ኬንያ እና ኖርዌይ የመንግሥት እና የኦሮሞ ነጻነት ሠራዊት ንግግርን እያሸማገሉ እንደሆነ ተጠቆመ

ዛንዚባር

ለሦስተኛ ቀን በቀጠለው የኢትዮጵያ መንግሥት እና የኦሮሞ ነጻነት ሠራዊት ልዩነታቸውን በሰላም ለመቋጨት በሚያደርጉት ውይይት ኬንያ እና ኖርዌይ በዋነኛ የአሸማጋይነት ሚና እየተጫወቱ እንደሆነ ተጠቆመ።

ቢቢሲ ለድርድሩ ቅርበት ካላቸው ምንጮች እንደሰማው የፌደራሉ መንግሥት እና የኦሮሞ ነጻነት ሠራዊት በታንዛኒያ ራስ ገዝ አስተዳደር በሆነችው ዛንዚባር እያደረጉት ባለው ውይይት የኬንያ እና የኖርዌይ አሸማጋዮች በስፍራው ተገኝተዋል።

ከዚህ ቀደም ሁለቱን ወገኖች በማቀራረብ እና ውይይቱም እንዲጀመር የስዊድን፣ የኖርዌይ፣ የኬንያ፣ የአውሮፓ ኅብረት እና የአሜሪካ ዲፕሎማቶች ድጋፍ እየሰጡ እንደነበር ለድርድሩ ቅርበት ያላቸው ምንጮች ተናግረው ነበር።

በዚህ ውይይት ላይ አጀንዳዎችን የመቅረጽ ውይይቶች እየተካሄዱ እንደሆነም ለጉዳዩ ቅርበት ያላቸው ምንጮች ተናግረዋል።

የሁለቱን ወገኖች ስድስት፣ ስድስት ልዑካን እና አሸማጋዮችን የያዘው ይህ ውይይት ማክሰኞ ሚያዝያ 17/ 2015 ዓ.ም. ተጀምሮ በሳምንቱ መጨረሻ ይጠናቀቃል የሚል ዕቅድ ተይዞ እንደነበር የተሰማ ቢሆንም፣ ሊራዘም እንደሚችል በስፍራው የምትገኘው የቢቢሲ ዘጋቢ ከምንጮቹ ሰምታለች።

ለዚህም በዋነኝነት በኦሮሚያ ክልል ያሉ ጥያቄዎች በጣም ውስብስብ እና በቀላሉ እልባት ሊደረስባቸው ስለማይችሉም እንደሆነም ነው ምንጮቹ የተናገሩት።

የኦሮሞ ነጻነት ሠራዊት ዋና አዛዥ መሮ ዲሪባ ውይይቱን አስመልክቶ ቢቢሲ ባናገረው ወቅት ከመንግሥት ጋር የሚደረገውን ድርድር መጀመሩ ተስፋ ሰጪ ቢሆንም ጊዜ ሊወስድ የሚችል መሆኑን ጠቁሞ ነበር።

ሁለቱ ወገኖች ውይይቱ እንደሚካሄድ ከመናገር ውጪ ዝርዝር መረጃዎችን ያልሰጡ ሲሆን፣ የታንዛንያም ሆነ ውይይቱ እየተካሄደበት ካለው የዛንዚባር አስተዳደሮችም ዝርዝር ከመናገር ተቆጥበዋል።

የዛንዚባር ባለሥልጣናት ውይይቱ እየተካሄደ እንደሆነ ቢናገሩም የድርድሩ አካል እንዳልሆኑ እና ከአዘጋጅነት የዘለለ ሚና የለንም ሲሉ ለቢቢሲ ተናግረዋል።

Skip podcast promotion and continue reading
የቢቢሲ አማርኛ ዩቲዩብ ቻናል

ዜና፣ ትንታኔ እና ታሪኮችን በምሥል እና በድምጽ ለማግኘት

ይህንን በመጫን ሰብስክራይብ ያድርጉ

End of podcast promotion

የኢትዮጵያ መንግሥትን በመወከል የጠቅላይ ሚኒስትሩ የብሔራዊ ደኅነት አማካሪ አምባሳደር ሬድዋን ሁሴን እና የፍትህ ሚኒስትሩ ጌዴዎን ጢሞቴዎስ ተደራዳሪ ሆነው መቅረባቸውንም ቢቢሲ ከምንጮቹ መረጃ አግኝቷል።

ሁለቱ ልዑካን በትግራይ ተቀስቅሶ ወደ አማራ እና አፋር ክልሎች ተዛምቶ ለበርካቶች ሰዎች እልቂት ለሆነው ጦርነት እልባት ለማግኘት የፌደራሉን መንግሥት ወክለው ከህወሓት ጋር የተደራደሩት ልዑካን አባል መሆናቸው ይታወሳል።

