የፋኖ ኃይሎች እና የኦሮሞ ነፃነት ሠራዊት 'የተኩስ አቁም' ንግግር ማድረጋቸውን አስተባበሉ

የፎቶው ባለመብት, AFP
በአማራ እና በኦሮሚያ ክልሎች የሚንቀሳቀሱ ታጣቂ ቡድኖች መደበኛ ያልሆነ የግጭት የማቆም ንግግር አድርገዋል መባሉን አስተባበሉ።
ከሰሞኑን በአገሪቱ ሁለት ታላላቅ ክልሎች ውስጥ የሚንቀሳቀሱት ታጣቂ ቡድኖች እርስ በእርሳቸው የሚያደርጉትን "ግጭት" ለማቆም መደበኛ ያልሆነ ስምምነት ላይ መድረሳቸውን የሚያመለክት ዘገባ ወጥቶ ነበር።
በኦሮሚያ እና በአማራ ክልል ውስጥ የሚንቀሳቀሱት ታጣቂዎች የጋራ ዓላማ እየፈለጉ ነው በሚል በተሠራጨው ዘገባ፣ ቡድኖቹን "ታሪካዊ ጠላቶች" በማለት ሁለቱ አማፂ ኃይሎች በአሜሪካ መደበኛ ያልሆነ ንግግር ማድረጋቸውን ጠቁሟል።
በመንግሥት በሽብር ቡድንነት ፈርጆ 'ሸኔ' ተብሎ የሚጠራው የኦሮሞ ነፃነት ሠራዊት (ኦነሠ) ከፋኖ ኃይሎች ጋር ከዚህ ቀደም ምንም ንግግር አድርጎ እንደማያውቅ ለቢቢሲ አፋን ኦሮሞ ተናግሯል።
የጦሩ ዋና አዛዥ አማካሪ የሆኑት አቶ ጅሬኛ ጉደታ "ድንበር ላይ ተገናኝተዋል የሚባለው ውሸት ነው። ለነፃነት የሚታገል አንድ ላይ መጥቶ ቢወያይም ክፋት የለውም። ይሁን እንጂ እስካሁን በዚህ መልክ ተገናኝቶ የተወያየ አካል የለም" ሲሉ ዘገባውን አስተባብለዋል።
ቢቢሲ ያነጋገራቸው ሁለት የፋኖ ቡድኖችም ተደረገ የተባለውን ንግግር አስተባብለው፤ ሁለቱ አማፂዎች ግንኙነት እንደሌላቸው ተናግረዋል።
የአማራ ፋኖ ሕዝባዊ ድርጅት (አፋሕድ) የተባለው የፋኖ አደረጃጀት የኦሮሞ ነጻነት ሠራዊት እየተባለ የሚጠራውም ሆነ የኦሮሞ ነፃነት ግንባር (ኦነግ) ከባለው ፓርቲ ጋር "ምንም ዓይነት ግንኙነት" አድርጎ እንደማያውቅ ተናግሯል።
የአፋሕድ የፖለቲካ ጉዳዮች መምሪያ ኃላፊ አቶ ጌታ አስራደ "በቀጥታም ሆነ በተዘዋዋሪ መንገድ ግንኙነት ወይም ድርድር ወይም ስምምነት አልተደረገም" ሲሉ ለቢቢሲ ምላሽ ሰጥተዋል።
ሌላኛው የፋኖ አደረጃጀት የሆነው የአማራ ፋኖ ብሔራዊ ኃይል (አፋብኃ) በኦሮሚያ ክልል ከሚንቀሳቀሰው ታጣቂ ቡድን ጋር "ግጭትም ሆነ ስምምነት" የለንም ብሏል።
የድርጅቱ የሕዝብ ግንኙነት ኃላፊ አቶ ዮሐንስ ንጉሡ "እስካሁን ያደረግነው ግልፅ ንግግር፤ ይፋዊ የሆነ ንግግር የለም። ስምምነት የተደረሰበት ጉዳይ የለም" ሲሉ ተደረገ ስለተባለው ስምምነት ማስተባበያ ሰጥተዋል።
ሁለቱም አማፂ ቡድኖች በአንዳንድ አካባቢዎች ላይ እንደሚንቀሳቀሱ ጭምጭምታዎች ያሉ ሲሆን፤ በተለይም የግዛት ውዝግብ ባለባቸው አካባቢዎች ግጭቶች እንዳሉ ይነገራል።
