በመንግሥት እና በኦሮሞ ነጻነት ሠራዊት መካከል በታንዛኒያ የሚደረገው ድርድር ተጀመረ

ድርድሩ በታንዛኒያዋ ራስ ገዝ አስተዳደር በሆነችው ዛንዚባር ደሴት እየተካሄደ ነው።
የምስሉ መግለጫ, ድርድሩ በታንዛኒያዋ ራስ ገዝ አስተዳደር በሆነችው ዛንዚባር ደሴት እየተካሄደ ነው።

በፌደራል መንግሥቱ እና በኦሮሞ ነጻነት ሠራዊት መካከል የሚደረገው ድርድር ትናንት ማክሰኞ ሚያዚያ 17/2015 ዓ.ም. በታንዛኒያዋ ራስ ገዝ ግዛት መጀመሩ ተገለጸ።

በድርድሩ ስፍራ የሚገኙ የቢቢሲ ምንጮች ሁለቱም ተደራዳሪ አካላት ስድስት- ስድስት ተወካዮችን ልክው ድርድሩ ትናንት ረፋድ ላይ መጀመሩን ተናግረዋል።

ሮይተርስ የዜና ወኪልም የምሥራቅ አፍሪካ የልማት በይነ መንግሥታት ባለሥልጣን (ኢጋድ) ዋና ፀሐፊ ቃል አቀባይ ኑር ሞሐመድ ሼክ ዋቢ አድርጎ ድርድሩ ትናንት መጀመሩን ዘግቧል።

የኢጋድ ዋና ፀሐፊ ቃል አቀባይ እንዳሉት በተጀመረው ንግግር “ፖለቲካዊ ስምምነት ላይ ይደረሳል” የሚል ተስፋ አላቸው።

ከጥቂት ቀናት በፊት ጠቅላይ ሚንስትር ዐቢይ አስተዳደራቸው 'ሸኔ' ብሎ ከሚጠራው ታጣቂ ቡድን ድርድር ሊያደርግ እንደሆነ ይፋ ማድረጋቸው ይታወሳል።

የኦሮሞ ነጻነት ሠራዊትም ከፌደራል መንግሥቱ ጋር ልዩነቶችን በንግግር ለመፍታት ከስምምነቱ መደረሱን አረጋግጧል።

ከዚህ ቀደም የሰሜን ኢትዮጵያን ጦርነት ለማስቆም የፌደራሉን መንግሥት ወክለው ከህወሓት ጋር ሲደራደሩ ከነበሩት መካከል አምባሳደር ሬድዋን ሁሴን እና የፍትሕ ሚንስትሩ ጌዲዮን ጢሞቲዮስ (ዶ/ር) በመንግሥት መወከላቸውን የቢቢሲ ምንጭ ተናግረዋል።

በአሮሞ ነጻነት ሠራዊት በኩል ደግሞ የታሪክ ምሁር ፕሮፌሰር መሐመድ ሐሰን እና የጦሩ አዛዥ አማካሪ የሆኑት ጂሬኛ ጉደታ እና አብዲ ጣሃ የተባሉ ግለሰብ ይገኙበታል።

ሁለቱ አካላት ለንግግር የተቀመጡት በታንዛኒያዋ ራስ ገዝ አስተዳደር በሆነችው ዛንዚባር ደሴት ሲሆን ንግግራቸው ለቀጣይ አምስት ቀናት ድረስ ሊቀጥል እንደሚችል ተነግሯል።

የኦሮሞ ነጻነት ሠራዊት ድርድሩ በግልጸኝነት የሚካሄድ ከሆነ ከሰላም ንግግሩ አዎንታዊ ነገር ሊገኝ እንደሚችል በመግለጫው ገልጾ ነበር።

የጦሩ ከፍተኛ አዛዥ የሆኑት መሮ ዲሪባ “የጥይት ድምጽ ሳይሰማ የኦሮሞ ሕዝብ ጥያቄ መልስ የሚያገኝ ከሆነ በራችን ሁሌም ክፍት ነው” ካሉ በኋላ፤ “ንግግር መጀመሩ ጥሩ ነው። . . . በመተማመን ላይ ተመስርቶ ከተካሄደ ለሰላም ወሳኝነት አለው” ሲሉ ለቢቢሲ ተናግረው ነበር።

የጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ መንግሥትም “ጦርነት ይብቃ፤ ሰላም እናጽና” በማለት ልዩነትን በንግግር ለመፍታት ፍላጎቱን አሳይቷል።

የኢትዮጵያ መንግሥት እና የኦሮሞ ነጻነት ሠራዊት በሚያደርጉት ድርድር ላይ የኖርዌይ፣ የኬንያ፣ የአውሮፓ ኅብረት፣ የአሜሪካ ዲፕሎማቶች እና የኢጋድ ተወካዮች እንደሚገኙ የቢቢሲ ምንጮች ገልጸዋለ።

ለጉዳዩ ቅርበት ያላቸው ምንጭ የተጠቀሷቸው አገራት በድርድሩ ላይ የሚኖራቸው ሚና እስካሁን ግልጽ አይደለም ብለዋል።

ላለፉት አራት ዓመታት በታጣቂ ኃይሉ እንቅስቃሴ ምክንያት በበርካታ የኦሮሚያ አካባቢዎች ሰላም ርቆ ዜጎች ለሞት እና ስደት ተዳርገዋል።

ለሁለት ዓመታት የዘለቀው ደም አፋሻሹ የሰሜን ኢትዮጵያው የእርስ በርስ ጦርነት በፌደራል መንግሥት እና በህወሓት መካከል የተደረሰው ሰምምነት እንዳስቆመው ሁሉ የመንግሥት እና የኦሮሞ ነጻነት ሠራዊት ንግግር ሰላም ለራቀው የኦሮሚያ ክልል ሰላምን ሊያመጣ ይችላል ተብሎ ተስፋ ተደርጓል።

ለዓመታት በመንግሥት ኃይሎች እና በአማጺው መካከል በተካሄዱ ግጭቶች እና በተፈጸሙ ጥቃቶች የተጎዱ እና ሰላማቸውን አጥተው የቆዩ የኦሮሚያ ክልል ነዋሪዎች ንግግር መጀመሩ የሰላም ተስፋን ሰጥቷቸዋል።