለያ ጣቢያ

የፎቶው ባለመብት, North Wollo Comm./fb

የምስሉ መግለጫ, ጥቃት የተፈጸመበት የሠልጣኞች ካምፕ የሚገኘው ተፈናቃዮች ከሰፈሩበት ጃራ መጠለያ ጣቢያ አጠገብ መሆኑን ዓይን እማኞች ተናግረዋል። ምሥል፦ ጃራ መጠለያ ጣቢያ መጋቢት 2015 ዓ.ም.

በአማራ ክልል ሰሜን ወሎ ዞን ታጣቂዎች በማሠልጠኛ ካምፕ ውስጥ በነበሩ የሚሊሻ አባላት ላይ በፈጸሙት ጥቃት "ቢያንስ 39 ሰዎች" መገደላቸውን የዓይን እማኞች ተናገሩ።

አንድ የሰሜን ወሎ ዞን አስተዳደር ከፍተኛ ኃላፊ በሠልጣኝ የሚሊሻ አባላት ላይ ጥቃት መፈጸሙን ለቢቢሲ አረጋግጠው፤ የደረሰውን የጉዳት መጠን በተመለከተ መረጃ "እየተሰበሰበ" መሆኑን ገልጸዋል።

በሰሜን ወሎ ዞን ሀብሩ ወረዳ ውስጥ በሚገኘው እና የሚሊሻ አባላት የሥልጠና ካምፕ ነው በተባለው ስፍራ ላይ ጥቃት የተፈጸመው ሰኞ መስከረም 5/2018 ዓ.ም. ለማክሰኞ አጥቢያ ከሌሊቱ 10 ሰዓት ገደማ ጀምሮ መሆኑን ሦስት ነዋሪዎች ለቢቢሲ ተናግረዋል።

ጥቃት የተፈጸመበት የሥልጠና ስፍራ፤ ከኦሮሚያ ክልል የተፈናቀሉ የአማራ ተወላጆች ከ2015 ዓ.ም. ጀምሮ ከሰፈሩበት ጃራ መጠለያ ጣቢያ አጠገብ የሚገኝ እንደሆነ ተነግሯል።

በመጠለያ ጣቢያው ነዋሪ የሆኑት ሦስት ግለሰቦች እንደገለጹት የሥልጠና ስፍራው ከዚህ ቀደም የመከላከያ ሠራዊት አባላት ሥልጠና የወሰዱበት ነው።

ከቅርብ ጊዜ ወዲህ ደግሞ ለክልሉ ሚሊሻ አባላት ሥልጠና እየተሰጠበት እንደሆነ አስረድተዋል። አንድ የመጠለያ ጣቢያው ነዋሪ "ማሠልጠኛ ሆኖ ሠልጣኞች እየሰለጠኑበት ያለው እኛ ስንኖርበት ከነበረው ቤት ነው" በማለት ተናግሯል።

የጃራ መጠለያ ጣቢያ ነዋሪዎች አጠገባቸው የሚገኝ ስፍራ ለፀጥታ ኃይሎች ማሠልጠኛነት መዋሉን በስጋት አንስተው እንደነበር ሦስቱም ምንጮች ገልጸዋል።

አንድ ምንጭ፤ "እባካችሁ እኛ ሞት ፈርተን፣ ሕይወታችንን ለማዳን ነው እዚህ የተቀመጥነው። ማሠልጠኛ አይሁን፤ ማሠልጠኛ የሚሆን ከሆነ እኛን ወደ ሌላ ቦታ አድርጎን እያልን ነው የተመሠረተው" ሲሉ በወቅቱ የተነሳውን ስጋት ጠቅሰዋል።

እንደ ነዋሪዎቹ ገለጻ በማሠልጠኛ ካምፑ በነበሩት የሚሊሻ አባላት ላይ ጥቃት የከፈቱት ወደ ስፍራው የመጡ ታጣቂዎች ናቸው። ሁለት ነዋሪዎች የጥይት እና የቦንብ ድምጾች ሲሰሙ እንደነበር የተናገሩ ሲሆን፣ በኋላ ላይ የተኩስ ልውውጥ እየተደረገ ለ30 ደቂቃ ገደማ መቆየቱን አስታውሰዋል።

"30 ደቂቃ ነው የቆየው። ብዙውን ዒላማ ያደረጉት እነሱን ስለሆነ ነው እንጂ ያለነው ሸራ ቤት ላይ ነው፤ በጣም ከባድ ነበር። ተኩሱ ወደ እኛ አለመዞሩ ነው እንጂ እንደምንም ተኝተን ነው ሕይወታችንን ያተረፍነው" ሲሉ አንድ ነዋሪ በወቅቱ የነበረውን ሁኔታ ገልጸዋል።

