የተባበሩት መንግሥታት በሰሜን ጎንደር የተፈጸመውን የቀይ መስቀል ባልደረባ "አሰቃቂ ግድያ" አወገዘ

አቶ ሆነልኝ ፋንታሁን

የፎቶው ባለመብት, Ethiopian Red Cross Society

የምስሉ መግለጫ, አቶ ሆነልኝ ፋንታሁን

የተባበሩት መንግሥታት የሰብዓዊ ጉዳዮች ማስተባበሪያ ቢሮ በአማራ ክልል ሰሜን ጎንደር ዞን ባልታወቀ ቡድን ታግቶ በተፈጸመበት ድብደባ ሕይወቱ ያለፈውን የቀይ መስቀል ባልደረባ ሆነልኝ ፋንታሁንን "አሰቃቂ ህልፈት" አወገዘ።

"የረድዔት ሠራተኞች የጥቃት ዒላማ ሊሆኑ አይገባም" ሲሉ በኢትዮጵያ የተባበሩት መንግሥታት የሰብዓዊ ጉዳዮች ማስተባበሪያ (ኦቻ) ጊዜያዊ አስተዳዳሪ ዶክተር አቡባካር ካምፖ መናገራቸውን ቢሮው ገልጿል።

የቀይ መስቀል ባልደረባ የነበረው አቶ ሆነልኝ ፋንታሁን ከደባርቅ ከተማ 15 ኪሎሜትር ርቀት ላይ በምትገኘው ጨነቅ አካባቢ በሰብዓዊ አገልግሎት ላይ ተሰማርቶ በነበረበት ወቅት "ባልታወቀ ቡድን ነሐሴ 8/2017 ዓ.ም. እገታ እንደተፈጸመበት" የኢትዮጵያ ቀይ መስቀል ማኅበር ነሐሴ 12/ 2017 ዓ.ም ባወጣው መግለጫ አስታውቋል።

በእገታው ወቅት የማኅበሩ ባልደረባ በተፈጸመበት "ድብደባ እና ኢ-ሰብዓዊ አያያዝ" በማግስቱ ነሐሴ 9/2017 ዓ.ም. ሕይወቱ ማለፉን ተቋሙ አክሏል።

አቶ ሆነልኝ በታገተበት ወቅት አብረውት በሥራ ላይ የነበሩት ዶ/ር ተፈራ አሰፋ እና አቶ አደላዳላው ይግዛው ከዚህ ጥቃት መትረፋቸውን ማኅበሩ አስተውቋል።

የኢትዮጵያ ቀይ መስቀል ማህበር ግለሰቦቹ "ከዚህ አሳዛኝ ክስተት በመትረፋቸው ብንፅናናም፣ አቶ ሆነልኝን ማጣታችን ግን ሕመሙ ለእኛ ከፍተኛ ነው" ሲል ሐዘኑን ገልጿል።

የመንግሥታቱ ድርጅት የሰብአዊ ጉዳዮች ማስተባበሪያ ቢሮ በበኩሉ "በአሳዛኝ እና በአሰቃቂ ሁኔታ" ሕይወቱ ያለፈው የቀይ መስቀል ባልደረባ ሞት እንዳሳዘነው ገልጾ "የረድኤት ሠራተኞች ደኅንነት ሕጋዊ እና ሞራላዊ ግዴታ ነው" ሲለ አሳስቧል።

ቢሮው አክሎም የረድዔት ሠራተኞች ጥበቃ እንዲደረግላቸው ጥሪ አቅርቦ ጥቃት በሚፈጽሙት ላይ "ተጠያቂነት" እንዲሰፍንም ጠይቋል።

Skip podcast promotion and continue reading
የቢቢሲ አማርኛ ዩቲዩብ ቻናል

ዜና፣ ትንታኔ እና ታሪኮችን በምሥል እና በድምጽ ለማግኘት

ይህንን በመጫን ሰብስክራይብ ያድርጉ

End of podcast promotion

የሦስት ልጆች አባት የሆነው የኢትዮጵያ ቀይ መስቀል ባልደረባ "ሌሎችን ሲያገለግል" ሕይወቱን አጥቷል ሲል የዩናይትድ ኪንግደም ኤምባሲ በበኩሉ የግለሰቡን ሞት አስመልክቶ ባወጣው የሐዘን መግለጫ አውጥቷል።

