የሰው ሕይወት ያለፈበት የቀይ መስቀል ሠራተኞች እገታን በተመለከተ የተለቀቁት ዶክተር እማኝነት

ሆነልኝ ፋንታሁን
የምስሉ መግለጫ, ከእገታው በኋላ ሕይወቱ ያለፈው የቀይ መስል ማኅበር ባልደረባው ሆነልኝ ፋንታሁን

ባለፈው ሳምንት በአማራ ክልል ሰሜን ጎንደር ዞን ሦስት የኢትዮጵያ ቀይ መስቀል ማኅበር ሠራተኞች "ባልታወቁ ታጣቂዎች" ከታገቱ በኋላ ከመካከላቸው የአንደኛው ሕይወት አልፏል።

በሰብአዊ እርዳታ ድርጅቱ ሠራተኞች ላይ ስለተፈጸመው እገታው ዝርዝር ሁኔታ እና በሂደቱ የሦስት ልጆች አባት ስለሆነው አቶ ሆነልኝ ፋንታሁን ህልፈት አብረው ታግተው የነበሩ የቀይ መስቀል ሠራተኛ እና የሟች ቤተሰብ ለቢቢሲ እማኝነታቸውን ተናግረዋል።

አቶ ሆነልኝ ፋንታሁን፣ ዶ/ር ተፈራ አሰፋ እና አደላደላው ይግዛው በተባሉ የቀይ መስቀል የሰሜን ጎንደር ማስተባበሪያ ጽህፈት ቤት ሠራተኞች ላይ ሲሆን፤ ሠራተኞቹ ነሐሴ 7/2017 ዓ.ም. ጃን አሞራ ለተባለ ወረዳ አዲስ አምቡላን አስረክበው ሲመለሱ እገታው መፈጸሙ ተነግሯል።

ከእገታው ከተለቀቁት ሁለት ሠራተኞች አንዱ የሆኑት ዶ/ር ተፈራ አሰፋ በማግስቱ ሐሙስ ነሐሴ 8/2017 ዓ.ም. ወደ ደባርቅ እየተመሰሉ እያለ ጨነቅ (አምባ ራስ) በተባለ የሰሜን ተራሮች ብሔራዊ ፓርክ አካባቢ ከጠዋቱ 02፡30 ላይ መሣሪያ በታጠቁ ሰዎች መታገታቸውን ለቢቢሲ ተናግረዋል።

በመልስ ጉዞ ላይ የነበሩት የማኅበሩ ባልደረቦች ይጓዙበት የነበረው መኪና በአራት ታጣቂዎች መንገድ ላይ እንዲቆም ከተደረገ በኋላ ድብደባ ተፈጽሞባቸው እንደታገቱ እማኝነታቸውን ሰጥተዋል።

"መጀመሪያ መሣሪያ ያልያዘ [ሰው] ከፊት መጣ፤ ሹፌሩን 'አቁም' አለው። መኪናው እየቆመ ሳለ ወዲያውኑ መሣሪያ የታጠቁ መኪናው ላይ ደገኑ። ለማነጋገር [መስኮቱን] ዝቅ ስናደርግ ውረዱ አሉን፤ ወረድን። ደበደቡን። የለበስነውን የቀይ መስቀል ሰደርያ አውልቁ አሉን፤ አወለቅን" ሲሉ የእገታው ክስተት እንዴት እንደጀመረ ገልፀዋል።

በአካባቢው ተመሳሳይ ጥቃቶች የተለመዱ በመሆናቸው ጉዞ ከመጀመራቸው በፊት ስለ መንገዱ ሁኔታ መረጃ ጠይቀው "ሰላም ነው" የሚል ምላሽ ካገኙ በኋላ መንገድ መጀመራቸውን የሚናገሩት ዶ/ር ተፈራ፤ እገታውን "ያልጠነበቅነው ነው" ብለዋል።

እገታውን የፈጸሙትን ታጣቂዎች ማንነት በተለመከተ "ሽፍታዎች ሊሆኑ ይችላሉ" ያሉ ሲሆን፤ ቢቢሲ ያነጋገራቸው ሌሎች ግለሰቦችም አጋቾቱን በአካባቢው ተመሳሳይ ድርጊት የሚፈጽሙ "ወንበዴዎች" ሲሉ ጠርተዋቸዋል።

Skip podcast promotion and continue reading
የቢቢሲ አማርኛ ዩቲዩብ ቻናል

ዜና፣ ትንታኔ እና ታሪኮችን በምሥል እና በድምጽ ለማግኘት

ይህንን በመጫን ሰብስክራይብ ያድርጉ

End of podcast promotion

አጋቾቹ የቀይ መስቀል ሠራተኞቹን እና ሻናጣዎቻቸውን ይዘው በእግር ለሁለት ሰዓታት ወደ ሌላ ቦታ እንደወሰዷቸው ዶ/ር ተፈራ ተናግረዋል።