ቢቢሲ ሁለቱ ታጣዊዎች የተኩስ ማቆም የሚያስፈልገው ውጊያ ያደርጉ እንደሆነ የጠየቃቸው አቶ ዮሐንስ "በመጀመሪያ እኛ የአማራ ፋኖ ብሔራዊ ኃይል [ከኦነሠ ጋር] ቀጥተኛ ግጭት ውስጥ አልገባንም። ስለዚህ የተኩስ አቁም ስምምነት መድረስ የሚችለው የተጋጨ አካል ነው፤ ቀጥታ ውጊያ ውስጥ የገባ እንጂ በእኛ በኩል ግጭት ውስጥ ስላልገባን ይህንን ማድረግ አይጠበቅብንም" ሲሉ ሁለቱም ታጣቂዎች በራሳቸው ቀጣና ውስጥ እንደሚንቀሳቀሱ ገልፀዋል።
የኦነሠ ዋና አዛዥ አማካሪ የሆኑት አቶ ጅሬኛ በፋኖ ስም በኦሮሚያ ክልል የሚንቀሳቀሱ ታጣቂዎችን "እንደ ጠላት" እንደሚያዩ ጠቁመው፤ "...በአገሩ ውስጥ [በአማራ ክልል] ጥያቄ አለኝ ብሎ የሚንቀሳቀስን [ኃይል] ግን በሌላ መልኩ እናየዋለን" ሲሉ በጋራ የመሥራት ሀሳብ ክፍት ሊሆን እንደሚችል ጠቆም አድርገዋል።
የአማራ ፋኖ ብሔራዊ ኃይል (አፋብኃ) የሕዝብ ግንኙነት ኃላፊ አቶ ዮሐንስ በበኩላቸው "በሚያስማሙ ጉዳዮች" ላይ ሁለቱ አማፂ ኃይሎች ወደፊት ሊነጋገሩ የሚችሉባቸው ዕድሎች ሊኖሩ እንደሚችሉ አመልክተዋል።
"የነፃነት ኃይሎች በጋራ መነጋገር ስለሚጠበቅባቸው አገሪቱን ከብተና ለመታደግ ሲባል ቀጣይ ውይይት ግን ሊኖር ይችላል።. . .በቀጣይ ያሉ ሁኔታዎችን በመገምገም በእነርሱ በኩል የፖሊሲ፤ የአቅጣጫ ማሻሻያዎች የሚኖሩ ከሆነ፤ አገር በማዳን ጉዳይ ግን በቀጣይ ውይይት ሊኖር ይችላል" ብለዋል።
በትግራይ የተካሄደው ጦርነት ካበቃ በኋላ መንግሥት በአማራ ክልል ያሉ ታጣቂ ቡድኖችን ትጥቅ ለማስፈታት መወሰኑን ተከትሎ በተለያዩ የክልሉ ክፍሎች ያሉ የፋኖ ታጣቂዎች የመንግሥት ኃሎች ጋር ግጭት ውስጥ ከገቡ ሁለት ዓመታት አልፏቸዋል።
በተለያዩ የኦሮሚያ ክልል የሚንቀሳቀሰው የኦሮሞ ነጻነት ሠራዊት ከኦሮሞ ነጻነት ግንባር ተለይቶ ከመንግሥት ኃይሎች ጋር መዋጋት ከጀመረ ዓመታት ተቆጥረዋል።
ቡድኑ በሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት በሽብርተኝነት የተፈረጀ ሲሆን፣ ከመንግሥት ጋር ያልተሳኩ ሁለት ድርድሮችን ማድረጉ ይታወሳል።
መንግሥት በየትኛውም የአገሪቱ ክፍሎች ውስጥ የሚንቀሳቀሱ ታጣቂ ኃይሎች የኃይል እንቅስቃሴያቸውን ካቆሙ ለመቀበል ዝግጁ መሆኑን ሲገልጽ ቆይቷል።
ባለፉት ወራትም ከሁለቱም ቡድኖች ወደ መንግሥት በሰላም የገቡ ታጣቂዎች እንዳሉ የመንግሥት መገናኛ ብዙኃን ሲዘግቡ ቆይተዋል።