ኤምባሲው አክሎም አቶ ሆነልኝ ፋንታሁን "ለከፈለው መስዋዕትነት አክብሮታችንን እየገለጽን፤ ለረድዔት ሠራተኞች የበለጠ ጥበቃ እንዲደረግ እንጠይቃለን" ብሏል።

የኢትዮጵያ ቀይ መስቀል ማኅበር አክሎም "የአቶ ሆነልኝ ቁርጠኝነት እና በመስዋዕትነት የታጀበ አገልግሎት የሰብአዊነት ምልክት ሆኖ ለዘላለም ሲታወስ ይኖራል።ለሰብዓዊነት እንኖራለን" ሲል አክብሮቱን ገልጿል።

ግለሰቡ በማን ታግቶ እንደነበር ዝርዝር መረጃ ያልሰጠው ቀይ መስቀል "ሁሉም ወገኖች የዓለም አቀፍ የሰብአዊነት ሕግጋትን እና የጄኔቫ ስምምነቶችን እንዲያከብሩ እንዲሁም ሠራተኞቻችን እና በጎ ፈቃደኞቻችን የሌሎችን ሕይወት ለመታደግ የራሳቸውን ሕይወት በየቀኑ አደጋ ላይ በመጣል የሚሰጡት የሰብአዊ ድጋፍ ያለ ስጋት በገለልተኝነት እንዲያደርሱ ጥበቃ እና ድጋፍ እንዲደረግላቸው እንጠይቃለን" ብሏል።

የዓለም አቀፉ ቀይ መስቀል እና ቀይ ጨረቃ ማኅበር ከጥር ወር ጀምሮ ባለው ጊዜ ውስጥ በኢትዮጵያ፣ በሱዳን፣ በደቡብ ሱዳን፣ በጋዛ እና በኢራን በሕይወት አድን ተግባራት ላይ ተሰማርተው የነበሩ 18 ሠራተኞቹ እና በጎ ፈቃደኞቹ መገደላቸውን ነሐሴ 13/2017 ዓ.ም. ባወጣው መግለጫ አስታውቋል።

በረድዔት ሠራተኞች ላይ የሚደርሰው "አጸያፊ ጥቃት" መቆም እንዳለበት ያሳሰበው ተቋሙ "ሌሎች በርካቶች ከሥራ ገበታቸው ውጪ በመኖሪያ ቤታቸው፣ ከቤተሰቦቻቸው ጋር ወይም የዕለት ተዕለት ኑሯቸው ላይ እያሉ ተገድለዋል። ሌሎች ተጨማሪ ደግሞ ቆስለዋል፣ ለዘፈቀደ እስር ተደርገዋል፣ ወይም ታግተዋል" ብሏል።

የዓለም አቀፉ ቀይ መስቀል በዚህ መግለጫው "ሁሉም መንግሥታት፣ ተፋላሚ ወገኖች እና የዓለም መሪዎች የሰዎችን ሕይወት ለመታደግ ሁሉንም መስዋዕትነት እየከፈሉ ያሉ የረድዔት ሠራተኞችን ለመጠበቅ አፋጣኝ እና ተጨባጭ እርምጃዎችን እንዲወስዱ እንጠይቃለን። የረድዔት ሠራተኞች ሲጠበቁ የእኛ የጋራ ሰብዓዊነትም ይጠበቃል" ብሏል።