"በጣም ውርጭ ያለበት፤ በረዶ ያለበት አካባቢ ነው" ሲሉ የአካባቢውን ሁኔታ ያስታወሱት ሠራተኛው፤ ታጣቂዎቹ ዋሻ ውስጥ እንዲያርፉ ካደረጉ በኋላ የማስለቀቂያ ገንዘብ እንዲከፈላቸው መጠየቃቸውን ገልፀዋል።

መጀመሪያ ላይ ለእያንዳንዳቸው አንድ ሚሊዮን ብር የማስለቀቂያ ገንዘብ ተጠይቆ እንደነበር የተናገሩት ዶ/ር ተፈራ አሰፋ፤ ለቤተሰቦቻቸውም ይህን ደውለው አሳውቀዋል።

ይህ የስልክ ጥሪ ሐሙስ ከቀኑ 10፡00 አካባቢ የደረሳቸው የአቶ ሆነልኝ ፋንታሁን ታላቅ ወንድም አቶ ዋሴ ፋንታሁን ድብልቅልቅ ባለ ስሜት ሁኔታውን እንደሰሙ ለቢቢሲ ተናግረዋል።

በሹፌሩ በኩል ስልክ ሲደወልላቸው "'ወንድሜ እንዳይሞት የሚገባውን ነገር አደርጋለሁ፤ የሚከፈልም ነገር ካለ ንገሩኝ፤ እንዳይሞትብኝ። ነገር ግን 'የቀይ መስቀል ሠራተኛ ላይ እንዴት ይህ ይፈጸማል?' አልኳቸው" ሲሉ በተደበላለቀ ስሜት ምላሽ እና ጥያቄ አቀረቡ።

ታጋቾቹ የቀረበላቸውን ጥያቄ ለቤተሰቦቻቸው ካሳወቁ በኋላ ለአማራ ክልል ቀይ መስቀል ማኅበር ቅርንጫፍ ጽ/ቤት ደውለው ስለሁኔታው እንዲያወቁ ያደረጉ ሲሆን፤ ይህንም የጽ/ቤቱ ኃላፊ አቶ ሻምበል ዋለ ለቢቢሲ አረጋግጠዋል።

የእገታቸውን ዜና ለቤተቦቻቸው እና ለቀይ መስቀል ካሳወቁ በኋላ ምሽት ላይ አቶ ሆነልኝ ሕመም እንደጀመራቸው ዶ/ር ተፈራ ተናግረዋል።

"ወደ ላይ ይለዋል፤ እንደገና ብርድ፤ ቅዝቃዜ አለው፤ ረሃብ ስለነበር ማታ ከምሽቱ 05፡00 ሰዓት አካባቢ ሾክ [መንቀጥቀጥ] ውስጥ ገባ። ራሱን ሳተ፤ ራሱን ማወቅ አልቻለም። በሚቀጥለው ቀንም እንዲሁ ታምሞ ዋለ" በማለት ባልደረባቸው ስለገጠመው ሕመም ገልፀዋል።

የማስለቀቂያ ገንዘብ ያለመክፈል ፖሊሲ ያለው ቀይ መስቀል ሁኔታውን ለአዲስ አበባው ዋና ጽ/ቤት እና ለዓለም አቀፉ የቀይ መስቀል ማኅበር በማሳወቅ ሠራተኞቹን ለማስለቀቅ በሽማግሌዎች በኩል ጥረት መደረጉን አቶ ሻምበል ተናግረዋል።

የሽማግሌዎችን ጫና ተከትሎ አርብ ነሐሴ 9/2017 ዓ.ም. ከሰዓት 10፡00 አካባቢ ታጣቂዎቹ ታጋቾቹን መለቀቃቸውን ዶ/ር ተፈራ ገልጸዋል።

ይሁን እንጂ የአቶ ሆነልኝ ሕመም መቀጠል ሌላ ፈተና እንደሆነባቸው ጠቁመዋል።

የቀይ መስቀል ሠራተኞች በአካባቢው

የፎቶው ባለመብት, Debark city communication

የምስሉ መግለጫ, የቀይ መስቀል ሠራተኞች በአካባቢው

ታጋቾቹ በታጣቂዎቹ ተይዘው በሰዓታት የእግር ጉዞ በመወሰዳቸው ከነበሩበት ለመመለስ አስቸጋሪ ሆኖባቸው ነበር። በተለይም የታመመው ባልደረባቸውን ይዘው ለመጓዝ ችግር ስለገጠማቸው አመራጭ መፈለግ ግድ ሆኖባቸው ነበር።

"መንገዱ ሩቅ ስለነበር ሹፌሩ [አቶ አደላደላው ይግዛው] ወደ መንደር ሄዶ [የሚረዳን] ሰው አመጣ። በቃሬዛ አድርገን ከምሽቱ 02፡00 ሲሆን ሕክምና ቦታ አደረስነው። ጉልኮስ ተደረገለት፤ [ግን] ለውጥ አልነበረውም። ሌሊት 05፡00 እንደገና ደባርቅ ሆስፒታል ይዘነው እየሄድን ሳለ ሕይወቱ አልፈ" በማለት የሦስት ዓመት ባልደረባቸው ሕይወት እንዴት እንዳለፈ ገልፀዋል።