በአሮሞ ነጻነት ሠራዊት በኩል ደግሞ የታሪክ ምሁሩ እና በአሜሪካ የጆርጂያ ስቴት ዩኒቨርስቲ መምህር የሆኑት ፕሮፌሰር መሐመድ ሐሰን፣ ከኦነግ መስራቾች አንዱና ለበርካታ ዓመታት አመራር የነበሩት ጣሃ አብዲ እንዲሁም የጦሩ አዛዥ ዋና አማካሪ የሆኑት ጂሬኛ ጉደታ ይገኙበታል።

በኦሮሚያ ክልል ለበርካታ ንጹሃን ሕይወት መቀጠፍ እና መፈናቀል ምክንያት የሆነው ጦርነት በሰላም እንዲቋጭም ግፊቶችም ሲደረጉ ቆይተዋል።

ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ የመንግሥታቸውን የስድስት ወራት አፈጻጸም ሪፖርት ባቀረቡበት መጋቢት 19/ 2015 ዓ.ም. በብልጽግና ፓርቲ ምክትል ፕሬዚዳንት የሚመራ የሰላም ኮሚቴ መቋቋሙን እና ሥራዎችም እየተሰሩ መሆናቸውን ጠቅሰው ነበር።

ጠቅላይ ሚኒስትሩ የምክትል ፕሬዚዳንቱን ስም ያልጠቀሱ ሲሆን ብልጽግናን በምክትልነት እየመሩ ያሉት አቶ ደመቀ መኮንን እና አቶ አደም ፋራህ ሲሆኑ ተቋቁሟል የተባለው ኮሚቴ በማን እንደሚመራ አልጠቀሱም ነበር።

በዚህ ሳምንት መጀመሪያ ላይ ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትር ደመቀ መኮንን ድርድሩ እየተካሄደበት ያለውን ታንዛንያን ጨምሮ በምሥራቅ አፍሪካ አገራት ጉብኝት ማድረጋቸው የተገለጸ ሲሆን፣ ጉዟቸው ከንግግሩ ጋር ግንኙነት እንዳለው ግን የተባለ ነገር የለም።

ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ ቀደም ሲል ከኦሮሞ ነጻነት ሠራዊት ወይም መንግሥት ሸኔ እያለ ከሚጠራው ኃይል ጋር አስር ያህል የውይይት ጥረቶች መደረጋቸውን ገልጸው፣ ቡድኑ አንድ የተዋቀረ ኃይል ባለመሆኑ ከተለያዩ ኃይሎችም የተለያዩ ሃሳቦች በመቅረባቸው ሂደቱ መጓተቱን መግለጻቸው ይታወሳል።

የአማጺው ቡድን መሪ በበኩሉ “በቅርቡ” የኦሮሞ ነጻነት ሠራዊት እና መንግሥት ሦስተኛ ወገን ባለበት በኬንያ ለመነጋገር ቀጠሮ ይዘው የኦሮሞ ነጻነት ሠራዊት ተወካዮች በቦታው ቢገኙም የመንግሥት ተወካዮች ግን ሳይገኙ ቀርተዋል ብሏል።

“በሌሎች አገራት ግብዣ በኬንያ ለመገናኘት ቀጠሮ ነበር። ነገር ግን መንግሥት ሳይገኝ ቀረ” ያለ ሲሆን፤ በአሁኑ ድርድር ስኬት ላይ ጥርጣሬዎች ቢኖሩም የንግግር ሂደቱ ሰላም ሊያመጣ ይችላል የሚል ተስፋ እንዳለው ጨምሮ ተናግሯል።

“ንግግር መጀመሩ ጥሩ ነው። መነጋገር እና መፍታት ያለብን ብዙ ነገሮች ስላሉ ጉዳዩ በአንድ ጊዜ የሚጠናቀቅ አይሆንም” ብሏል።

ከኦሮሞ ነጻነት ግንባር (ኦነግ) ተለይቶ የወጣው እና መንግሥት ሸኔ የሚለው የኦሮሞ ነጻነት ሠራዊት፣ ባለፉት ዓመታት በአራቱ የወለጋ ዞኖች፣ በምዕራብ ሸዋ እና ደቡብ ኦሮሚያ አካባቢዎች ሲንቀሳቀስ ቆይቷል።

የኦሮሞ ነጻነት ሠራዊት ተቀዳሚው ዓላማ የኦሮሞ ሕዝብ የራሱን መብት በራሱ እንዲወስን እና ዲሞክራሲ፣ ፍትህ እና ሕገ መንግሥታዊ ሥርዓት እንዲመለስ እታገለላለሁ የሚል ድርጅት እንደሆነ ይገልጻል።

ዛንዚባር