በካምፑ ውስጥ የነበሩ በተለይ እናቶች እና ህጻናት እጅጉን ተረብሸው እንደነበረም ተናግረዋል።

ተፈናቃዮች የሰፈሩበት ጃራ መጠለያ ጣቢያ

የፎቶው ባለመብት, North Wollo Comm./fb

የምስሉ መግለጫ, ተፈናቃዮች የሰፈሩበት ጃራ መጠለያ ጣቢያ
Skip podcast promotion and continue reading
የቢቢሲ አማርኛ ዩቲዩብ ቻናል

ዜና፣ ትንታኔ እና ታሪኮችን በምሥል እና በድምጽ ለማግኘት

ይህንን በመጫን ሰብስክራይብ ያድርጉ

End of podcast promotion

ቢቢሲ ካነጋገራቸው ነዋሪዎች ሁለቱ፤ ጥቃቱ ካበቃ በኋላ የተፈጠረውን ለመመልከት ንጋት ላይ ወደ ካምፑ መሄዳቸውን አስረድተዋል። አንድ ነዋሪ፤ "ከመጡት ወገን ነው ተብሎ አንድ ሰው ወድቆ አይቻለሁ። ከእነዚህኞቹም ከሚሠለጥኑት አካሎች ወደ 39 የሚሆኑ ወድቀው አይቻለሁ" ሲሉ ዓይን እማኝነታቸውን ሰጥተዋል።

ሌላ ነዋሪ ደግሞ፤ "እስከ 46 [የተገደለ] ሰው በትክክል አይተናል። የቆሰሉት ደግሞ 52 አካባቢ ናቸው" ብለዋል።

ቢቢሲ ያነጋገራቸው ሦስተኛው የጃራ መጠለያ ነዋሪ ደግሞ "የሞቱ ሰዎችን ቁጥር 56" እንዲሁም የቁስለኞችን ብዛት ደግሞ "53" አድርሰውታል።

ምንጮቹ በመጠለያ ጣቢያው ውስጥ በነበሩ ተፈናቃዮች ላይ ጉዳት እንዳልደረሰ ተናግረዋል። አንድ ነዋሪ በበኩላቸው በመጠለያ ጣቢያው የነበረ እና በሚሊሻነት ተመዝግቦ ሥልጠና ላይ የነበረ አንድ ሰው በጥቃቱ ተገድሎ መቀበሩን ገልጸዋል።

ሌላ ነዋሪ፤ "ማን እንደተጎዳ፣ ምን እንደሆነ ለማየት ሄድን። እዚያ ስንሄድ የሞቱትም በየቦታው ወዳድቀው ነበር። የቆሰሉትም በዚያው ልክ ወደ ሐኪም ቤት እንዲሄዱ ተደረገ። የሞቱትን ደግሞ በመጠቅለል ወደየቤተሰቦቻቸው የተላከው" ሲሉ የተመለከቱትን አስረድተዋል።

ጉዳት የደረሰባቸው ሰዎች ለተጨማሪ ሕክምና ወልዲያ እና ሌሎች አጎራባች አካባቢዎች ወደሚገኙ የሕክምና ተቋማት እንደተወሰዱም ምንጮቹ አክለዋል።

ቢቢሲ፤ ጉዳት ደረሰባቸው ሰዎች በወልዲያ አጠቃላይ ስፔሻላይዝድ ሆስፒታል ይገኙ እንደሆነ ለማጣራት ያደረጋቸው ጥረቶች አልተሳኩም።

ቢቢሲ ያነጋገራቸው አንድ የሰሜን ወሎ ዞን ከፍተኛ አመራር ለሚሊሻ አባላት ሥልጠና ሲሰጥበት በነበረ ካምፕ ላይ ጥቃት መፈጸሙን አረጋግጠዋል።

"ጉዳቱ ደርሷል" ያሉት ከፍተኛ ኃላፊው፤ "የጉዳቱን መጠን በተመለከተ ቁጥራቸውን፣ የቆሰለውን፣ የተሰዋውን፣ እንዴት ነው የተፈጠረው? የሚለው" መረጃ "ገና እየተሰበሰበ" መሆኑን አስረድተዋል።

"ከጉዳት አኳያ ያለውን ዝርዝር መረጃ እንዲያጣራ [ቦታው ላይ] የተመደበ ሰው" መኖሩንም አክለዋል።

ቢቢሲ ካነጋገራቸው የጃራ መጠለያ ጣቢያ ነዋሪዎች አንዱ ጥቃት የተፈጸመው በክልሉ በሚንቀሳቀሱት ፋኖ ኃይሎች እንደሆነ መስማታቸውን ገልጸዋል።

"የአማራ ፋኖ ብሔራዊ ኃይል" አንድ አመራር የቡድኑ ታጣቂዎች "ጃራ ካምፕ" እየተባለ በሚጠራ "ወታደራዊ ማሠልጠኛ ካምፕ" ላይ ጥቃት መፈጸማቸውን አስታውቀው ነበር።

የታጣቂ ቡድኑ አባላት ሌሊት ላይ ከፍተውታል ባሉት ጥቃት "በርካታ የአድማ ብተና የሚሊሻ" አባላትን መግደላቸውን ገልጸዋል።