ዶ/ር ተፈራ አሰፋ ለባልደረባቸው አቶ ሆነልኝ ህልፈት ምክንያቱ የደረሰበት ድብደባ፣ ድንጋጤ፣ የአካባቢው ቅዝቃዜ፣ የአደሩበት ሁኔታ እና ረሃብ ሊሆን እንደሚችል ገምተዋል።

የኢትዮጵያ ቀይ መስቀል ማኅበር ሰኞ ዕለት ባወጣው መግለጫ "ድብደባ እና ኢ-ሰብዓዊ አያያዝ" ለአቶ ሆነልኝ ሞት ምክንያት ነው ብሏል።

በማኅበሩ የአደጋ ስጋት ቅነሳ አስተባባሪ የነበሩት አቶ ሆነልኝ፤ በቀይ መስቀል ለሦስት ዓመታት ያገለገለ ሲሆን፣ ባለትዳር እና የአራት ወር፣ የአራት ዓመት እና የስድስት ዓመት ዕድሜ ያላቸው የሦስት ልጆች አባት ነበረ።

"[ሆነልኝ] እንደ የመጀመሪያ ልጄ ነበር" የሚሉት የሟቹ ታላቅ ወንድም አቶ ዋሴ ፈንታሁን፤ ወንድማቸውን እራሳቸው አስተምረው ለወግ ማብቃታቸውን ለቢቢሲ ተናግረዋል።

የወንድማቸውን ህልፈት ከእገታ ከመለቀቁ ጋር ተደበላልቆ ነበር የሰሙት "[አርብ ነሐሴ 9] ከሰዓት በኋላ 10፡00 ሰዓት ላይ ተለቆልሃል አሉኝ። በዚያው ሌሊት 09፡00 ሰዓት ላይ በዚያው ስልክ ሞተልህ አሉኝ" በማለት በሐዘን በተሰበረ ድምጽ ተናግረዋል።

"ምን እንደሆነ ሳላውቀው፤ ወንድሜን ሳላስታምመው፣ አፈር ሳላለብሰው አጣሁት" የሚሉት አቶ ዋሴ፤ መንገዱ ሰላም ባለመሆኑ ወንድማቸውን መቅበር እንኳ እንዳልቻሉ ተናግረዋል።

"ወላጅ አባቱ ሽማግሌ ነው፤ እስካሁን [ሞቱን] አልሰማም" ያሉት የሟች ወንድም፤ ቀብሩ ባለቤቱ እና ልጆቹ በሚኖሩበት ደቡብ ጎንደር አዲስ ዘመን ከተማ ውስጥ ተፈጽሟል።

የአማራ ክልል የትጥቅ ግጭት ከተቀሰቀሰ በኋላ በርካታ የረድኤት ድርጅት ሠራተኞች ግድያን ጨምሮ የተለያዩ ጥቃቶች እንደተፈፀመባቸው የተለያዩ ድርጅቶች አስታውቀዋል።

በጥቃቶች ምክንያት አንዳንድ ድርጅቶችም ክልሉን ለቀው መውጣታቸውን የገለጹ ሲሆን፤ ይህም የሰብዓዊ እርዳታ እና የመሠረታዊ ፍላጎቶች አቅርቦት እንዲስተጓጎል ማድረጉ ይነገራል።

ዶ/ር ተፈራ እሳቸው እና ባልደረቦቻቸው ላይ የተፈጸመው ጥቃት እና በአካባቢው ያለው የፀጥታ ሁኔታ ሕክምና እና እርዳታ ለሚያስፈልጋቸው የማኅበረሰብ ክፍሎች ለመድረስ "ከባድ" እንቅፋት እንደሆነ ያምናሉ።

የተባበሩት መንግሥታት የሰብአዊ ድጋፍ ማስተባበሪያ (ኦቻ) እገታውን እና የተፈጸመውን ድርጊት አውግዞ ለሰብአዊ እርዳታ ሠራተኞች ጥበቃ እንዲደረግ ጥሪ አቅርቧል።

ማክሰኞ ነሐሴ 13/2017 ዓ.ም. ስለ ጥቃቱ መግለጫ ያወጣው አማራ ፋኖ ሕዝባዊ ድርጅት የተባለው ቡድን በኢትዮጵያ ቀይ መስቀል ማኅበር ባልደረቦች ላይ የተፈጸመውን እገታ እና ድብደባ እንደሚያወግዝ አስታውቋል።

አክሎም ከጥቂት ወራት በፊት የአንድ የረድኤት ሠራተኛ ግድያን ጨምሮ አሁን በቀይ መስቀል ሠራተኞች ላይ የተፈጸመውን ጥቃት ገለልተኛ አካል እንዲመረምርም ጥሪ አቅርቧል።