የረድዔት ሠራተኞች ላይ ሆን ብለው ያነጣጠሩ ጥቃቶች መጨመራቸውን በርካታ ተቋማት እያሳሰቡ ይገኛሉ።

የተባበሩት መንገግሥታት ድርጅት የዓለም ምግብ ፕሮግራም ባለፈው ዓመት ሰኔ ወር ላይ ባወጣው ሪፖርት በአምስት ወራት ውስጥ 50 የረድዔት ሠራተኞች በኢትዮጵያ በሰብዓዊ ተግባራት ላይ ተሰማርተው እያሉ ሕይወታቸውን እንዳጡ አስታውቆ ነበር።

የአውሮፓውያኑ 2024 ከገባ ጀምሮ 50 የረድዔት ሠራተኞች ሕይወታቸው እንዳለፈ ያስታወቀው ተቋሙ፣ በምን ሁኔታ እና የት ቦታ እንደሞቱ ዝርዝር መረጃ አልሰጠም።

ከፀጥታ ችግር በተጨማሪ የነዳጅ እጥረት፣ የመንገድ መዘጋት እና ደካማ መሠረተ ልማት በእርዳታ አቅርቦት ሰንሰለት ላይ ችግር መደቀኑንም የዓለም ምግብ ፕሮግራም አመልክቷል።

ከአራት ዓመታት በፊት በትግራይ ጦርነት ወቅት በክልሉ የሰብዓዊ ተልዕኮ ላይ የነበሩ ድንበር የለሽ የሐኪሞች ቡድን (ኤምኤስኤፍ) ሦስት ሠራተኞች "ሆን ተብሎ እና በግልጽ ተለይተው" በኢትዮጵያ መከላከያ ሠራዊት "መረሸናቸውን" ተቋሙ በቅርቡ ማስታወቁ ይታወሳል።

በኢትዮጵያ ከ2019 ጀምሮ እስከ 2023 ባሉት ዓመታት 36 የረድዔት ሠራተኞች መገደላቸውን የተባበሩት መንግሥታት የሰብዓዊ ጉዳዮች ማስተባበሪያ ቢሮ ( ዩኤን ኦቻ) ከሁለት ዓመት በፊት ያወጣው ሪፖርት ያሳያል።

በተለያዩ የኢትዮጵያ አካባቢዎች ባሉ ጦርነቶች እና ግጭቶች ምክንያት ሰብዓዊ ተደራሽነት ፈታኝ መሆኑንም ማስተባበሪያ ቢሮው ባለፈው ዓመት መጋቢት ወር ላይ ባወጣው ሪፖርት ላይ ጠቅሷል።

ዩኤን ኦቻ በአማራ ክልል በቀጠለው ግጭት ምክንያት ግብረ ሰናይ ድርጅቶች ችግር እየገጠማቸው እንደሆነ እና በርካታ ጉዳቶች ማጋጠማቸውን ገልጿል።

የረድዔት ሠራተኞች በታጠቁ አካላት ቀጥታ ዒላማ ባይሆኑም "ባለው የፀጥታ ሁኔታ ተለዋዋጭነት፣ የአካባቢ ሚሊሻዎችን ጨምሮ መሳሪያ ያነገቱ ዜጎች በአጠቃላይ የታጠቁ አካላት መበራከት ለረድዔት ሠራተኞች እና ለሰብዓዊ እርዳታ ሥራዎች ከፍተኛ ስጋትን ደቅነዋል" ብሎ ነበር።

የተባበሩት መንግሥታት የሰብዓዊ ጉዳዮች ማስተባበሪያ ቢሮ በረድዔት ሠራተኞች ላይ ዕገታ፣ ዝርፊያ እና ጥቃትን ጨምሮ 93 ክስተቶችን በአውሮፓውያኑ 2023 መዝግቤያለሁ ብሏል።

በጥር እና የካቲት ወራትም አምስት የረድዔት ሠራተኞች በትግራይ፣ በአማራ እና በኦሮሚያ ክልሎች ውስጥ መገደላቸውንም አካቷል።

በትግራይ የሰሜናዊ ክፍል ሪፖርቱ በስም ያልጠቀሳቸው የውጭ ኃይሎች መኖራቸው ችግሮችን እንዳባባሱም ጠቅሷል።